የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሆሴዕ 7

7
1“ሕዝቤን እስራኤልን ለመፈወስና እንደገናም እንዲበለጽጉ ለማድረግ በፈለግሁ ጊዜ የሕዝቡ በደልና የሰማርያ ክፋት ጐልቶ ይታያል፤ እርስ በርሳቸው ሐሰት ይናገራሉ፤ ቤት እየሰበሩ ይሰርቃሉ፤ በቡድን በቡድን ሆነው በየመንገዱ ይዘርፋሉ። 2ነገር ግን እኔ ይህን ሁሉ ክፋታቸውን እንደማስታውስ ከቶ አይገነዘቡም፤ ከዚህ የተነሣ በገዛ ኃጢአታቸው ተከበዋል፤ ክፉ ሥራቸው ሁሉ ከእኔ የተሰወረ አይደለም።”
በቤተ መንግሥት የተደረገ ሤራ
3እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እነርሱ ንጉሡን በክፋታቸው፥ መኳንንቱን በውሸታቸው ያስደስታሉ። 4ሁሉ ዘማውያን ናቸው፤ ሊጡ እስኪቦካለት ድረስ ዳቦ ጋጋሪው እሳቱን መቈስቈስ እንደማያስፈልገው እንደ ጋለ ምድጃ ናቸው። 5በንጉሣቸው ክብረ በዓል ቀን መኳንንቱ ብዙ የወይን ጠጅ በመጠጣት ሰክረው ታመሙ፤ ጋጋሪውም ለሚያፌዙ ሰዎች ምልክት ለመስጠት እጁን ዘረጋ። 6ሤራ ለመጐንጐን ልባቸው እንደ ምድጃ የጋለ ነው፤ ቊጣቸው ሌሊቱን ሙሉ ሲጤስ ያድራል፤ ሲነጋ ግን እንደሚነድ እሳት ይንበለበላል። #7፥6 ጋጋሪው፦ በዕብራይስጥ “እርሱ” ብቻ የሚል ሲሆን ከላይ አመጣጡ ጋጋሪውን ያመለክታል፤ በአንዳንድ ትርጒም ግን “ንጉሡ” የሚለውን ተከትለዋል።
7“ሁሉም በቊጣ እንደ ምድጃ ግለው ገዢዎቻቸውን ፈጁ፤ ንጉሦቻቸውንም በየተራ አጠፉ፤ ይህም ሁሉ ሲሆን ከእነርሱ አንድ እንኳ የእኔን ርዳታ የጠየቀ የለም።”
የእስራኤል ሕዝብ ከአሕዛብ ጋር መደባለቃቸው
8እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤል ሕዝብ ከአሕዛብ ጋር ተደባለቁ፤ በዚህም ምክንያት እነርሱ እንዳልተገለበጠ ቂጣ የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ 9ባዕዳን ጒልበታቸውን በዘበዙት፤ እነርሱ ግን አልተገነዘቡትም፤ ሽበት ጣል ጣል አድርጎባቸዋል፤ እነርሱ ግን አልተገነዘቡትም። 10የእስራኤል ሕዝብ ትምክሕታቸው በራሳቸው ላይ ይመሰክርባቸዋል፤ ይህም ሁሉ ሆኖ ወደ እኔ ወደ አምላካቸው አልተመለሱም ከቶም አልፈለጉኝም። 11የእስራኤል ሕዝብ እንደ ርግብ የዋህና አእምሮ የጐደላቸው ሆነዋል፤ ስለዚህም ርዳታ ለማግኘት አንድ ጊዜ ወደ ግብጽ ይጣራሉ፤ አንድ ጊዜም ወደ አሦር ይበራሉ። 12በሚዘዋወሩበት ቦታ ሁሉ ወጥመዴን ዘርግቼ እንደ ወፍ እይዛቸዋለሁ፤ ስለ ሠሩትም ክፉ ሥራ እቀጣቸዋለሁ።
13“ከእኔ ርቀው ስለ ሄዱ ወዮላቸው! በእኔም ላይ ስለ ዐመፁ ጥፋት ይምጣባቸው፤ እኔ ልታደጋቸው ፈልጌ ነበር፤ እነርሱ ግን በእኔ ላይ ሐሰት ይናገራሉ። 14በአልጋቸው ላይ ተጋድመው ይጮኻሉ እንጂ ከልባቸው ወደ እኔ አይጸልዩም፤ እህልና የወይን ጠጅ ለማግኘት ሰውነታቸውን ይተለትላሉ፤ በእኔም ላይ ያምፃሉ። 15ያሠለጠንኳቸውና ጒልበታቸው አንዲጠነክር ያደረግኹ እኔ ነኝ፤ እነርሱ ግን በእኔ ላይ ያሤራሉ፤ 16ከእኔ ርቀው ወደ ከንቱ አምልኮ ተመለሱ፤ ዓላማውን እንደሚስት እንደ ተበላሸ ቀስት ሆኑ፤ አለቆቻቸውም ክፉ ነገርን ከመናገራቸው የተነሣ በሰይፍ ተመተው ይሞታሉ፤ በግብጻውያንም ዘንድ መዘባበቻ ይሆናሉ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ