ትንቢተ ሆሴዕ 5
5
ስለ ጣዖት አምልኮ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
1“ካህናት ሆይ! ይህን ስሙ!
እናንተም የእስራኤል ሕዝብ አስተውሉ!
እናንተም ንጉሣውያን ቤተሰብ ይህን አድምጡ! እነሆ ፍርድ በእናንተ ላይ መጥቶአል፤ በምጽጳ እንደ ወጥመድ፥ በታቦርም እንደ ተዘረጋ መረብ ሆናችኋል።
2ዐመፀኞች የግድያ ሥራቸውን አስፋፍተዋል፤ ስለዚህ ሁሉንም እቀጣቸዋለሁ።
3“እኔ የአንቺን የእስራኤልን ሁኔታ ዐውቃለሁ፤ ከእኔ መሰወር አይቻልሽም፤ በጣዖት አምልኮ ዝሙት ረክሰሻል።”
4የዝሙት መንፈስ በእስራኤል ሕዝብ ውስጥ ስላለና እግዚአብሔርንም ስለማያውቁ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ሥራቸው አይፈቅድላቸውም። 5የእስራኤል ሕዝብ ትምክሕት በራሳቸው ላይ ይመሰክርባቸዋል፤ ኃጢአታቸውም መሰናክል ሆኖ ይጥላቸዋል፤ የይሁዳም ሕዝብ ከእነርሱ ጋር ተሰናክለው ይወድቃሉ። 6መሥዋዕት አድርገው ለማቅረብ በጎቻቸውንና ከብቶቻቸውን ነድተው እግዚአብሔርን ለመፈለግ ይሄዳሉ፤ ነገር ግን እርሱ ስለ ተለያቸው አያገኙትም። 7እነርሱ ራሳቸው ጣዖት አምላኪዎች ስለ ሆኑ ለእግዚአብሔር ታማኞች ሆነው አልተገኙም። ልጆቻቸውም እንደ ጣዖት ልጆች ተቆጥረዋል፤ ስለዚህ በዚህ ወር መባቻ እነርሱም ምድራቸውም አብረው ይጠፋሉ።
በይሁዳና በእስራኤል መካከል ስለሚደረገው ጦርነት
8ለጦርነት እንዲወጡ በገባዖን የመለከት፥ በራማም የጥሩንባ ድምፅ አሰሙ! በቤትአዌን “የብንያም ነገድ ሆይ! ከአንተ ጋር ነን” እያላችሁ ጩኹ! 9በቅጣት ቀን እስራኤል ባድማ ትሆናለች፤ ይህም በእርግጥ እኔ በእስራኤል ነገዶች ላይ እንዲደርስ የወሰንኩት ጥፋት ነው።
10እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የይሁዳ መሪዎች የእስራኤልን ድንበር እንደሚያፈርሱ ሰዎች ሆነዋል፤ ስለዚህ እኔ ቊጣዬን እንደ ጐርፍ ውሃ አወርድባቸዋለሁ። 11እስራኤል ከንቱ ነገርን በመከተል ላይ ስለ ጸና ጭቈናና ፍትሕ ማጣት ደረሰበት። 12ስለዚህ ብልና ነቀዝ እህልንና እንጨትን እንደሚያጠፉ እኔም እስራኤልንና ይሁዳን አጠፋለሁ።
13“እስራኤል መታመሙን፥ ይሁዳም መቊሰሉን ባየ ጊዜ፥ እስራኤል ወደ አሦር ፊቱን መለሰ፤ ርዳታም ለማግኘት ወደ ታላቁ ንጉሥ መልእክተኛ ላከ፤ ነገር ግን እርሱ ሊያድናቸው ወይም ቊስላቸውን ሊፈውስ አልቻለም። 14ከዚህ የተነሣ እስራኤልን እንደ አንበሳ፥ ይሁዳንም እንደ ደቦል አንበሳ በመሆን ሰባብሬአቸው እሄዳለሁ፤ ነጥቄ እወስዳቸዋለሁ፤ ማንም ሊያድናቸው አይችልም።
15“መከራ ሲበዛባቸው እኔን ይፈልጋሉ፤ ስለዚህ የሠሩትን በደል ተገንዝበው ወደ እኔ እስከሚመለሱ፥ ድረስ ከእነርሱ እርቃለሁ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ሆሴዕ 5: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997