የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሆሴዕ 2

2
1ስለዚህ ወንድሞቻችሁ የሆኑትን እስራኤላውያንን “አሚ” እኅቶቻችሁንም “ሩሃማ” ብላችሁ ጥሩአቸው። #2፥1 አሚ፦ “ሕዝቤ” ማለት ነው። #2፥1 ሩሃማ፦ “ምሕረት የሚደረግለት” ማለት ነው።
የእስራኤል ሕዝብ ባለመታመኑ መቀጣቱ
2ልጆቼ ሆይ! ከእንግዲህ ወዲያ እናታችሁ ሚስቴ ስላልሆነችና እኔም ባልዋ ስላልሆንኩ የዝሙት አመለካከትዋንና አመንዝራነትዋን እንድታስወግድ ውቀስዋት። 3ባትመለስ ግን እንደ ተወለደችበት ቀን እርቃንዋን አስቀራታለሁ፤ እንደ ደረቀ ባዶ ምድር አደርጋታለሁ፤ በውሃ ጥምም እገድላታለሁ። 4ከዘማዊት ሴት የተወለዱ ስለ ሆኑ ለልጆችዋም አልራራላቸውም። 5እናታቸው አመንዝራ ስለ ሆነች እነርሱን ባሳፋሪ መንገድ ፀንሳቸዋለች፤ እርስዋም ይህን ያደረገችው ምግቤንና ውሃዬን፥ የሱፍና የተልባ እግር ልብሴን፥ ዘይቴንና መጠጤን የሚሰጡኝ ስለ ሆነ ፍቅረኞቼን ተከትዬ እሄዳለሁ ብላ ነው።
6ስለዚህ መንገድዋን በእሾኽ እዘጋዋለሁ፤ መውጫ በር እንዳታገኝም ዙሪያውን በግንብ አጥራለሁ። 7ፍቅረኞችዋን ተከትላ ትሄዳለች፤ ነገር ግን ልትደርስባቸው አትችልም፤ ትፈልጋቸዋለች፤ ነገር ግን አታገኛቸውም፤ ከዚህ በኋላ “ከአሁኑ ኑሮዬ ይልቅ የዱሮው ይሻለኛል፤ ስለዚህ ወደ ቀድሞው ባሌ እሄዳለሁ” ትላለች።
8እርስዋ እህልን፥ የወይን ጠጅን፥ የወይራ ዘይትን የሰጠኋት፥ እኔ እንደ ሆንኩ ከቶ አልተገነዘበችም፤ እኔ ያበዛሁላትን ብርና ወርቅ “በዓል” ተብሎ ለሚጠራው ጣዖት አቀረበች። 9እህሉን በመከር ጊዜ ወይኑንም በወቅቱ እወስድባታለሁ፤ ራቁትነትዋን የምትሸፍንባቸውን የሱፍና የተልባ እግር ልብሶቼንም እወስድባታለሁ። 10በፍቅረኞችዋም ፊት እርቃንዋን አስቀራታለሁ፤ ከእጄም የሚያድናት የለም። 11የምትደሰትባቸውን በዓላትዋን ሁሉ ሰንበትዋን፥ ዓመታዊና ወርኀዊ በዓላትዋን እሽራለሁ፤ የተለዩ በዓላትዋንም ሁሉ እንዳታከብር አደርጋታለሁ። 12ከፍቅረኛዎችዋም ያገኘቻቸውን የወይን ተክሎችና የበለስ ዛፎች እነቃቅላለሁ፤ የወይንና የፍራፍሬ እርሻዎችዋን ወደ ጫካነት እለውጣለሁ፤ የዱር አራዊትም ይበሉአቸዋል። 13“በዓል” ለሚባለው ጣዖት ለማጠንና ጌጣጌጥዋን አድርጋ ፍቅረኛዎችዋን በመከተል እኔን በመተዋ እቀጣታለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር።
እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለው ፍቅር
14ስለዚህ እንደገና ወደ በረሓ እወስዳታለሁ፤ እዚያም በፍቅር ቃል አባብዬ እማርካታለሁ። 15የቀድሞውን የወይን ተክል እመልስላታለሁ፤ የመከራንም ሸለቆ የተስፋ በር እንዲሆናት አደርጋለሁ፤ እዚያም ከግብጽ ስትወጣ በወጣትነትዋ ወራት በነበራት ሁኔታ በደስታ ትዘምራለች። #ኢያሱ 7፥24-26። 16በዚያን ቀን “ባለቤቴ” ብላ እንጂ እንደ በዓል ጣዖት “ጌታዬ” ብላ አትጠራኝም። 17ከአንደበትዋ የ“በዓል” ጣዖቶችን ስም ለማስወግድ የእነርሱ ስም ዳግመኛ አይጠራም።
18በዚያን ጊዜ ስለ እናንተ ከአራዊት፥ ከሰማይ ወፎችና በደረታቸው በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጥረቶች ጋር ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ ከምድሪቱም ላይ ቀስትን፥ ሰይፍንና ጦርነትን አስወግዳለሁ፤ እናንተንም በሰላም እንድታርፉ አደርጋለሁ።
19እስራኤል ሆይ! ለዘለዓለም እንደ ባለቤቴ አደርግሻለሁ፤
በጽድቅ፥ በፍትሕ፥ በዘለዓለማዊ ፍቅርና በምሕረት
እንደ ባለቤቴ እንድትሆኚ አደርጋለሁ።
20ቃል ኪዳኔን በመጠበቅ እንደ ባለቤቴ አደርግሻለሁ፤
አንቺም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ታውቂያለሽ።
21እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በዚያን ቀን እኔ መልስ አሰጣለሁ፤
እኔ ለሰማያት መልስ እሰጣለሁ፤
ሰማያትም ለምድር መልስ ይሰጣሉ።
22ምድርም እህልን፥ ወይንንና የወይራ ዘይትን በማስገኘት
ለኢይዝራኤል መልስ ትሰጣለች።
23ሕዝቤን በምድሪቱ ላይ እመሠርታለሁ፤
እንዲበለጽጉም አደርጋቸዋለሁ፤
‘ምሕረት አይደረግላችሁም’ የተባሉትን ምሕረት አደርግላቸዋለሁ፤
‘ሕዝቤ አይደላችሁም’ የተባሉትንም ‘ሕዝቤ ናችሁ’ እላቸዋለሁ፤
እነርሱም ‘አንተ አምላካችን ነህ’ ይሉኛል።” #ሮም 9፥25፤ 1ጴጥ. 2፥10።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ