ትንቢተ ሕዝቅኤል 38
38
ጎግ የእግዚአብሔር መሣሪያ ሆኖ ይነሣል
1እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ 2“የሰው ልጅ ሆይ! በማጎግ ምድር የሚገኙት የሜሼክና የቱባል ሕዝቦች ገዢ የሆነውን ጎግን በመቃወም ትንቢት ተናገርበት፤ #ራዕ. 20፥8። 3እኔ ልዑል እግዚአብሔር እርሱን የምቃወም መሆኔን ንገረው። 4በመንጋጋው መንጠቆ አስገብቼ በመጐተት እርሱንና ሠራዊቱን ወደ መጡበት ወደ ኋላቸው እመልሳቸዋለሁ፤ ሠራዊቱ ከፈረሶችና የጦር ልብስ ከለበሱ ፈረሰኞቹ ጋር እጅግ የበዛ ነው፤ እያንዳንዱ ወታደር ትልቅና ትንሽ ጋሻ አንግቦ ሰይፍ ታጥቆአል፤ 5ከፋርስ፥ ከኢትዮጵያና ከሊቢያ የመጡ ሰዎችም ሁሉ ጋሻ አንግበው የራስ ቊር ደፍተው የእርሱ ተባባሪዎች በመሆን ከእርሱ ጋር ተሰልፈዋል። 6ጎሜር ከሠራዊቱ ሁሉ ጋርና፥ ራቅ ካለው የሰሜን ክፍልም ቤት ቶጋርማና ሠራዊቱ ከእርሱ ጋር ናቸው፤ እንዲሁም ከሌሎች ብዙዎች አገሮች የመጡ ሰዎች ከእርሱ ጐን ተሰልፈዋል። 7ስለዚህ እንዲዘጋጅ ንገረው፤ ሠራዊቱንም ሁሉ በእርሱ ትእዛዝ ሥር እንዲያዘጋጅ አስታውቀው። 8መዘጋጀትም ያለበት ከብዙ ጊዜ በኋላ በጦርነት ወድማ የነበረችውን የእስራኤልን ምድር እንዲወር ስለማዘው ነው፤ ለብዙ ጊዜ ባድማ ሆና ነበር፤ ሕዝብዋ ይኖሩባቸው ከነበሩት አገሮች ተመልሰዋል፤ አሁን እስራኤላውያን በሀገራቸው ውስጥ በሚገኙ ተራራዎች ላይ በሰላም ይኖራሉ። 9እርሱና ሠራዊቱ፥ እንዲሁም ከእርሱ ጋር ያሉ ብዙ ሕዝብ እንደ ማዕበል ሞገድ ሆነው ይመጣሉ፤ እንደ ደመናም ሆነው ምድሪቱን ይሸፍናሉ።”
10ልዑል እግዚአብሔር ለጎግ የሚለው ይህ ነው፥ “ያ ዘመን ሲደርስ ሐሳብ ወደ አእምሮህ ይመጣል፤ ክፉ ዕቅድም ታቅዳለህ። 11አንተም እንደዚህ ትላለህ፦ ቅጽር በሌላቸው መንደሮች ላይ እወጣለሁ፤ ቅጽርና ባለ መወርወሪያ መዝጊያ ሳይኖራቸው ጸጥ ብለው በሰላም በሚኖሩ ሰዎች ላይ አደጋ እጥላለሁ። 12ከሕዝቦች መካከል የተመለሱትም ሰዎች በምድር እምብርት ላይ ይኖራሉ፤ እነርሱም እንስሶችና ቈሳቊስ አሉአቸው። ባድማ የነበረችውም ምድር አሁን የሰው መኖሪያ ሆናለች፤ ሐሳቤ ምርኮን ለመማረክና ለመውሰድ፥ እንዲሁም በእነርሱ ላይ አደጋ ለመጣል ነው። 13ሳባና ዴዳን፥ እንዲሁም የተርሴስ ነጋዴዎችና ወጣት ጦረኞች እንዲህ ይሉሃል፦ ‘ምርኮን ለመውሰድ መጣህን? ብርንና ወርቅን፥ እንስሶችና ቈሳቊስን፥ ማለት ብዙ ምርኮን እንዲያጓጒዙልህ ብዛት ያላቸውን ሰዎችህን ሰበሰብክን?’ ”
14ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ! በጎግ ላይ እንዲህ ብለህ ትንቢት ተናገር፤ “ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘በዚያን ቀን ሕዝቤ እስራኤል በሰላም በሚኖሩበት ጊዜ አንተ ራስህን ታነሣሣለህ። 15በስተ ሰሜን በኩል ርቀህ ከምትኖርበት ስፍራ ሁሉም በፈረስ ላይ የሚቀመጡትን የብዙ ሕዝቦች ታላላቅ ሠራዊትን መርተህ ትመጣለህ። 16በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ምድርን እንደሚሸፍን ደመና ትመጣባቸዋለህ፤ ጎግ ሆይ፥ በኋለኛው ዘመን በምድሬ ላይ እንድትመጣ አደርግሃለሁ፤ ይህንንም የማደርገው በአንተ አማካይነት ቅድስናዬን በፊታቸው በምገልጥበት ጊዜ ሕዝቦች እንዲያውቁኝ ነው።’ ” 17ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አንተን እንደማመጣ አገልጋዮቼ የእስራኤል ነቢያት በቀድሞ ዘመን በመደጋገም ትንቢት ተናግረዋል።”
እግዚአብሔር በጎግ ላይ የሚያመጣው ቅጣት
18ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ጎግ እስራኤልን በሚወርበት ጊዜ የእኔ ብርቱ ቊጣ ይነሣሣል፤ 19በዚያን ቀን በእስራኤል ምድር ታላቅ የመሬት መንቀጥቀጥ እንደሚሆን በቅናቴና በሚነድ ቊጣዬ ዐውጃለሁ። 20እያንዳንዱ የዓሣና የወፍ ዐይነት፥ እያንዳንዱም አውሬና እንስሳ በምድር የሚኖር እያንዳንዱ ሰው እኔን በመፍራቱ ይንቀጠቀጣል፤ ተራራዎች ይወድቃሉ፤ ገደሎች ተፈረካክሰው ይናዳሉ፤ እያንዳንዱም የቅጽር ግንብ ይደረመሳል። 21በተራሮቼ ሁሉ በጎግ ላይ ሰይፍ እንዲመዘዝ አደርጋለሁ፤ የያንዳንዱም ሰው ሰይፍ ጓደኛውን ይበላል። 22በቸነፈርና በግድያ እንዲቀጣ እፈርድበታለሁ፤ በእርሱ ላይ፥ በወታደሮቹ ላይና ከእርሱ ጋር በነበሩት ሰዎች ላይ የዝናብ ዶፍ፥ የበረዶ ናዳ፥ እሳትና ዲን አዘንብባቸዋለሁ። 23በዚህም ዐይነት ታላቅነቴንና ቅድስናዬን አሳያለሁ፤ በብዙ ሕዝቦችም ዘንድ ራሴን አሳውቃለሁ፤ ከዚያ በኋላ እነርሱ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 38: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997