ወደ ገላትያ ሰዎች 3:1-25

ወደ ገላትያ ሰዎች 3:1-25 አማ05

እናንተ ሞኞች የገላትያ ሰዎች! ማን አፍዝ አደንግዝ አደረገባችሁ? ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ ተሰቅሎ በፊት ለፊታችሁ በግልጥ ይታይ ነበር። ማወቅ የምፈልገው ይህን ብቻ ነው፤ ለመሆኑ እናንተ መንፈስ ቅዱስን የተቀበላችሁት ሕግን በመፈጸም ነውን? ወይስ የምሥራቹን ቃል ሰምታችሁ በማመን ነው? እናንተ በእግዚአብሔር መንፈስ ጀምራችሁ አሁን በሥጋዊ ጥረት መፈጸም ትፈልጋላችሁ፤ ለካ እስከዚህ ድረስ ሞኞች ናችሁ! በወንጌል ምክንያት የተቀበላችሁት መከራ ሁሉ ከንቱ ሆኖ ቀረ ማለት ነውን? ይህን አድርጋችሁ ከሆነ በእርግጥ ከንቱ ሆኖ ቀርቶአል። እግዚአብሔር መንፈሱን የሚሰጣችሁና በእናንተ ዘንድ ተአምራትን የሚያደርገው ሕግን በመፈጸማችሁ ነውን? ወይስ የምሥራቹን ቃል ሰምታችሁ በማመናችሁ ነው? ይህም “አብርሃም በእግዚአብሔር አመነ፤ እምነቱም ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። እንግዲህ የሚያምኑ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ ዕወቁ። እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንደሚያጸድቅ ቅዱስ መጽሐፍ አስቀድሞ አይቶ “ሕዝቦች ሁሉ በአንተ ይባረካሉ” በማለት አስቀድሞ ለአብርሃም የምሥራቹን ቃል አብሥሮአል። ስለዚህ የሚያምኑ ሁሉ ከአመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ። “በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ትእዛዞች ሁሉ ጸንቶ የማይኖርና የማይፈጽማቸው ሁሉ የተረገመ ነው” ተብሎ ስለ ተጻፈ “ሕግን በመፈጸም እንጸድቃለን” የሚሉ ሁሉ የተረገሙ ናቸው። “ጻድቅ ሰው ግን በእምነት ሕይወትን ያገኛል” ተብሎ ስለ ተጻፈ ሕግን በመፈጸም ማንም ሰው በእግዚአብሔር ፊት እንደማይጸድቅ ግልጥ ነው። ሕግ በእምነት ላይ የተመሠረተ አይደለም፤ እንዲያውም “ሰው በሕግ ሊኖር የሚችለው የሕግ ትእዛዞችን ሁሉ ሲፈጽም ነው” ተብሎ ተጽፎአል። “በእንጨት ላይ ተሰቅሎ የሚሞት ሁሉ የተረገመ ነው” ተብሎ ስለ ተጻፈ ክርስቶስ ስለ እኛ እንደ ተረገመ ሰው ሆኖ ሕግ ከሚያስከትለው ርግማን ዋጀን። ይህም የሆነው እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠው በረከት በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ለአሕዛብ እንዲደርስና እኛም እግዚአብሔር እሰጣችኋለሁ ያለውን መንፈስ ቅዱስን በእምነት እንድንቀበል ነው። ወንድሞቼ ሆይ! እስቲ ይህን ነገር በሰው ዘንድ ከተለመደ ነገር ጋር አነጻጽሩት፤ አንድ ሰው የገባው ቃል ኪዳን እንኳ ከጸደቀ በኋላ ማንም ሰው ሊሽረው ወይም ሊጨምርበት አይችልም። እግዚአብሔርም ለአብርሃምና ለዘሩ የተስፋ ቃል የሰጠው በዚህ ዐይነት ነው፤ መጽሐፍ የተስፋ ቃል ከአብርሃም በኋላ የተሰጠው ለብዙዎች እንደ ሆነ አድርጎ “ለዘሮችህ” አይልም፤ ነገር ግን ለአንድ እንደ ሆነ አድርጎ “ለዘርህ” ይላል፤ ይህም “ዘርህ” የተባለው ክርስቶስ ነው። እንግዲህ እኔ የምለው ይህን ነው፤ ከአራት መቶ ሠላሳ ዓመት በኋላ የተሰጠው ሕግ ቀደም ብሎ በእግዚአብሔር ተረጋግጦ የተሰጠውን ቃል ኪዳን በመሻር የተስፋውን ቃል ሊያጠፋው አይችልም። አንድ ነገር የሚወረሰው በሕግ አማካይነት ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር በሰጠው የተስፋ ቃል አማካይነት መሆኑ በቀረ ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ውርስን ለአብርሃም የሰጠው በተስፋው ቃል አማካይነት ነው። ታዲያ፥ ሕግ የተሰጠው ለምንድን ነው? ሕግ የተጨመረው ለአብርሃም በተስፋ የተሰጠው ዘር እስኪመጣ ድረስ ክፉ ሥራ ምን መሆኑን ለማመልከት ነው፤ ሕጉ በሥራ ላይ የዋለው በመላእክት ተሰጥቶ በአንድ ሰው አማካይነት ነው። ይሁን እንጂ በመካከል ሆኖ የሚያስታርቅ ሰው ለሁለት ወገን ነው እንጂ ለአንድ ወገን ብቻ አይሠራም፤ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው። እንግዲህ ሕግ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ይቃወማልን? ከቶ አይቃወምም! ሕይወት የሚገኝበት ሕግ ተሰጥቶ ቢሆን ኖሮ ጽድቅ በሕግ አማካይነት በተገኘ ነበር። ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የተስፋ ቃል ለሚያምኑ እንዲሰጥ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚለው ዓለም በሙሉ ለኃጢአት በመገዛት የኃጢአት እስረኛ ሆኖአል። እምነት ከመምጣቱ በፊት የሕግ እስረኞች ነበርን፤ ይህም እምነት እስከሚገለጥበት ጊዜ ድረስ በሕግ ጥበቃ ሥር ነበርን። በዚህ ዐይነት በእምነት እንድንጸድቅ ክርስቶስ እስኪመጣ ሕግ ሞግዚታችን ሆኖ ነበር። አሁን ግን እምነት ስለ መጣ በሕግ ሞግዚትነት ሥር መሆናችን ቀርቶአል።