የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፍጥረት 42:1-24

ኦሪት ዘፍጥረት 42:1-24 አማ05

ያዕቆብ በግብጽ እህል መኖሩን በሰማ ጊዜ ልጆቹን “እርስ በርሳችሁ እየተያያችሁ የምትቀመጡት ለምንድን ነው? በግብጽ አገር እህል መኖሩን ሰምቼአለሁ፤ በራብ እንዳንሞት ወደዚያ ሂዱና እህል ሸምቱልን” አላቸው። ስለዚህ ዐሥሩ የዮሴፍ ወንድሞች እህል ለመሸመት ወደ ግብጽ ሄዱ፤ ነገር ግን “ጒዳት ይደርስበታል” ብሎ ስለ ፈራ ያዕቆብ ከዮሴፍ ጋር ከአንድ እናት የወለደውን ልጁን ብንያምን ከወንድሞቹ ጋር ወደ ግብጽ አላከውም፤ በከነዓን ምድርም ራብ ገብቶ ስለ ነበር የያዕቆብ ልጆች ከሌሎች ሰዎች ጋር እህል ለመሸመት ወደ ግብጽ ሄዱ። ዮሴፍ የግብጽ ምድር አስተዳዳሪ በመሆኑ ከዓለም ዙሪያ ለሚመጡ ሰዎች ሁሉ እህል እንዲሸጥላቸው ያደርግ ነበር፤ ስለዚህ የዮሴፍ ወንድሞች ወደ እርሱ መጡና ግንባራቸው መሬት እስኪነካ ዝቅ ብለው እጅ ነሡት። ዮሴፍ ወንድሞቹን ባያቸው ጊዜ ዐወቃቸው፤ ነገር ግን የማያውቃቸው በመምሰል በቊጣ ቃል “ከየት ነው የመጣችሁት?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም “እህል ለመሸመት ከከነዓን አገር መጣን” አሉት። ዮሴፍ ወንድሞቹን ያወቃቸው ቢሆንም እንኳ እነርሱ አላወቁትም ነበር፤ ስለ እነርሱ ያየው ሕልም ሁሉ ትዝ አለውና “እናንተ ሰላዮች ናችሁ፤ የመጣችሁትም የአገራችንን ደካማነት እምን ላይ እንደ ሆነ ለመሰለል ነው” አላቸው። እነርሱም “ጌታችን ሆይ፥ እኛ ሰላዮች አይደለንም፤ እኛ አገልጋዮችህ እዚህ የመጣነው እህል ለመግዛት ነው” አሉት። “እኛ ሁላችን የአንድ ሰው ልጆች ነን፤ እኛ የምንታመን ነን፤ ሰላዮችም አይደለንም” አሉት። ዮሴፍም “አይደለም! እናንተ የመጣችሁት የአገራችንን ደካማነት በምን በኩል እንደ ሆነ ለመሰለል ነው” አላቸው። እነርሱም “እኛ አገልጋዮችህ በከነዓን ምድር የሚኖር የአንድ ሰው ልጆች የሆንን ዐሥራ ሁለት ወንድማማቾች ነን፤ አንዱ ወንድማችን ሞቶአል፤ የመጨረሻ ታናሽ ወንድማችን አሁን ከአባታችን ጋር ይገኛል” አሉት። ዮሴፍም እንዲህ አላቸው “ይኸው እኔ እንዳልኩት ያለ ጥርጥር ሰላዮች ናችሁ፤ እንግዲህ ታማኝነታችሁ ተፈትኖ የሚረጋገጠው በዚህ ነው፤ ታናሽ ወንድማችሁ እስከሚመጣ ድረስ እንደማልለቃችሁ በንጉሡ በፈርዖን ስም እምላለሁ። ከእናንተ አንዱ ሄዶ ወንድማችሁን ያምጣ፤ የተናገራችሁት እውነት መሆኑ ተረጋግጦ ነጻ እስክትለቀቁ ድረስ የቀራችሁት እዚሁ በእስር ቤት ትቈያላችሁ አለበለዚያ ግን በፈርዖን ስም እምላለሁ፤ እናንተ ሰላዮች ናችሁ።” ከዚህ በኋላ ሦስት ቀን አስሮ አቈያቸው። በሦስተኛው ቀን ዮሴፍ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ እግዚአብሔርን የምፈራ ሰው ስለ ሆንኩ እንዲህ ብታደርጉ ሕይወታችሁን ታድናላችሁ፤ እናንተ ታማኞች ሰዎች ከሆናችሁ ከእናንተ አንዱ እዚሁ በእስር ቤት ይቈይ፤ የቀራችሁት እህሉን ይዛችሁ ወደ ተራቡት ዘመዶቻችሁ ሂዱ። ከዚህ በኋላ ታናሽ ወንድማችሁን ይዛችሁልኝ ኑ፤ በዚህ ዐይነት የተናገራችሁት ሁሉ እውነት መሆኑ ይረጋገጣል፤ ከመሞትም ትድናላችሁ።” እነርሱም በዚህ ነገር ተስማሙ፤ እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ “በእርግጥ በወንድማችን ላይ ስላደረስነው በደል ተገቢውን ቅጣት በመቀበል ላይ ነን፤ ምሕረት እንድናደርግለት ተጨንቆ ሲለምነን ልመናውን አልተቀበልንም ነበር፤ በእኛም ላይ ይህ ጭንቀት ሊደርስብን የቻለው በዚህ ምክንያት ነው።” ሮቤልም “እኔ በልጁ ላይ ጒዳት እንዳታደርሱ ነግሬአችሁ ነበር፤ ነገር ግን አልሰማችሁኝም፤ እነሆ፥ እርሱን በመግደላችን በቀሉን እየተቀበልን ነው” አላቸው። ዮሴፍ እነርሱ የሚሉትን ሁሉ ያዳምጥ ነበር፤ እነርሱ ግን ከዮሴፍ ጋር የሚነጋገሩት በአስተርጓሚ ስለ ነበር የእነርሱን ንግግር ዮሴፍ እንደሚሰማቸው አላወቁም። ዮሴፍ ከእነርሱ ነጠል ብሎ አለቀሰ፤ እንደገናም ወደ እነርሱ ተመልሶ አነጋገራቸውና ስምዖንን ከመካከላቸው ወስዶ በፊታቸው አሰረው።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}