እግዚአብሔር ኖኅንና ልጆቹን ባረካቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “ብዙ፥ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት፤ እንስሶች፥ ወፎች፥ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችና ዓሣዎች ሁሉ እናንተን በመፍራትና በመደንገጥ ይኑሩ፤ ሁሉም በሥልጣናችሁ ሥር ይሁኑ። ከዚህ በፊት የአትክልት ዐይነቶችን ምግብ አድርጌ እንደሰጠኋችሁ እነዚህንም ተንቀሳቃሽ ፍጥረቶች ሁሉ ምግብ እንዲሆኑአችሁ ሰጥቻችኋለሁ። ነገር ግን በደሙ ውስጥ ሕይወት ስላለ ደም ያለበትን ሥጋ አትብሉ። ነፍሳችሁ ያለችበትን ደማችሁን በእርግጥ በተጠያቂነት ላይ እሻዋለሁ፤ ከእንስሶች ሁሉና ከሰውም ላይ እሻዋለሁ፤ ከሰው ሁሉ የሰውን ሕይወት እሻዋለሁ። ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሔር አምሳያ ስለ ሆነ፥ ሰውን የሚገድል ሁሉ በሰው እጅ ይሞታል። “እናንተ ፍሬያማ ሆናችሁ ተባዙ፤ ዘራችሁ በምድር ላይ ይብዛ።” ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ለኖኅና ለልጆቹ እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፥ ከእናንተና ከዘራችሁ ጋር ቃል ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤ እንዲሁም ሕይወት ካላቸው ፍጥረቶች ሁሉ፥ ማለትም ከወፎች፥ ከእንስሶችና ከአራዊት፥ ከአንተ ጋር ከመርከቡ ውስጥ ከወጡት ፍጥረቶችና ዘሮቻቸው ሁሉ ጋር ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ በዚህም በገባሁላችሁ ቃል ኪዳን መሠረት፥ ከእንግዲህ ወዲህ ሕያዋን ፍጥረቶች ሁሉ በጥፋት ውሃ ከቶ አይደመሰሱም፤ ምድርም ዳግመኛ በጥፋት ውሃ አትጠፋም።” እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፦ “ከእናንተና ከሕያዋን ፍጥረቶች ሁሉ ጋር ለምገባው ለዚህ ለዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን ምልክት ይሆን ዘንድ፥ ቀስቴን በደመናዎች ላይ አደርጋለሁ፤ ይህም ቀስት ከምድር ጋር ለገባሁት ቃል ኪዳን ምልክት ሆኖ ይኖራል። ሰማይን በደመና በምሸፍንበትና ቀስትም በደመና ላይ በሚታይበት ጊዜ ሁሉ፥ ‘ከእንግዲህ ወዲህ የጥፋት ውሃ፤ ሕያዋን ፍጥረቶችን ሁሉ ከቶ አያጠፋም’ ብዬ ከእናንተና ከሌሎች ሕያዋን ፍጥረቶች ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አስታውሳለሁ። ቀስት በደመናዎች ላይ በሚታይበት ጊዜ ተመልክቼ በእኔና በምድር ላይ ባሉት ሕይወት ባላቸው ፍጥረቶች መካከል ያለውን ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን አስታውሳለሁ።” እግዚአብሔርም ኖኅን እንዲህ አለው፦ “ይህ ቀስት በምድር ላይ በእኔና ሕይወት ባላቸው ፍጥረቶች ሁሉ መካከል የገባሁትን ቃል ኪዳን የሚያስታውስ ምልክት ነው።”
ኦሪት ዘፍጥረት 9 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 9:1-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos