ስለዚህ ፈርዖን ዮሴፍን እንዲያመጡት አዘዘ፤ ወዲያውኑ ከእስር ቤት ይዘውት መጡ፤ ጠጒሩን ተላጭቶ ልብሱን ከለወጠ በኋላ ወደ ንጉሡ ፊት ቀረበ። ንጉሡም ዮሴፍን “ሕልም አይቼ ነበር፤ ነገር ግን ማንም ሊተረጒመው አልቻለም፤ አንተ ሕልም የመተርጐም ችሎታ እንዳለህ ሰምቼአለሁ” አለው። ዮሴፍም “ንጉሥ ሆይ፥ እኔ ሕልም የመተርጐም ችሎታ የለኝም፤ ትክክለኛውን ትርጒም ሊሰጥህ የሚችል እግዚአብሔር ነው” አለ። ንጉሡም እንዲህ አለ፤ “በሕልሜ በዓባይ ወንዝ ዳር ቆሜ ነበር፤ ሰባት የወፈሩና የሰቡ ላሞች ከወንዙ ወጥተው ሣር ሲበሉ አየሁ፤ ቀጥሎም አጥንቶቻቸው እስከሚታይ ድረስ የከሱ ሌሎች ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጡ፤ እንደ እነርሱ የሚያስከፉ ላሞች በግብጽ ምድር ከቶ አይቼ አላውቅም። የከሱትና አስከፊ የሆኑት ላሞች በመጀመሪያ የወጡትን ሰባት የወፈሩ ላሞች ዋጡአቸው። ከዋጡአቸውም በኋላ እንደ ቀድሞው የከሱ ስለ ነበሩ፥ እንደ ዋጡአቸው ማንም ሊያውቅ አይችልም ነበር፤ በዚህ ጊዜ እኔ ከእንቅልፌ ነቃሁ። ደግሞም በሕልሜ በአንድ የእህል አገዳ ላይ ሰባት የዳበሩና ያማሩ የእሸት ዛላዎች አየሁ፤ ቀጥሎም የቀጨጩና በበረሓ ነፋስ ተመተው የሰለቱ ሰባት የእሸት ዛላዎች ታዩ። የቀጨጩትም ዛላዎች የሚያምሩትን ዛላዎች ዋጡአቸው፤ ያየኋቸውንም ሕልሞች ለአስማተኞች ነገርኩ፤ ነገር ግን ሕልሞቹን ማንም ሊተረጒምልኝ አልቻለም።” ዮሴፍም ፈርዖንን እንዲህ አለው፤ “የሁለቱም ሕልሞችህ ትርጒም አንድ ነው፤ እግዚአብሔር ወደ ፊት የሚያደርገውን ነገር አስቀድሞ ገልጦልሃል፤ ሰባቱ የሚያምሩ ላሞች ሰባት ዓመቶች ናቸው፤ ሰባቱም ያማሩ የእሸት ዛላዎች ሰባት ዓመቶች ናቸው፤ የሁለቱም ትርጒም አንድ ነው። ከእነርሱም በኋላ የወጡት ሰባት የከሱትና አስከፊዎቹ ላሞች ሰባት ዓመቶች ናቸው፤ እንዲሁም ሰባቱ የቀጨጩና በበረሓ ነፋስ ተመተው የሰለቱ የእሸት ዛላዎች ሰባት ዓመቶች ናቸው፤ የሁለቱም ትርጒም አንድ ነው፤ ይኸውም ሰባት የራብ ዓመቶች ናቸው። ልክ እንደ ነገርኩህ ነው፤ እግዚአብሔር ወደ ፊት የሚያደርገውን ነገር አስቀድሞ ገልጦልሃል፤ በመላው የግብጽ ምድር ላይ ታላቅ ጥጋብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመቶች ይመጣሉ። ከዚያ በኋላ ሰባት የራብ ዓመቶች ይመጣሉ፤ ራብ አገሪቱን በብርቱ ስለሚጐዳት እነዚያ የጥጋብ ዓመቶች ይረሳሉ። ተከታዩ የራብ ዘመን እጅግ አሠቃቂ ስለሚሆን የጥጋብ ጊዜ ፈጽሞ እንዳልነበረ ይሆናል። ሕልሙን ደጋግመህ ማየትህ የሚያመለክተው፥ ነገሩ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወሰነና በቅርብ ጊዜም ውስጥ የሚፈጸም መሆኑን ነው። “እንግዲህ ጥበብና ማስተዋል ያለውን ሰው መርጠህ በአገሪቱ አስተዳዳሪ አድርገህ ሹመው፤ በሰባቱ የጥጋብ ዓመቶች አንድ አምስተኛውን ሰብል የሚሰበስቡ ሰዎችን መርጠህ ሹም። እነርሱ በሚመጡት የጥጋብ ዓመቶች ትርፍ የሆነውን ሰብል ሁሉ እንዲሰበስቡ እዘዛቸው፤ በየከተማውም እህል በጐተራ እንዲያከማቹና እንዲጠብቁት ሥልጣን ስጣቸው። ይህም የሚከማቸው እህል በግብጽ ምድር ላይ ወደፊት በሚመጡት ሰባት የራብ ዓመቶች ለአገሪቱ መጠባበቂያ ይሆናል፤ በዚህ ሁኔታ አገሪቱ በራብ ከመጐዳት ትድናለች።”
ኦሪት ዘፍጥረት 41 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 41:14-36
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች