ኦሪት ዘፍጥረት 27
27
ይስሐቅ ያዕቆብን መረቀው
1ይስሐቅ አርጅቶ ዐይኖቹም ፈዘው ነበር፤ ታላቁን ልጁን ዔሳውን “ልጄ ሆይ!” ብሎ ጠራው፤ ልጁም “እነሆ፥ አለሁ!” አለ።
2ይስሐቅም እንዲህ አለው፤ “እንደምታየኝ አርጅቼአለሁ፤ የምሞትበትንም ቀን አላውቅም፤ 3ስለዚህ የምታድንበትን ቀስትና ፍላጻ ያዝ፤ ወደ ዱር ሂድና አውሬ አድነህ ሥጋ አምጣልኝ፤ 4ልክ እንደምወደው አድርገህ የጣፈጠ ምግብ ሠርተህ አምጣልኝ፤ ከበላሁም በኋላ ከመሞቴ በፊት የመጨረሻ ምርቃቴን እሰጥሃለሁ።”
5ይስሐቅ ለልጁ ለዔሳው የሚለውን ሁሉ ርብቃ ትሰማ ነበር፤ ስለዚህ ዔሳው ወደ አደን ከሄደ በኋላ፥ 6ርብቃ ልጅዋን ያዕቆብን “አባትህ ወንድምህን ዔሳውን እንዲህ ሲለው ሰማሁ፤ 7‘አውሬ አድነህ ሥጋ አምጣልኝ፤ ልክ እንደምወደው አድርገህ የጣፈጠ ምግብ ሥራልኝ፤ ሳልሞትም በእግዚአብሔር ፊት እመርቅሃለሁ፤’ 8አሁንም ልጄ ሆይ፥ የምነግርህን አድምጥ፤ የማዝህንም አድርግ፤ 9አባትህ እንደሚወደው አጣፍጬ ጥሩ ምግብ እንድሠራለት፥ ወደ መንጋዎች ሂድና ሁለት የሰቡ የፍየል ጠቦቶችን አምጣልኝ፥ 10አንተም ያዘጋጀሁትን ምግብ እንዲበላ ለአባትህ ወስደህ ታቀርብለታለህ፤ በዚህ ዐይነት አባትህ ከመሞቱ በፊት ይመርቅሃል።”
11ያዕቆብ ግን እናቱን ርብቃን “የወንድሜ የዔሳው ገላ ጠጒራም ነው፤ የእኔ ገላ ግን ምንም ጠጒር የሌለው ለስላሳ ነው፤ 12ምናልባት አባቴ ቢዳስሰኝና እንዳታለልኩት ቢያውቅ በምርቃት ፈንታ ርግማን እንደማተርፍ ታውቂ የለምን?” አላት።
13እናቱም “ልጄ ሆይ፥ የአንተ ርግማን በእኔ ላይ ይሁን፤ አሁንም እንደ ነገርኩህ አድርግ፤ ሄደህ ጠቦቶቹን አምጣልኝ” አለችው።
14ስለዚህ ሄዶ ጠቦቶቹን አመጣላት፤ እርስዋም ልክ አባቱ እንደሚወደው አድርጋ ጥሩ ወጥ ሠራች፤ 15የታላቁ ልጅዋን የዔሳውን የክት ልብስ ከተቀመጠበት ቦታ አውጥታ ለያዕቆብ አለበሰችው። 16የፍየሎቹንም ቆዳ በክንዶቹ ላይና ጠጒር በሌለበት በአንገቱ ላይ አለበሰችው። 17ያዘጋጀችውንም ጥሩ ወጥ ከጋገረችው እንጀራ ጋር ለልጅዋ ለያዕቆብ ሰጠችው።
18ያዕቆብም ወደ አባቱ ሄደና “አባባ!” አለው፤
እርሱም “እነሆ፥ አለሁ! ለመሆኑ አንተ የትኛው ልጄ ነህ?” አለ።
19ያዕቆብም “የበኲር ልጅህ ዔሳው ነኝ፤ እነሆ፥ እንዳዘዝከኝ አድርጌአለሁ፤ እንድትመርቀኝ እስቲ ቀና በልና ያመጣሁልህን የአደን ሥጋ ተመገብ” አለው።
20ይስሐቅም “ልጄ ሆይ፥ እንዴት በቶሎ ልታገኝ ቻልክ?” አለው።
ያዕቆብም “አምላክህ እግዚአብሔር ስለ ረዳኝ በቶሎ ለማግኘት ቻልኩ” አለው።
21ይስሐቅም “እስቲ ወደ እኔ ቀረብ በልና ልዳብስህ፤ በእርግጥ አንተ ዔሳው ነህን?” አለው። 22ያዕቆብም ወደ አባቱ ተጠጋ፤ አባቱም ዳሰሰውና “ድምፅህ የያዕቆብን ድምፅ ይመስላል፤ ክንድህ ግን የዔሳውን ክንድ ይመስላል” አለው። 23ክንዶቹ እንደ ዔሳው ክንዶች ጠጒራም ስለ ነበሩ ይስሐቅ ያዕቆብን ለይቶ ማወቅ አልቻለም፤ ሊመርቀው ከተዘጋጀ በኋላ፥ 24“በእርግጥ አንተ ልጄ ዔሳው ነህን?” ሲል እንደገና ጠየቀው፤ እርሱም “አዎ፥ ነኝ” አለ።
25ይስሐቅም “ልጄ በል ከአደንከው ሥጋ አቅርብልኝ፤ ከበላሁም በኋላ እመርቅሃለሁ” አለው።
ያዕቆብም ምግቡን አቀረበለት፤ የወይን ጠጅም እንዲጠጣ አመጣለት። 26ከዚህ በኋላ አባቱ ይስሐቅ “ልጄ ሆይ፥ ቀረብ በልና ሳመኝ” አለው፤ 27ያዕቆብም ቀርቦ ሳመው። ይስሐቅ የያዕቆብን ልብስ ባሸተተ ጊዜ እንዲህ ሲል መረቀው፥
“እነሆ የልጄ መልካም ሽታ፥
እግዚአብሔር እንደ ባረከው የእርሻ ሽታ ነው፤ #ዕብ. 11፥20።
28እግዚአብሔር ከሰማይ የሚያረሰርስ ጠል ይስጥህ!
ምድርህን ያለምልምልህ!
እህልህንና ወይንህን ያብዛልህ!
29መንግሥታት ይገዙልህ፤ ሕዝቦችም ያገልግሉህ፤
በወንድሞችህ ሁሉ ላይ አለቃ ሁን፤
የእናትህም ልጆች ይስገዱልህ፤
የሚረግሙህ የተረገሙ ይሁኑ፤
የሚመርቁህም የተመረቁ ይሁኑ።” #ዘፍ. 12፥3።
ዔሳው የይስሐቅን በረከት መለመኑ
30ይስሐቅ ያዕቆብን መርቆ እንዳበቃና ያዕቆብም ከአባቱ ፊት እንደ ወጣ ወዲያው ወንድሙ ዔሳው ከአደን ተመልሶ መጣ። 31እርሱም በበኩሉ የጣፈጠ ወጥ ሠርቶ ለአባቱ አቀረበለትና “አባቴ ሆይ፥ እንድትመርቀኝ፥ እስቲ ቀና ብለህ ካመጣሁልህ የአደን ሥጋ ብላ” አለው።
32ይስሐቅም “አንተ ማን ነህ?” አለው።
እርሱም “እኔ የበኲር ልጅህ ዔሳው ነኝ” አለ።
33ይስሐቅም እጅግ ደንግጦ እየተንቀጠቀጠ “ታዲያ፥ አውሬ አድኖ ያመጣልኝ ማን ነበር? ልክ አንተ ከመምጣትህ በፊት ተመገብኩ፤ የመጨረሻ ምርቃቴንም ሰጠሁት፤ ምርቃቱም የእርሱ ሆኖ ይኖራል” አለው።
34ዔሳው ይህን በሰማ ጊዜ ድምፁን ከፍ በማድረግ ምርር ብሎ እያለቀሰ “አባቴ ሆይ! እኔንም መርቀኝ!” አለ።
35ይስሐቅም “ወንድምህ መጥቶ እኔን በማታለል የአንተን ምርቃት ወስዶብሃል” አለው።
36ዔሳውም “እርሱ እኔን ሲያሰናክለኝ ይህ ሁለተኛው ነው፤ ያዕቆብ መባሉ ተገቢ ነው፤ ከዚህ በፊት ብኲርናዬን ወሰደብኝ፤ አሁን ደግሞ ምርቃቴን ቀማኝ፤ ታዲያ፥ ለእኔ ያስቀረኸው ምንም ምርቃት የለምን?” አለው። #ዘፍ. 25፥29-34።
37ይስሐቅም “ቀደም ብዬ እርሱን የአንተ ጌታ አድርጌዋለሁ፤ ወንድሞቹ ሁሉ የእርሱ አገልጋዮች እንዲሆኑ አድርጌአለሁ፤ እህልና የወይን ጠጅ እንዲበዛለት አድርጌአለሁ፤ ልጄ ሆይ! እንግዲህ ለአንተ ምን ላደርግልህ እችላለሁ?” አለው።
38ዔሳውም “አባቴ ሆይ! ምርቃትህ አንዲት ብቻ ናትን? እባክህ እኔንም መርቀኝ” እያለ ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ። #ዕብ. 12፥17።
39ይስሐቅም እንዲህ አለው፤
“በረከት ከሞላበት ለምለም ምድር ርቀህ ትኖራለህ፤
የሰማይ ጠልም አታገኝም፤ #ዕብ. 11፥20።
40በሰይፍህ ኀይል ትኖራለህ፤
የወንድምህም አገልጋይ ትሆናለህ፤
በተቃወምከው ጊዜ ግን ከእርሱ ጭቈና ትላቀቃለህ።” #ዘፍ. 36፥8፤ 2ነገ. 8፥20።
41አባቱ ስለ መረቀው ዔሳው ያዕቆብን አጥብቆ ጠላው፤ በልቡም “አባቴ በቅርብ ቀን ይሞታል፤ ከዚያ በኋላ ወንድሜን ያዕቆብን እገድለዋለሁ” ብሎ አሰበ።
42ነገር ግን ርብቃ የዔሳውን ዕቅድ ስለ ሰማች፥ ያዕቆብን ጠርታ እንዲህ አለችው፤ “አድምጠኝ፤ ወንድምህ ዔሳው አንተን በመግደል ሊበቀልህ አስቦአል፤ 43አሁንም ልጄ ሆይ፥ የምልህን አድርግ፤ ተነሥተህ በካራን ወደሚኖረው ወደ ወንድሜ ወደ ላባ ሽሽ፤ 44የወንድምህ ቊጣ እስኪበርድ ድረስ ለጥቂት ጊዜ እዚያው ቈይ፤ 45ቊጣውም ሲበርድ ያደረግህበትን ነገር ይረሳል፤ ከዚያ በኋላ ሰው ልኬ አስመጣሃለሁ፤ ለምን ሁለታችሁንም በአንድ ቀን ልጣ?”
ይስሐቅ ያዕቆብን ወደ ላባ መላኩ
46ርብቃ ይስሐቅን “ዔሳው ባገባቸው በእነዚህ በሒታውያን ሴቶች ምክንያት መኖሬን ጠላሁት፤ ያዕቆብ ደግሞ ከነዚህ ከሒታውያን ሴቶች አንዲቱን ካገባ ከመኖር ይልቅ ሞቴን እመርጣለሁ” አለችው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 27: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997