ኦሪት ዘፍጥረት 20
20
አብርሃምና አቤሜሌክ
1አብርሃም በመምሬ የነበረውን መኖሪያውን ለቆ ወደ ኔጌብ ሄደ፤ በቃዴስና በሹር መካከልም ተቀመጠ፤ በገራርም በእንግድነት በተቀመጠበት ጊዜ፥ 2አብርሃም ሚስቱን ሣራን እኅቴ ናት አለ፤ ስለዚህ የገራራ ንጉሥ አቤሜሌክ ሰዎች ልኮ ሣራን እንዲያመጡለት አደረገ። #ዘፍ. 12፥13፤ 26፥7። 3ነገር ግን አንድ ሌሊት እግዚአብሔር በሕልም ተገልጦ አቤሜሌክን “ይህች ሴት ባለባል ስለ ሆነች እርስዋን በመውሰድህ ምክንያት ትሞታለህ” አለው።
4ሆኖም አቤሜሌክ ገና ወደ እርስዋ አልቀረበም ነበርና እንዲህ አለ፦ “ጌታ ሆይ! እኔ ምንም በደል አልፈጸምኩም፤ ታዲያ እኔንና ሕዝቤን ታጠፋለህ 5እኅቴ ነች ያለኝ ራሱ አብርሃም ነው፤ እርስዋም ወንድሜ ነው ብላኛለች፤ እኔ ይህን ያደረግኹት በቅንነትና በንጹሕ ኅሊና ስለ ሆነ ምንም በደል አልፈጸምኩም” አለ።
6እግዚአብሔርም በሕልም እንዲህ አለው፦ “በንጹሕ ኅሊና እንዳደረግህ ዐውቄአለሁ፤ ወደ እርስዋ ቀርበህ በእኔ ፊት ኃጢአት እንዳትሠራ ያደረግኩህም ስለዚህ ነው። 7አሁን ግን ሴቲቱን ለባልዋ መልሰህ ስጥ፤ እርሱ ነቢይ ስለ ሆነ እንዳትሞት ይጸልይልሃል፤ እርስዋን መልሰህ ባትሰጥ ግን እንደምትሞት ዕወቅ፤ አንተ ብቻ ሳትሆን ሕዝብህም በሙሉ ታልቃላችሁ።”
8በማግስቱ ጠዋት በማለዳ አቤሜሌክ ባለሟሎቹን ጠርቶ የሆነውን ነገር ሁሉ በተረከላቸው ጊዜ ደነገጡ። 9ከዚህ በኋላ አቤሜሌክ አብርሃምን ጠርቶ፦ “ይህ ያደረግህብን ነገር ምንድን ነው? በእኔና በመንግሥቴ ላይ ይህን በደል ያመጣህብን ምን ያስቀየምኩህ ነገር ቢኖር ነው? አንተ ያደረግህብኝን ነገር ከቶ ማንም ሰው አያደርገውም፤ 10ለመሆኑ ይህን ያደረግኸው ለምንድን ነው?”
11አብርሃምም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ ‘እዚህ ቦታ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው የለም’ ብዬ በማሰብ ‘ሚስቴን ለመውሰድ በመፈለግ ይገድሉኛል’ ብዬ ስለ ሰጋሁ ነው፤ 12ደግሞም እርስዋ የአባቴ ልጅ ስለ ሆነች በእርግጥ እኅቴ ናት፤ ነገር ግን የእናቴ ልጅ ስላልሆነች አገባኋት። 13ስለዚህ እግዚአብሔር ከአባቴ ቤት ወጥቼ ወደ ባዕድ አገር እንድሄድ ባዘዘኝ ጊዜ ‘በምንሄድበት ቦታ ሁሉ እኅቱ ነኝ ብትዪ ለእኔ ታላቅ ውለታ እንዳደረግሽልኝ እቈጥረዋለሁ’ ብዬአት ነበር።”
14ከዚህ በኋላ አቤሜሌክ ሣራን ለአብርሃም መልሶ ሰጠው፤ እንዲሁም በጎችና በሬዎች የወንድና የሴት አገልጋዮችም ሰጠው። 15አብርሃምን “እነሆ የእኔ ግዛት በፊትህ ነው፤ በፈለግከው ስፍራ ኑር” አለው። 16ሣራንም “አንቺ ምንም አስነዋሪ ተግባር ያልፈጸምሽ ንጹሕ መሆንሽን ከአንቺ ጋር ያሉት ሰዎች ሁሉ እንዲረዱት ምልክት ይሆን ዘንድ ለወንድምሽ ለአብርሃም አንድ ሺህ ብር ሰጥቼዋለሁ” አላት።
17ከዚያ በኋላ አብርሃም ለእግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም አቤሜሌክንና ሚስቱን፥ ሴቶች አገልጋዮቹንም ፈውሶአቸው ልጆች እንዲወልዱ አድርጎአቸዋል፤ 18በአብርሃም ሚስት በሣራ ምክንያት የአቤሜሌክ ቤተሰብን ማሕፀን ሁሉ ዘግቶ ነበር።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 20: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997