የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 19

19
በግብጽ ላይ የተነገረ የእግዚአብሔር ቃል
1ስለ ግብጽ የተነገረ የእግዚአብሔር ቃል የሚከተለው ነው፦
እነሆ፥ እግዚአብሔር በደመና ሆኖ በፍጥነት ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጻውያን ጣዖቶች በፊቱ ይናወጣሉ፤ የግብጽ ሕዝብም በፍርሃት ይርበደበዳሉ። 2እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በግብጽ ምድር የእርስ በርስ ጦርነት እንዲቀሰቀስ አደርጋለሁ፤ ወንድም በወንድሙ ላይ፥ ጐረቤትም በጐረቤቱ ላይ በጠላትነት እንዲነሣ አደርጋለሁ፤ ከተሞች በከተሞች ላይ፥ ነገሥታት በነገሥታት ላይ በጠላትነት ተነሥተው ይዋጋሉ። 3ግብጻውያን ተስፋ ይቈርጣሉ፤ ዕቅዳቸውም ተግባራዊ እንዳይሆን አደርጋለሁ፤ በዚህም ጊዜ እንዲረዱአቸው ጣዖቶቻቸውን ይጠይቃሉ፤ ሙታንን ወደሚጠሩ ጠንቋዮቻቸው ሄደው ይማከራሉ፤ ከሙታን መናፍስትም ምክር ይጠይቃሉ። 4እነርሱን በጭካኔ ለሚገዛቸው ንጉሥ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ እኔ ጌታ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
5በዓባይ ውስጥ ያለው ውሃ ዝቅ ይላል፤ ወንዙም ቀስ በቀስ ይደርቃል፤ 6ወንዞቹ ይገማሉ፤ የግብጽ መስኖ ውሃ ቀስ በቀስ እየጐደለ ይደርቃል፤ ደንገሎቹና ቀጤማዎቹ ይጠወልጋሉ። 7በዓባይ ወንዝ ዳርቻ ያለው አትክልት ሁሉ ይደርቃል፤ በወንዙ አጠገብ የተዘራውም ሰብል ሁሉ ደርቆ ነፋስ ይወስደዋል። 8መንጠቆአቸውን ወደ አባይ ወንዝ የሚጥሉ ዓሣ አጥማጆች ያዝናሉ፤ ያለቅሳሉም፤ መረቦቻቸውንም በውሃ ላይ የሚዘረጉ ተስፋ ይቈርጣሉ፤ 9የተበጠረውን የተልባ እግር የሚሠሩ ተስፋ ይቈርጣሉ ቀጭን ሐር የሚሠሩ ያፍራሉ። 10ሸማኔዎች ግራ ይጋባሉ፤ ደመወዝተኞችም እየጮኹ ያለቅሳሉ።
11በጾዓን ያሉ የንጉሡ ባለ ሥልጣኖች ፍጹም ሞኞች ናቸው፤ ጠቢባን የሆኑት የግብጽ ንጉሥ አማካሪዎች ጥቅም የሌለው ምክር ይመክራሉ፤ እንዴት አድርገው ለንጉሡ “እኛ ብልኆች ነን፤ ዘራችንም ከቀድሞ ነገሥታት ሲወርድ፥ ሲዋረድ የመጣ ነው” ይላሉ? 12የግብጽ ንጉሥ ሆይ! እነዚያ ብልኆች አማካሪዎችህ የት አሉ? የሠራዊት አምላክ በግብጽ ላይ ያቀደውን ይንገሩህ። 13የጾዓን ባለ ሥልጣኖች ሞኞች ሆኑ፤ የሜምፊስ መሪዎችም ተታለሉ፤ የሕዝብዋ ከፍተኛ አማካሪዎች ግብጽን አሳትዋት። 14የተዘበራረቀ ምክር እንዲሰጡ ያደረጋቸውም እግዚአብሔር ነው፤ በመጨረሻም ግብጽ በሁሉ ነገር በመሳሳት የገዛ ትፋቱ አዳልጦት እንደሚጥለው ሰካራም ትንገዳገዳለች። 15በግብጽ ባለጸጋም ሆነ ድኻ፥ ዝነኛ የሆነ ወይም ታዋቂነት የሌለው ምንም ነገር ማድረግ አይችልም።
ስለ ግብጽ የተነገረ ትንቢት
16የግብጽ ሕዝብ በፍርሃት እንደ ሴት የሚሆኑበት ጊዜ ይመጣል፤ የሠራዊት አምላክ እነርሱን ለመቅጣት ኀይሉን በሚያሳይበት ጊዜ በፍርሃት ይንቀጠቀጣሉ፤ 17ይሁዳ ለግብጽ ሕዝብ አስፈሪ ትሆናለች፤ የይሁዳ ስም ሲነሣ እንኳ በጣም ይሸበራሉ፤ ይህም የሚሆነው የሠራዊት አምላክ እነርሱን ለመቅጣት መዘጋጀቱን በማወቃቸው ነው።
18በዚያን ጊዜ በግብጽ ውስጥ የሚገኙ አምስት ከተሞች የዕብራውያን ቋንቋ ይናገራሉ፤ በዚያም የሚኖሩ ሕዝቦች በሠራዊት አምላክ ስም ይምላሉ፤ ከእነዚህ ከተሞች አንዲቱ “የፀሐይ ከተማ” ተብላ ትጠራለች።
19በዚያን ጊዜ በግብጽ ምድር መካከል ለእግዚአብሔር መሠዊያ ይሠራል፤ እንዲሁም በግብጽ ጠረፍ ላይ ለእግዚአብሔር የተለየ የድንጋይ ዐምድ ይተከላል። 20እነርሱም የሠራዊት አምላክ በግብጽ ምድር ለመኖሩ ምልክትና ምስክር ይሆናሉ፤ በዚያ የሚኖሩ ሕዝቦች ችግር ሲደርስባቸው እግዚአብሔር እንዲረዳቸው በሚጠይቁበት ጊዜ የሚታደጋቸውን አዳኝ ይልክላቸዋል፤ እርሱም ከጠላቶቻቸው ያድናቸዋል። 21እግዚአብሔር ለግብጽ ሕዝብ ራሱን ይገልጥላቸዋል፤ በዚያን ጊዜ እነርሱም አምላክነቱን ዐውቀው ይሰግዱለታል፤ መሥዋዕትና መባም ያቀርቡለታል፤ ለእግዚአብሔርም ስእለት ይሳላሉ፤ ስእለታቸውንም ሁሉ ይፈጽማሉ። 22እግዚአብሔር ግብጻውያንን ይቀጣል፤ ነገር ግን መልሶ ይፈውሳቸዋል፤ ወደ እርሱ ይመለሳሉ፤ እርሱም ጸሎታቸውን ሰምቶ ይፈውሳቸዋል።
23በዚያን ጊዜ በግብጽና በአሦር መካከል አውራ ጎዳና ይከፈታል፤ የእነዚህ ሁለት አገር ሕዝቦች አንዱ ወገን ወደ ሌላ ይተላለፋሉ፤ የሁለቱም ሕዝቦች አምልኮ አንድ ዐይነት ይሆናል። 24በዚያን ጊዜ እስራኤል ከግብጽና ከአሦር ጋር ተደምራ ሦስተኛ አገር ትሆናለች፤ እነዚህም ሦስት ሕዝቦች በዓለም መካከል በረከት ይሆናሉ። 25የሠራዊት አምላክም “እናንተ በግብጽ የምትኖሩ ሕዝቤ፥ የፈጠርኳችሁ አሦራውያንና የመረጥኳችሁ የእስራኤል ሕዝብ የተባረካችሁ ሁኑ” ይላቸዋል። #ኤር. 46፥2-26፤ ሕዝ. 29፥1—32፥32።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ