ትንቢተ ዕንባቆም 3
3
የዕንባቆም ጸሎት
1በመዝሙር የቀረበ የነቢዩ ዕንባቆም ጸሎት ይህ ነው፤
2እግዚአብሔር ሆይ! ስላደረግኸው አስደናቂ ሥራ ሁሉ ሰምቼ እጅግ ፈራሁ፤
አሁንም በዘመናችን የቀድሞውን ሥራህን ደግመህ አድርግ፤
በየዘመናቱም እንዲታወቅ አድርግ፤
በምትቈጣበት ጊዜ እንኳ ምሕረትህን አታርቅ።
3እግዚአብሔር በቅድስናው ከቴማን አገርና፥
ከፋራን ተራራ እንደገና ይመጣል፤
መለኮታዊ ክብሩ ሰማያትን ሸፍኖአል፤
ምስጋናውም ምድርን ሞልቶአል።
4ብርሃኑ እንደ ፀሐይ ብርሃን ነው
ኀይሉን ከሸፈነው እጁም
የብርሃን ጮራ ይወጣል፤
5ቸነፈር ፊት ፊቱ ይሄዳል፤
መቅሠፍትም ከኋላው ይከተለዋል።
6እርሱ ሲቆም ምድር ትናወጣለች፤
እርሱ ሲመለከታቸው ሕዝቦች ይንቀጠቀጣሉ፤
የጥንቱ ተራራዎች ይናዳሉ፤
ከጥንት ጀምሮ የእርሱ መረማመጃ የነበሩት ኰረብቶች
ወደ ታች ይሰጥማሉ።
7የኢትዮጵያ ሰፈር ሲጨነቅ፥
የምድያምም ሰዎች ሲንቀጠቀጡ አየሁ። #3፥7 ኢትዮጵያ፦ ይህ ኢትዮጵያ የሚለው ቃል የሚገኘው በሰብዓ ሊቃናት ትርጓሜ ነው እንጂ በዕብራይስጡ ኩሻን ይላል። ኩሽና ኩሻን የተለያዩ ቃላት ናቸው። ኢትዮጵያ የምትጠራበት የዕብራይስጡ ቃል ኩሽ ነው እንጂ ኩሻን አይደለም። ኩሻን የሚባሉት በኤዶም አጠገብ ይኖሩ የነበሩ የዐረብ ነገድ ናቸው። (መሳ. 3፥8-10)
8እግዚአብሔር ሆይ! ፈረሶችህንና ሠረገላዎችህን ወደ ድል በመራኸቸው ጊዜ፥
ኀይለኛው ቊጣህ በወንዞች ላይ ነበርን?
ወይስ በባሕሩ ላይ ተቈጥተህ ነበርን?
9ቀስትህን ከሰገባው አወጣህ፤
ፍላጻህንም ለመወርወር አነጣጠርህ፤
ምድሪቱንም ሰንጥቀህ ወንዞች አስገኘህ።
10ተራራዎች አንተን አይተው በፍርሃት ተንቀጠቀጡ፤
የዝናብም ጐርፍ ምድርን እየጠራረገ አለፈ፤
ውቅያኖስ ከፍተኛ ድምፅ አሰማ፤
ማዕበሉም ወደ ላይ ከፍ ከፍ አለ።
11እንደ ፍላጻ ከሚወረወረውና
እንደ ጦር ከሚያንጸባርቀው መብረቅህ የተነሣ
ፀሐይና ጨረቃ በየቦታቸው ቆሙ።
12በምድር ላይ ቆምክ፤
በቊጣህም ሕዝቦችን ረጋገጥካቸው።
13ሕዝብህን ለመታደግ፥ ቀብተህ ያነገሥከውንም ንጉሥ ለማዳን ወጣህ፤
የጥፋት አገር መሪ የሆነውን ቀጠቀጥከው፤
ተከታዮቹንም አጥፍተህ እርቃኑን አስቀረኸው።
ከእግር እስከ ራሱም አራቈትከው።
14እኛን ለመበታተን እንደ ዐውሎ ነፋስ የመጣውን
የጦረኞቹን አለቃ በገዛ ቀስቱ ወጋኸው።
ደካማ እንስሶችን ለመቦጨቅ እንደሚጓጓ አውሬ
እርሱም የተደበቁትን ድኾች ለማጥቃት የተዘጋጀ ነበር።
15አንተ ባሕሩን በፈረሶችህ በምትረጋግጥበት ጊዜ
ጥልቁ ባሕር ይናወጣል።
16ይህን ሁሉ ስሰማ ሰውነቴ ይርበደበዳል፤
ድምፁም ከንፈሮቼን ያንቀጠቅጣል፤
አጥንቶቼ ይበሰብሳሉ፤
እግሮቼ ከታች ይብረከረካሉ፤
በጠላቶቻችን ላይ መከራ የሚደርስበትን ጊዜ
በትዕግሥት እጠባበቃለሁ።
17ምንም እንኳ የበለስ ዛፍ ባያብብ፥
በወይን ተክል ላይም ፍሬ ባይገኝ፥
የወይራ ዛፍም ምንም ፍሬ ባይሰጥ፥
በእርሻዎች ላይ ሰብል ቢጠፋ፥
የበግ መንጋዎች ሁሉ ቢያልቁ፥
በበረት ውስጥ ምንም ከብት ባይገኝ፥
18ይህም ሁሉ ቢሆን፥ እኔ በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤
በአምላኬ፥ በመድኃኒቴ ሐሤት አደርጋለሁ።
19ጌታ እግዚአብሔር ብርታቴ ነው፤
እግሮቼንም እንደ ዋልያ እግሮች ያጠነክርልኛል፤
በተራሮችም ላይ እንድራመድ ያደርገኛል። #2ሳሙ. 22፥34፤ መዝ. 18፥33።
Currently Selected:
ትንቢተ ዕንባቆም 3: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997