የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 7

7
የእስራኤል መጨረሻ መቃረብ
1እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ 2“የሰው ልጅ ሆይ! እኔ ልዑል እግዚአብሔር ስለ እስራኤል ምድር የምለው ይህ ነው፤ በሁሉም አቅጣጫ የዚህች ምድር የመጨረሻ መጥፊያ ደርሶአል።
3“የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! አሁን መጥፊያችሁ ደርሶአል። ቊጣዬን አወርድባችኋለሁ፤ እንደ አካሄዳችሁም እፈርድባችኋለሁ ስለ ርኲሰታችሁም ሁሉ እቀጣችኋለሁ። 4ከቶ አልራራላችሁም፤ ምሕረትም አላደርግላችሁም። በርኲሰት ላይ እስካላችሁ ድረስ እንደ አካሄዳችሁ እቀጣችኋለሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።”
5ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “መከራ በመከራ ላይ ይመጣባችኋል፤ 6መጨረሻው መጥቶአል፤ መጨረሻው ደርሶአል፤ በእናንተ ላይ ተነሥቶአል፤ እነሆ፥ መጥቶአል። 7በምድሪቱ የምትኖሩ ሕዝብ ሁሉ የመጥፊያችሁ ጊዜ ደርሶአል፤ ጊዜው ደርሶአል፤ ቀኑም ቀርቦአል፤ እርሱም የሁከት ቀን ነው እንጂ በከፍተኛ ቦታዎች የመፈንጠዣ ቀን አይደለም።
8“አሁን እኔ በቅርቡ ቊጣዬንና መዓቴን አወርድባችኋለሁ፤ እንዳካሄዳችሁም እፈርድባችኋለሁ፤ በአጸያፊ ድርጊታችሁም ምክንያት እቀጣችኋለሁ። 9ከቶ አልራራላችሁም፤ ምሕረትም አላደርግላችሁም፤ በርኲሰት ላይ እስካላችሁ ድረስ እንደ አካሄዳችሁ እቀጣችኋለሁ፤ በዚያን ጊዜ የምቀጣችሁ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።”
10እነሆ፥ የጥፋት ቀን በእስራኤል ላይ ሊመጣ ተቃርቦአል፤ ግፍና ዐመፅ በዝቶአል፤ ትዕቢትም ከፍ ከፍ ብሎአል። 11ከዐመፅ የተነሣ ክፉ ሥራ በዝቶአል፤ ከእነርሱ መካከል አንዳቸውም አይተርፉም። ከብልጽግናቸውና ከተትረፈረፈ ሀብታቸው አንድ ነገር እንኳ አይኖርም።
12እነሆ ጊዜው ደርሶአል፤ ቀኑም ቀርቦአል፤ የእኔ የእግዚአብሔር ቊጣ በሁሉም ላይ ስለሚመጣ ገዢ አይደሰት፤ ሻጭም አይዘን። 13ሻጭና ገዢ በሕይወት እስካሉ ድረስ ሻጭ የሸጠውን ዕቃ መልሶ ሊያገኘው እንደማይችል ሁሉ እንዲሁም ራእዩ የተነገረው ስለ ሁሉም ስለ ሆነ ሊታጠፍ አይችልም። እነርሱም ስለ በበደሉ ሕይወታቸውን ማዳን አይችሉም። 14መለከት ይነፋል ሁሉ ነገር ይዘጋጃል፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቊጣ በሰው ሁሉ ላይ ስለሚገለጥ ማንም ወደ ጦርነት አይሄድም።
በእስራኤል ኃጢአት ምክንያት የሚመጣው ቅጣት
15ውጪ ጦርነት፥ በየቤቱም በሽታና ራብ አለ፤ ከከተማ ውጪ የሚኖር ሁሉ በጦርነት ይሞታል፤ በከተማም ያለ በበሽታና በረሀብ ይመታል። 16የሸለቆ ርግቦች ራሳቸውን ለማዳን ወደ ተራራ እንደሚወጡ እንዲሁም ከሰዎቹ መካከል ከሞት የተረፉ ካሉ በተራራ ላይ ተገኝተው በኃጢአታቸው ምክንያት እንደ ሸለቆ ርግቦች የሐዘን እንጒርጒሮ ያሰማሉ። 17እጆች ሁሉ ይዝላሉ፤ ጒልበቶች ሁሉ ይብረከረካሉ፤ 18ማቅ ይለብሳሉ፤ ድንጋጤ ይይዛቸዋል፤ በፊቶቻቸው ላይ ኀፍረት ይታያል፤ ራሳቸውንም ይላጫሉ። 19ብራቸውን በየመንገዱ ላይ ይወረውራሉ፤ ወርቃቸውም እንደ ርኩስ ነገር ይቈጠራል፤ ብርና ወርቃቸው በእግዚአብሔር ቊጣ ቀን አያድኑአቸውም፤ ራባቸውን አያስወግዱላቸውም፤ ወይም ሆዳቸውን አይሞሉላቸውም፤ በኃጢአት ለመውደቃቸው ምክንያት የሆኑባቸው እነርሱ ናቸው። 20መመኪያቸው ከሆኑት ውብ ጌጦቻቸው አስጠሊና አጸያፊ ጣዖቶቻቸውን ሠሩባቸው፤ ስለዚህ እነዚህን ጌጦቻቸውን በእነርሱ ዘንድ አረክሳቸዋለሁ።
21እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ጌጦቻችሁን ለባዕዳን በምርኮ፥ ለምድር ኃጢአተኞችም በብዝበዛ መልክ አሳልፌ እሰጣለሁ። እነርሱም ያረክሱታል። 22ወንበዴዎች ወደ ቤተ መቅደሴ ገብተው ያረክሱታል። ሲያረክሱትም አልከለክላቸውም።
23“ሀገሪቱ በነፍስ ግድያ ወንጀል፥ ከተማይቱ በዓመፅ ስለ ተሞሉ የማሰሪያ ሰንሰለት አዘጋጅ። 24በሕዝቦች መካከል እጅግ የከፉትን ወደዚህ አምጥቼ ቤቶቻችሁን እንዲወርሱ አደርጋለሁ፤ የኀያላንን ትዕቢት አጠፋለሁ፤ የተቀደሱ ቦታዎቻችሁንም ያረክሳሉ። 25ጭንቀት በሚመጣበት ጊዜ ሰላምን ትሻላችሁ፤ ነገር ግን አታገኙም፤ 26አንዱ መቅሠፍት ሌላውን ያስከትላል፤ አንዱ ወሬም ሌላውን ወሬ ተከታትሎ ይመጣል፤ ነቢያት ያዩትን ራእይ እንዲነግሩአችሁ ትለምኑአቸዋላችሁ፤ ካህናት ሕዝቡን የሚያስተምሩት ሕግ፥ ሽማግሌዎችም ለሕዝቡ የሚሰጡት ምክር ጠፋባቸው። 27ንጉሡ ያለቅሳል፤ መስፍኑም ሙሉ በሙሉ ተስፋ ይቈርጣል፤ ሕዝቡም ከፍርሃት የተነሣ ይርበደበዳሉ፤ እንደ አካሄዳችሁ እቀጣችኋለሁ፤ በሌሎች ላይ በፈረዳችሁት ዐይነት እፈርድባችኋለሁ፤ በዚህም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ