የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 36:13-38

ትንቢተ ሕዝቅኤል 36:13-38 አማ05

“እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምለው ይህ ነው፤ ሕዝቡ ይህችን ምድር ‘ሰው በላ’ ብለው የሚጠሩአትና ሕዝብዋንም ‘ልጆች አልባ’ አድርጋለች የሚሉት ነገር እውነት ነው። ከእንግዲህ ወዲህ ግን ምድሪቱ ‘ሰው በላ’ አትሆንም፤ ልጆቻችሁንም አትነጥቅም፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። ምድሪቱ ከእንግዲህ ወዲህ የሕዝቦች ማላገጫ አትሆንም፤ በንቀትም አይመለከቱአትም፤ ምድሪቱንም ዳግመኛ ልጅ አልባ የሚያደርጋት አይኖርም። እኔ ጌታ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ! የእስራኤል ሕዝብ በዚህች አገር ሲኖሩ በከንቱ አኗኗራቸውና በመጥፎ ሥራቸው ሁሉ ምድሪቱን አርክሰዋት ነበር፤ በፊቴም የነበራቸው አካሄድ፥ ሴት በወር አበባዋ ወቅት እንደ ርኩስ ሆና የምትታይበትን ያኽል ነበር። በሀገሪቱ ላይ ስለ ፈጸሙት ግድያና በጣዖት አምልኮም ምድሪቱን በማርከሳቸው ምክንያት ኀይለኛ ቊጣዬን አወረድኩባቸው። አኗኗራቸውና ሥራቸው ሁሉ መጥፎ ስለ ነበረ ፈረድኩባቸው፤ በባዕዳን አገሮችም እንዲበተኑ አደረግሁ። እነዚህ የእግዚአብሔር ሕዝብ ቢሆኑም እንኳ እርሱ ከሰጣቸው ምድር ወጥተዋል” ብለው የተበታተኑባቸው አገሮች ሕዝቦች ስለሚናገሩ ሕዝቤ ቅዱስ ስሜን አሰድበዋል። ነገር ግን የእስራኤል ሕዝብ በሄዱባቸው ሕዝቦች መካከል ቅዱስ ስሜን ማሰደባቸው ያሳስበኛል። “እንግዲህ እነሆ፥ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ስለ እነርሱ የምልህን ሁሉ ንገራቸው፤ ከእንግዲህ ወዲህ የማደርግላችሁ ነገር በሄዳችሁበት ስፍራ ሁሉ ስላሰደባችሁት ስለ ቅዱስ ስሜ እንጂ ስለ እናንተ ስለ እስራኤላውያን ብዬ አይደለም። በሕዝቦች መካከል ተሰድቦ የነበረውን፥ ማለት እናንተ አሰደባችሁት የነበረውን የታላቁን ስሜን ቅድስና አሳያለሁ፤ ከዚያ በኋላ በእናንተ አማካይነት በእነርሱ ፊት ቅድስናዬን በምገልጥበት ጊዜ ሕዝቦች እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ። ከመንግሥቶች ከአገሮች ሁሉ አውጥቼ በመሰብሰብ ወደ ገዛ ምድራችሁ እመልሳችኋለሁ። በእናንተ ላይ ንጹሕ ውሃ በመርጨት ከጣዖት አምልኮአችሁና ከርኲሰታችሁ ሁሉ እንድትነጹ አደርጋለሁ። አዲስ ልብ እሰጣችኋለሁ፤ አዲስ መንፈስንም በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ ከሰውነታችሁ እንደ ድንጋይ የጠጠረ ልብን አውጥቼ እንደ ሥጋ የለሰለሰ ልብን እሰጣችኋለሁ። መንፈሴን አሳድርባችኋለሁ፤ የሰጠኋችሁንም ሕግና ሥርዓት ሁሉ በጥንቃቄ መፈጸም እንድትችሉ አደርጋችኋለሁ። ከዚያም በኋላ ለቀድሞ አባቶቻችሁ በሰጠኋት ምድር ትኖራላችሁ፤ እናንተ ሕዝቤ ትሆናላችሁ፤ እኔም አምላካችሁ እሆናለሁ። ከርኲሰታችሁ ነገር ሁሉ አድናችኋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ራብ እንዳይደርስባችሁ እህል እንዲበዛላችሁ አዛለሁ። የዛፋችሁና የእርሻችሁ ፍሬ ሁሉ እንዲበዛ አደርጋለሁ፤ ከዚያም በኋላ እናንተን በአሕዛብ መካከል የሚያዋርድ ራብ አይደርስባችሁም። መጥፎ ጠባያችሁንና ትፈጽሙት የነበረውንም ክፉ ሥራ ሁሉ ታስታውሳላችሁ፤ በኃጢአታችሁና ትፈጽሙት በነበረው የረከሰ ሥራ ምክንያት ራሳችሁን ትጸየፋላችሁ። እኔ የማደርገውን ነገር ሁሉ ለእናንተ ብዬ የማላደርግ መሆኔ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፤ ስለዚህ እስራኤል ሆይ! በአካሄዳችሁ ኀፍረትና ውርደት ይሰማችሁ።” ይህን የተናገረ ልዑል እግዚአብሔር ነው። ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔ ከኃጢአታችሁ ሁሉ በማነጻችሁ ጊዜ የፈራረሱትን ሁሉ በመገንባት እንደገና በከተሞቻችሁ እንድትኖሩ አደርጋለሁ። በእርሻዎቻችሁ በኩል በሚያልፉ ሰዎች ሁሉ ዘንድ ባድማ ሆና ትቈጠር የነበረችው ምድር ትታረሳለች። ተመልካችም ሁሉ ‘ጭራሽ ምድረ በዳ ሆና የነበረች ይህች ምድር እንዴት የዔደንን ገነት መሰለች! ቀድሞ ባድማ ወናና የፍርስራሽ ክምር ሆነው የነበሩትስ ከተሞች እንዴት እንደገና ሕዝብ ሊኖርባቸውና የተመሸጉ ሊሆኑ ቻሉ?’ ይላሉ። በዚያን ጊዜ ከጥፋት የተረፉት የጐረቤት አገሮች ሕዝብ ሁሉ የፈረሱ ከተሞችን መልሼ የሠራሁና ባድማ የሆነውን ቦታ ያለመለምኩ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ እንደምፈጽም ተናግሬአለሁ፤ ደግሞም እፈጽመዋለሁ።” ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እስራኤላውያን ደግመው አንድ ጊዜ ይህን እንዲለምኑኝ አደርጋለሁ፤ ቊጥራቸውንም እንደ በጎች መንጋ አበዛዋለሁ። ቀድሞ ኢየሩሳሌም በበዓል ቀን ለመሥዋዕት በሚቀርቡ በጎች ትሞላ እንደ ነበረች የፈራረሱት ከተሞች በሕዝብ የተሞሉ ይሆናሉ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ያውቃሉ።”