ኦሪት ዘፍጥረት 31
31
ያዕቆብ ከላባ ተሰውሮ መሄዱ
1የላባ ወንዶች ልጆች “ያዕቆብ የአባታችንን ሀብት ወሰደ፤ ይህን ሁሉ ሀብት ያገኘው ከአባታችን ነው” እያሉ መናገራቸውን ያዕቆብ ሰማ። 2በላባም ዘንድ እንደ ቀድሞው ተወዳጅ አለመሆኑን ተረዳ። 3በዚህን ጊዜ እግዚአብሔር ያዕቆብን “ወደ አባቶችህና ወደ ዘመዶችህ አገር ተመለስ፤ እኔም ከአንተ ጋር እሆናለሁ” አለው።
4ስለዚህ ያዕቆብ መንጋዎቹ ወደ ተሰማሩበት መስክ እንዲመጡ ራሔልንና ልያን አስጠራቸው፤ 5እንዲህም አላቸው፤ “አባታችሁ እንደ ቀድሞው ጊዜ እንደማይወደኝ ተረድቼአለሁ፤ ነገር ግን የአባቴ አምላክ ከእኔ ጋር አለ፤ 6ጒልበቴን ሳልቈጥብ በትጋት አባታችሁን እንዳገለገልኩ እናንተም ታውቃላችሁ፤ 7እርሱ ግን ዐሥር ጊዜ ደመወዜን በመለዋወጥ አታለለኝ፤ ሆኖም እኔን ለመጒዳት እግዚአብሔር አልፈቀደለትም፤ 8ላባ ‘ዝንጒርጒሮቹ ሁሉ ለአንተ ደመወዝ ይሁኑ’ ባለኝ ጊዜ፥ መንጋዎቹ ሁሉ ዝንጒርጒር ወለዱ፤ ደግሞም ‘ሽመልመሌ መሳዮቹ ሁሉ ለአንተ ደመወዝ ይሁኑ’ ባለኝ ጊዜ፥ መንጋዎቹ ሁሉ ሽመልመሌ መሳዮች ወለዱ። 9እግዚአብሔር የአባታችሁን የላባን መንጋዎች ወስዶ ለእኔ የሰጠኝ በዚህ ዐይነት ነው።
10“እንስሶቹ ለመፅነስ ፍትወት በሚያድርባቸው ወራት የሚያጠቁአቸው አውራ ፍየሎች ሽመልመሌ፥ ዝንጒርጒርና ነቊጣ መሆናቸውን በሕልም አየሁ። 11በዚያው ሕልም የእግዚአብሔር መልአክ ‘ያዕቆብ!’ ብሎ ጠራኝ፤ እኔም ‘እነሆ፥ አለሁ!’ አልኩ። 12እርሱም እንዲህ አለኝ፤ ‘መንጋዎቹን የሚያጠቁአቸው አውራ ፍየሎች ሽመልመሌ፥ ዝንጒርጒርና ነቊጣ ያለባቸው መሆናቸውን ተመልከት፤ ላባ የፈጸመብህን በደል ስላየሁ ይህን ያደረግኹት እኔ ነኝ፤ 13የመታሰቢያ ድንጋይ አቁመህ ዘይት በመቀባት በተሳልክበት ቦታ በቤትኤል የተገለጥኩልህ አምላክህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤ አሁንም ከዚህ አገር በፍጥነት ወጥተህ ወደ ተወለድክበት አገር ተመለስ።’ ” #ዘፍ. 28፥18-22።
14ራሔልና ልያ ለያዕቆብ እንዲህ ሲሉ መለሱለት፦ “በአባታችን ቤት የውርስ ድርሻ ቀርቶልናልን? 15እርሱ እኛን የሚያየን እንደ ባዕድ አይደለምን? አስቀድሞ ሸጦን ነበር፤ አሁን ደግሞ ለእኛ ዋጋ የተከፈለውን ሁሉ አጥፍቶታል፤ 16አሁንም እግዚአብሔር ከአባታችን ወስዶ ለአንተ የሰጠህ ሀብት ሁሉ የእኛና የልጆቻችን ነው፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ያዘዘህን ሁሉ አድርግ።”
17ያዕቆብም ተነሥቶ ልጆቹንና ሚስቶቹን በግመሎች ላይ አስቀመጠ፤ 18በመስጴጦምያ ሳለ ያገኛቸውን መንጋዎችና ዕቃዎችን ሁሉ ይዞ ወደ ከነዓን ምድር ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ሄደ። 19ላባ በጎች ሊሸልት ሄዶ ስለ ነበር፥ እርሱ በሌለበት ራሔል በቤት የነበሩትን የአባቷን ጣዖቶች ሰርቃ ሄደች። 20ያዕቆብ መሄዱን ለላባ ሳይገልጥለት አታሎት ሄደ፤ 21የራሱ የሆነውን ሀብት ይዞ በፍጥነት ተጓዘ፤ የኤፍራጥስንም ወንዝ ተሻግሮ ወደ ኮረብታማው አገር ወደ ገለዓድ ሄደ።
ያዕቆብ በጒዞ ላይ ሳለ ላባ መከታተሉ
22ያዕቆብ በስውር መሄዱን ላባ ከሦስት ቀን በኋላ ሰማ፤ 23ከዘመዶቹ ጋር ሆኖ ያዕቆብን ተከታተለው፤ ሰባት ቀን ከተጓዘ በኋላ ገለዓድ በተባለው ተራራማ አገር ላይ ሊደርስበት ተቃረበ። 24በዚያን ሌሊት እግዚአብሔር ለላባ በሕልም ተገለጠለትና “ያዕቆብን፥ ክፉም ሆነ ደግ እንዳትናገረው ተጠንቀቅ” አለው። 25ያዕቆብ ገለዓድ በተባለው ኮረብታማ ስፍራ ድንኳኑን በመትከል ሰፍሮ ሳለ ላባ ደረሰበት፤ ላባና ዘመዶቹም እዚያው ድንኳናቸውን ተክለው ሰፈሩ።
26ከዚህ በኋላ ላባ ያዕቆብን እንዲህ አለው፤ “ስለምን እንዲህ አድርገህ አታለልከኝ? ሴቶች ልጆቼንስ በጦርነት እንደ ተማረኩ ያኽል ይዘሃቸው ለምን ሄድክ? 27ሳትነግረኝ ተሰውረህ በመሄድ ለምን አታለልከኝ? ነግረኸኝ ቢሆን ኖሮ በከበሮና በመሰንቆ እየተዘፈነ በደስታ በሸኘሁህ ነበር። 28ልጆቼንና የልጅ ልጆቼን በመሳም እንድሰናበታቸው አላደረግህም፤ ይህ ያደረግኸው ነገር ስሕተት ነው። 29ጒዳት ላደርስብህ እችል ነበር፤ ነገር ግን ባለፈው ሌሊት የአባትህ አምላክ ‘ያዕቆብን፥ ክፉም ሆነ ደግ አንድ ቃል እንዳትናገረው’ ብሎ አስጠነቀቀኝ፤ 30ወደ ትውልድ አገርህ ለመመለስ ባለህ ብርቱ ፍላጎት እንደ ተለየኸኝ ዐውቃለሁ፤ ታዲያ የቤቴን ጣዖቶች የሰረቅህብኝ ለምንድን ነው?”
31ያዕቆብም “ሴቶች ልጆችህን ነጥቀህ ትወስድብኛለህ ብዬ ስለ ፈራሁ ነው፤ 32ከእኛ መካከል የአንተ ጣዖቶች የተገኙበት ሰው ቢኖር ግን ይሙት፤ እነሆ፥ አሁን ዘመዶቻችንን ምስክር በማድረግ የአንተ የሆነውን ነገር ሁሉ ፈልገህ ውሰድ” አለው፤ ያዕቆብ ይህን ያለው ራሔል የአባቷን ጣዖቶች ሰርቃ እንደ ወሰደች ስላላወቀ ነው።
33ከዚህ በኋላ ላባ ወደ ያዕቆብ ወደ ልያና ወደ ሁለቱ አገልጋዮች ድንኳን ተራ በተራ ገብቶ በረበረ፤ ነገር ግን ምንም አላገኘም፤ በመጨረሻ ወደ ራሔል ድንኳን ገባ፤ 34ራሔል ግን ጣዖቶቹን ወስዳ በግመሉ ኮርቻ ሥር በመሰወር በላያቸው ላይ ተቀምጣባቸው ነበር፤ ላባ በድንኳኑ ውስጥ ያለውን ጓዝ ሁሉ በርብሮ ምንም ነገር አላገኘም። 35ራሔልም አባቷን “ጌታዬ በወር አበባዬ ምክንያት መነሣት ስላልቻልኩ ቅር አትሰኝብኝም” አለችው። ላባ በሁሉ ስፍራ ፈልጎ ጣዖቶቹን ማግኘት አልቻለም።
36በዚህ ጊዜ ያዕቆብ እንዲህ ሲል ላባን በቊጣ ቃል ተናገረው፤ “ታዲያ፥ የፈጸምኩት በደል ምንድን ነው? እስቲ ምን አጥፍቼ ነው እንዲህ የምታሳድደኝ? 37ዕቃዬን ሁሉ ከበረበርክ በኋላ የአንተ የሆነ ነገር ምን አግኝተሃል? አንዳች ነገር አግኝተህ ቢሆን በአንተና በእኔ ዘመዶች ፊት እዚህ አቅርበው፤ እነርሱም ከአንተና ከእኔ አጥፊው ማን እንደሆን ይፍረዱ። 38ከአንተ ጋር መኖር ከጀመርኩ ኻያ ዓመት ሆነኝ፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ በጎችህና ፍየሎችህ የጨነገፉበት ጊዜ የለም፤ ከመንጋህም አንድ ጠቦት እንኳ በልቼ አላውቅም፤ 39ከበጎችህ አንዱን አውሬ ሲበላው ወዲያው እከፍልህ ነበር እንጂ የእኔ ስሕተት ያለመሆኑን ለማስረዳት ወደ አንተ አምጥቼው አላውቅም፤ በቀንም ቢሆን በሌሊት የተሰረቀ እንስሳ ቢኖር ታስከፍለኝ ነበር። 40ብዙ ጊዜ በቀን ሐሩርና በሌሊት ቅዝቃዜ እሠቃይ ነበር፤ በቂ እንቅልፍ ያገኘሁበት ጊዜ አልነበረም። 41ከአንተ ጋር የነበርኩበትን ኻያ ዓመት ያሳለፍኩት በዚህ ሁኔታ ነበር፤ ከዚህም ዐሥራ አራቱን ዓመት ያገለገልኩህ ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ለማግኘት ብዬ ነው፤ የቀሩትን ስድስት ዓመቶች ያገለገልኩህ መንጋዎችህን ለማግኘት ብዬ ነው። ይህም ሆኖ ደመወዜን ዐሥር ጊዜ ለዋወጥክብኝ። 42አባቴ ይስሐቅ የሚያመልከው የአብርሃም አምላክ ከእኔ ጋር ባይሆን ኖሮ ባዶ እጄን በሰደድከኝ ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር መከራዬንና ልፋቴን አይቶ ባለፈው ሌሊት ገሥጾሃል።”
በያዕቆብና በላባ መካከል የተደረገ ስምምነት
43ላባም ያዕቆብን እንዲህ አለው፦ “እነዚህ ሴቶች የእኔ ልጆች ናቸው፤ ልጆቻቸውም የእኔው ናቸው፤ እነዚህም መንጋዎች የእኔ ናቸው፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ የምታየው ሁሉ የራሴ ነው፤ ነገር ግን ልጆቼንም ሆነ ልጆቻቸውን ለማስቀረት ምንም ማድረግ አልቻልኩም፤ 44ስለዚህ እኔና አንተ በመሐላ የስምምነት ውል እናድርግ፤ ለምናደርገው ውል ምስክር ሆኖ እንዲኖር ድንጋይ ሰብስበን በመከመር ሐውልት እናቁም።”
45ስለዚህ ያዕቆብ ትልቅ ድንጋይ አንሥቶ የመታሰቢያ ሐውልት እንዲሆን አቆመው። 46ቤተሰቡንም ሁሉ “ድንጋይ ሰብስቡ” አላቸው፤ ድንጋይ ሰብስበው ከቈለሉ በኋላም በአጠገቡ ተቀምጠው ምግብ ተመገቡ። 47ላባም ይጋርሣሀዱታ ብሎ ጠራት፤ ያዕቆብም ገለዓድ ብሎ ሰየማት። #31፥47 ይጋርሣሀዱታ፦ በሶርያ ቋንቋ “የምስክር ካብ” ወይም “ሐውልት” ማለት ነው። 48ላባም “እነሆ፥ ዛሬ ይህ የድንጋይ ካብ በእኔና በአንተ መካከል ምስክር ነው” አለ። ገለዓድ ተብላ የተጠራችበት ምክንያት ለዚህ ነው። #31፥48 ገለዓድ፦ በዕብራይስጥ “የምስክር ካብ” ወይም “ሐውልት” ማለት ነው። 49ላባም “እንግዲህ ከዚህ በምንለያይበት ጊዜ እግዚአብሔር እኔንና አንተን ይጠብቀን” በማለት ያንኑ ስፍራ ምጽጳ ብሎ ጠራው። #31፥49 ምጽጳ፦ በዕብራይስጥ “መጠበቂያ” ማለት ነው። 50ላባም ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “ልጆቼን ብታጒላላቸው ወይም ሌሎችን ሴቶች በላያቸው ብታገባ ምንም እንኳ እኔ ላውቅ ባልችል እግዚአብሔር ምስክራችን መሆኑን አትርሳ። 51በመካከላችን የቈለልኩት ድንጋይና ያቆምኩት ሐውልት እነሆ፥ 52እኔ አንተን ለማጥቃት ይህን የድንጋይ ቊልል እንደማላልፍ፥ አንተም እኔን ለማጥቃት ይህን የድንጋይ ቊልልና ይህን የመታሰቢያ ሐውልት እንደማታልፍ፥ ይህ የድንጋይ ቊልልና ይህ የመታሰቢያ ሐውልት ምስክሮች ናቸው። 53ይህንን ሳናደርግ ብንቀር ግን ከአብርሃም አምላክ፥ ከናኮር አምላክና ከአባታቸውም አምላክ ቅጣት ይድረስብን።” ከዚህ በኋላ ያዕቆብ አባቱ ይስሐቅ በሚያመልከው አምላክ ስም ይህን ቃል ለመጠበቅ ማለ። 54በተራራውም ላይ ያዕቆብ መሥዋዕት አቀረበ፤ ሰዎቹን ሁሉ ጠርቶም ምግብ እንዲመገቡ አደረገ፤ ከበሉም በኋላ ሌሊቱን በዚያ አሳለፉ። 55በማግስቱ ላባ ጥዋት በማለዳ ተነሥቶ ልጆቹንና የልጅ ልጆቹን በመሳምና በመመረቅ ተሰናበታቸው፤ ከዚያም ተነሥቶ ወደ ቤቱ ተመለሰ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 31: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997