የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 47

47
ከቤተ መቅደሱ ሥር የሚፈልቀው ውሃ
1ከዚያም በኋላ ወደ ቤተ መቅደሱ መግቢያ መለሰኝ፤ እዚያም ከቤተ መቅደሱ መድረክ ሥር ውሃ ወደ ምሥራቅ ይፈስ ነበር፤ (ይህም የቤተ መቅደሱ በር ወደ ምሥራቅ ዞሮ ስለ ነበረ ነው) ውሃውም የሚፈሰው ከቤተ መቅደሱ በስተደቡብ በኩል ባለው መድረክ ሥር ከመሠዊያው በስተደቡብ ነበር። #ዘካ. 14፥8፤ ዮሐ. 7፥38፤ ራዕ. 22፥1። 2ያም ሰው በሰሜኑ ቅጽር በር በኩል ከቤተ መቅደሱ አውጥቶ ወሰደኝ፤ ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ በሚመለከተውም ቅጽር በር አዞረኝ፤ ከቅጽር በሩም በስተ ደቡብ ውሃው ወደ ምሥራቅ ይፈስ ነበር። 3ያም ሰው በያዘው የመለኪያ ገመድ ወደ ምሥራቅ የሚፈሰውን ውሃ በመከተል አንድ ሺህ ክንድ ለካ፤ በዚያም ውሃ እየተራመድኩ እንድሻገር አደረገኝ፤ ውሃውም እስከ ቊርጭምጭሚቴ ደረሰ። 4እንደገናም አንድ ሺህ ክንድ ለካና እንድራመድ አደረገኝ፤ ውሃውም እስከ ጒልበቴ ደረሰ፤ ቀጥሎም አንድ ሺህ ክንድ ለክቶ በውሃው ውስጥ እንድራመድ አደረገኝ፤ ውሃውም እስከ ወገቤ ደረሰ። 5እንደገናም አልፎ አንድ ሺህ ክንድ ለካ፤ ውሃው ጥልቅ ስለ ነበረ ልሻገረው የማልችል ወንዝ ሆነ፤ እርሱም ሊራመዱበት የማይቻል ለዋና ግን በቂ ጥልቀት ነበረው። 6ሰውየውም “የሰው ልጅ ሆይ! ይህን ሁሉ በጥንቃቄ አስታውስ” አለኝ።
ከዚያን በኋላ ያ ሰው ወደ ውሃው ዳርቻ መለሰኝ፤ 7እዚያም እንደ ደረስኩ በወንዙ ግራና ቀኝ ስመለከት ብዙ ዛፎችን አየሁ፤ 8እርሱም እንዲህ አለኝ፦ “ይህ ውሃ በምድሪቱ ውስጥ ወደ ምሥራቅ፥ ወደ ዮርዳኖስ ሸለቆና ወደ ሙት ባሕር ይፈስሳል፤ ወደ ሙት ባሕር በሚፈስበት ጊዜ የጨዉ ባሕር ታድሶ ጥሩ ውሃ ይሆናል። 9ውሃው በሚፈስበት ስፍራ ሁሉ ልዩ ልዩ ዐይነት እንስሶችና ዓሣም በብዛት ይገኛል፤ የወንዙ ፈሳሽ በሙት ባሕር የሚገኘውን በማደስ ያጠራዋል፤ በሚፈስበትም ቦታ ሁሉ ሕይወትን ይሰጣል። 10ከዔንገዲ ጀምሮ እስከ ዔንዔግላይም ድረስ ዓሣ አጥማጆች ይቆማሉ፤ ያም ቦታ መረቦች የሚዘረጉበት ቦታ ይሆናል፤ በሜዲትራኒያን ባሕር እንደሚገኘው ዐይነት በዚህም ልዩ ልዩ ዓሣ ይገኛል። 11ነገር ግን ረግረጉና እቋሪው ውሃ የጨው መከማቻ እንደ ሆነ ይቀራል እንጂ የጠራ ውሃ አይሆንም። 12በፈሳሹ ውሃ ዳርና ዳር ለምግብ የሚሆኑ ተክሎች በየዐይነቱ ይገኛሉ፤ እነርሱም ቅጠሎቻቸው አይደርቁም፤ ፍሬ ማፍራትንም አያቋርጡም፤ ከቤተ መቅደሱ ሥር የሚፈሰውን ወንዝ ውሃ ስለሚያገኙ በየወሩ አዲስ ፍሬ ያፈራሉ፤ ዛፎቹ ፍሬአቸው ለምግብ፥ ቅጠላቸው ለፈውስ የሚጠቅም ነው።” #ራዕ. 22፥2።
የምድሪቱ ወሰኖች
13ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ለዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ በርስትነት የምታካፍላቸው የመሬት ድንበር የሚከተለው ነው፤ የዮሴፍ ነገድ ሁለት ድርሻ ይኖረዋል። 14እኔ ለቀድሞ አባቶቻችሁ ይህችን ምድር ርስት አድርጌ ልሰጣቸው በመሐላ ቃል ገብቼላቸዋለሁ፤ አሁንም እናንተ ሁላችሁ እኩል ተከፋፈሉት፤ ይህም ምድር በርስትነት የእናንተ ይሆናል።
15“የመሬቱ ድንበር እንደሚከተለው ነው፦ የሰሜኑ ድንበር ከሜዲቴራኒያን ባሕር ተነሥቶ ወደ በሔትሎን በኩል ወደ ሐማት መተላለፊያ፥ ወደ ጼዳድም፥ 16በደማስቆና በሐማት መካከል ወደሚገኙት ወደ ቤሮታና ሲብራይም ከተሞች፥ በሐውራን ጠረፍ ወደምትገኘው ወደ ቲኮን ከተማ እስከ ምሥራቅ ይዘልቃል። 17በዚህም መሠረት ድንበሩ ከሜዲቴራኒያን ባሕር ተነሥቶ እስከ ሐጻር ዔኖን፥ እርሱም በደማስቆና በሐማት ድንበር በስተሰሜን እስካለው ቦታ ድረስ ይደርሳል፤ ይህም የሰሜኑ ድንበር ነው።
18“የምሥራቁ ድንበር በደማስቆና በሐውራን መካከል አልፎ በዮርዳኖስ በኩል፥ በጊልዓድና በእስራኤል ምድር መካከል አልፎ ወደ ሙት ባሕርና እስከ ታማር ድረስ ነው። ይህም የምሥራቁ ድንበር ይሆናል።
19“የደቡቡም ድንበር ከታማር ተነሥቶ እስከ መሪባ ቃዴስ ድረስ፥ ከዚያም ከግብጽ ሸለቆ እስከ ሜዲቴራኒያን ባሕር ይደርሳል፤ ይህም የደቡብ ድንበር ነው።
20“የምዕራቡ ድንበር የሜድትራኒያን ባሕር ሆኖ፥ እስከ ሐማት መግቢያ አንጻር ድረስ ይደርሳል። ይህም የምዕራቡ ድንበር ይሆናል።
21“ይህችን ምድር በእስራኤል ነገዶች መካከል ተከፋፈሉአት። 22ዘላቂ ርስትም ትሁንላችሁ፤ ልጆች ወልደው በመካከላችሁ የሚኖሩ ባዕዳንም ምድሪቱን በምትካፈሉበት ጊዜ የራሳቸው ድርሻ ይኑራቸው፤ እንደማንኛውም እስራኤላውያን ዜጋ ተቈጥረው ምድሪቱን ከሚካፈሉት ከእስራኤል ነገዶች ጋር ዕጣ እንዲጣልላቸው ያስፈልጋል። 23በእስራኤል የሚኖር እያንዳንዱ የውጪ አገር ተወላጅ አብሮ ከሚኖረው ከእስራኤል ሕዝብ ነገድ ጋር የራሱ ድርሻ ይኑረው፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ