ትንቢተ ኢሳይያስ 2
2
ዘለዓለማዊ ሰላም
(ሚክ. 4፥1-3)
1የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ይሁዳ አገርና ስለ ኢየሩሳሌም ከተማ የተናገረው ቃል ይህ ነው፦
2የዘመኑ ፍጻሜ ሲደርስ
የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የተሠራበት ተራራ
ከሌሎች ተራራዎች ሁሉ በልጦ ይታያል፤
ከኰረብቶችም ሁሉ እጅግ ከፍ ይላል፤
የብዙ መንግሥታት ሕዝቦች ወደ እርሱ ይጐርፋሉ።
3ስለዚህ ብዙ ሕዝቦች እንዲህ ይላሉ፦
“ሕግ ከጽዮን፥ የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ስለሚገኝ
ኑ ወደ እግዚአብሔር ተራራ እንውጣ፤
ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤተ መቅደስም እንሂድ፤
እርሱ ፈቃዱን እንድናደርግ ያስተምረናል፤
እኛም በእርሱ መንገድ እንሄዳለን።”
4እርሱ በብዙ መንግሥታት መካከል በመፍረድ አለመግባባትን ያስወግዳል፤
ስለዚህም ሰይፋቸውን ወደ ማረሻ፥
ጦራቸውንም ወደ ማጭድ ይለውጣሉ፤
መንግሥት በመንግሥት ላይ ጦርነት አያነሣም፤
ከዚያም በኋላ የጦር ትምህርት የሚማር አይኖርም። #ኢዩ. 3፥10።
5እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ!
ኑ! በእግዚአብሔር ብርሃን እንመላለስ!
የእልኸኛነት መወገድ
6አምላክ ሆይ! የያዕቆብ ዘሮች የሆኑ ሕዝብህን እርግፍ አድርገህ ትተሃል፤ ምድሪቱ በምሥራቅ አገር ሰዎች ጥንቈላና በፍልስጥኤማውያን ሟርት ተሞልታለች፤ ሕዝቡም ከአሕዛብ ጋር ተባብረዋል። 7ምድራቸው በብርና በወርቅ ስለ ተሞላች፥ ሀብታቸው ከመጠን በላይ ነው፤ አገራቸው በፈረሶች የተሞላች ሆናለች፤ ሠረገሎቻቸውም እጅግ ብዙ ናቸው። 8ከዚህም ጋር ምድራቸው በጣዖት የተሞላች ሆናለች፤ በገዛ እጃቸውም ለሠሩት ምስል ይሰግዳሉ።
9ከዚህም የተነሣ በሁሉም ላይ ኀፍረትና ውርደት ይደርስባቸዋል፤ ጌታ ሆይ! በደላቸውን ይቅር አትበል!
10ከእግዚአብሔር ቊጣና ከአስፈሪ ግርማው ለማምለጥ በአለት ስንጣቂ ዋሻና በመሬት ጒድጓድ ውስጥ ተሸሸጉ! #ራዕ. 3፥10። #ራዕ. 6፥15፤ 2ተሰ. 1፥9። 11ትዕቢተኞች ይዋረዳሉ፤ ኩራተኞችም ይቀላሉ፤ እግዚአብሔር ብቻ በክብር ከፍ ከፍ ይላል፤ 12የሠራዊት አምላክ ትዕቢተኞችና ኩራተኞች የሚዋረዱበትን ቀን ወስኖአል። 13እርሱ ታላላቅ የሊባኖስ ዛፎችንና የባሳን የወርካ ዛፎችን ያጠፋል። 14ታላላቅ ተራራዎችንና ኰረብቶችን ዝቅ በማድረግ ደልዳላ ቦታ ያደርጋቸዋል። 15ረጃጅም የከተማ መጠበቂያ ግንቦችንና የጦር ምሽጎችን ሁሉ ዝቅ ያደርጋል፤ 16እጅግ የተዋቡ ዕቃዎችንና የተርሴስ መርከቦችን እንኳ ያሰጥማል፤ 17-18የሰዎች ኲራት ይጠፋል፤ እብሪት የሞላበት ትዕቢታቸውም ያከትማል፤ ጣዖቶች ሁሉ ይደመሰሳሉ፤ በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር ብቻ በክብር ከፍ ከፍ ይላል።
19እግዚአብሔር ምድርን ለማናወጥ በሚመጣበት ጊዜ ከቊጣውና ከአስፈሪ ግርማው ለማምለጥ በአለት ዋሻና በመሬት ንቃቃት ውስጥ ለመሸሸግ ይሞክራሉ። 20ሰዎች ይሰግዱላቸው ዘንድ በእጃቸው የሠሩአቸውን የብርና የወርቅ ምስሎች ለፍልፈሎችና ለሌሊት ወፎች እየጣሉላቸው ይሄዳሉ። 21እግዚአብሔር ምድርን ለማናወጥ በሚመጣበት ጊዜ ከቊጣውና ከአስፈሪ ግርማው ተሰውረው ለማምለጥ በድንጋይ ዋሻና በተሰነጠቀ አለት ውስጥ ይሸሸጋሉ።
22እንግዲህ ትንፋሹ አፍንጫው ላይ በሆነች በሟች ሰው መተማመናችሁ ይቅር፤ እርሱ ለምንም አይጠቅምም።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 2: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997