በዚህ ጊዜ አብርሃም በጣም አርጅቶ ነበር፤ እግዚአብሔርም አብርሃምን በሁሉም ነገር ባረከው። አብርሃም የንብረቱ ሁሉ ኀላፊ በመሆን ለረዥም ዘመን የኖረውን አገልጋዩን እንዲህ አለው፤ “እጅህን በጒልበቴ ላይ አድርገህ ማልልኝ፤ ይኸውም እኔ በመካከላቸው ከምኖረው ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች መካከል ለልጄ ሚስት እንዳትመርጥ በሰማይና በምድር አምላክ በእግዚአብሔር ስም ማልልኝ፤ ነገር ግን ወደ ትውልድ አገሬ ሂድ፤ እዚያም ካሉት ወገኖቼ መካከል ለልጄ ለይስሐቅ ሚስት ምረጥለት።” አገልጋዩም “ምናልባት የምመርጥለት ሴት ከእኔ ጋር ወደዚህ አገር ለመምጣት እምቢ ብትልስ? ልጅህን ቀድሞ አንተ ወደነበርክበት አገር እንዲመለስ ላድርገውን?” ብሎ ጠየቀ። አብርሃም ግን እንዲህ አለው፤ “በምንም ምክንያት ቢሆን ልጄን ወደዚያ አገር መልሰህ እንዳትወስድ ተጠንቀቅ! ከአባቴ ቤትና ከትውልድ አገሬ አውጥቶ ይህን ምድር ለዘሬ እንደሚሰጥ በመሐላ ቃል የገባልኝ እግዚአብሔር፥ የሰማይ አምላክ ከዚያ ለልጄ ሚስት ማግኘት እንድትችል መልአኩን በፊትህ ይልካል። ልጅትዋ ከአንተ ጋር ለመምጣት ፈቃደኛ ባትሆን ከዚህ መሐላ ነጻ ትሆናለህ፤ ልጄን ግን በምንም ዐይነት ወደዚያ አትመልሰው።” ከዚህ በኋላ አገልጋዩ እጁን በጌታው በአብርሃም ጒልበት ላይ አድርጎ አብርሃም ያዘዘውን ሁሉ እንደሚፈጽም በመሐላ ቃል ገባ። የአብርሃም ንብረት ኀላፊ የነበረው መጋቢ ከጌታው ቤት ምርጥ የሆኑ የስጦታ ዕቃዎችን በዐሥር ግመሎች ጭኖ በሰሜን መስጴጦምያ ናኮር ወደሚኖርበት ከተማ ሄደ። እዚያ በደረሰ ጊዜ ከከተማው ውጪ ባለ የውሃ ጒድጓድ አጠገብ ግመሎቹ ተንበርክከው እንዲያርፉ አደረገ፤ ሰዓቱም ሊመሽ ተቃርቦ፥ ሴቶች ውሃ ለመቅዳት የሚወጡበት ጊዜ ነበር፤ አገልጋዩም እንዲህ ብሎ ጸለየ፤ “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ ዛሬ የእኔን ሐሳብ በመፈጸም ለጌታዬ ለአብርሃም ዘለዓለማዊ ፍቅርህን ግለጥ። እነሆ፥ እኔ በዚህ የውሃ ጒድጓድ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ የከተማይቱም ልጃገረዶች ውሃ ሊቀዱ ወደዚህ ይመጣሉ፤ ከእነርሱም አንድዋን ልጃገረድ ‘እንስራሽን ዘንበል አድርገሽ ውሃ አጠጪኝ’ እላታለሁ፤ ‘አንተም ጠጣ፤ ግመሎችህም እንዲጠጡ ውሃ ቀድቼ አመጣለሁ’ ካለችኝ ለአገልጋይህ ለይስሐቅ ሚስት እንድትሆን የመረጥካት እርስዋ ትሁን፤ በዚህም ሁኔታ ለጌታዬ ለአብርሃም ዘለዓለማዊ ፍቅርህን እንዳሳየኸው ዐውቃለሁ።” ገና ጸሎቱን ሳይጨርስ ርብቃ እንስራ ተሸክማ መጣች፤ የዚህችም ልጅ አባት በቱኤል ይባል ነበር፤ እርሱም የአብርሃም ወንድም ናኮር ከሚስቱ ከሚልካ የወለደው ነው። ርብቃ ገና ወንድ ያልደረሰባት በጣም ቈንጆ ልጃገረድ ነበረች፤ እርስዋ ወደ ውሃው ጒድጓድ ወርዳ በእንስራዋ ውሃ ከቀዳች በኋላ ተመለሰች። አገልጋዩም ወደ እርስዋ ሮጦ ሄደና “እባክሽ ከእንስራሽ ጥቂት ውሃ አጠጪኝ” አላት። እርስዋም “እሺ ጌታዬ ጠጣ” አለችና እንስራዋን ከትከሻዋ አውርዳ ዘንበል አድርጋ ያዘችለት። ጠጥቶም ከረካ በኋላ “ለግመሎችህም ውሃ እቀዳላቸዋለሁ፤ እስኪበቃቸውም ድረስ ይጠጡ” አለችው። ወዲያውኑ በእንስራዋ የያዘችውን ውሃ ግመሎቹ በሚጠጡበት ገንዳ ላይ ገልብጣ ግመሎቹ ሁሉ ጠጥተው እስከሚረኩ ድረስ እየተጣደፈች ከጒድጓድ ውሃ መቅዳት ቀጠለች። ሰውየውም እግዚአብሔር የሄደበትን ተልእኮ አቃንቶለት እንደሆን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ሁሉ ዝም ብሎ ይመለከት ነበር። ግመሎቹ ጠጥተው ካበቁ በኋላ ሰውየው አምስት ግራም ያኽል የሚመዝን የወርቅ ጒትቻ አውጥቶ በጆሮዋ ላይ አደረገላት፤ መቶ ዐሥር ግራም ያኽል የሚመዝን ሁለት የወርቅ አምባሮችንም አውጥቶ በእጆችዋ ላይ አደረገላትና፥ “የማን ልጅ ነሽ? እስቲ እባክሽ ንገሪኝ፤ ለእኔና አብረውኝ ላሉት ሰዎች ማደሪያ የሚሆን ስፍራ በአባትሽ ቤት ይገኛልን?” ብሎ ጠየቃት። እርስዋም “የባቱኤል ልጅ ነኝ፤ ባቱኤልም ሚልካ ለናኮር የወለደችለት ነው፤ በቤታችን ብዙ ገለባና ድርቆሽ አለ፤ ለእናንተም ማደሪያ ቦታ ይገኛል” አለችው። ሰውየውም በመንበርከክ ለእግዚአብሔር ሰግዶ፥ “ለጌታዬ ያለውን ታማኝነትና ዘለዓለማዊ ፍቅር የጠበቀ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ በቀጥታ መርቶ ወደ ጌታዬ ዘመዶች ቤት ያመጣኝ እርሱ ነው” አለ። ልጅትዋ ወደ ቤት ሮጣ ሄደችና የሆነውን ሁሉ ለእናትዋና ከእርስዋ ጋር ላሉት ሁሉ ነገረቻቸው።
ኦሪት ዘፍጥረት 24 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 24:1-28
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች