የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 27

27
ስለ ጢሮስ የወጣ ሙሾ
1እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 2“የሰው ልጅ ሆይ! ስለ ጢሮስ ሙሾ አውጣ፤ 3ወደ ባሕር መግቢያ በሚወስደው መንገድ ላይ ተቀምጣ ከተለያዩ የጠረፍ ከተሞች ለሚመጡ ነጋዴዎች አገናኝ ለሆነችው ለጢሮስ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገራት፦
‘ጢሮስ ሆይ! በፍጹም ውብ ነኝ ብለሻል።
4መኖሪያሽ ባሕር ነው፤
ገንቢዎችሽ እንደ ተዋበች መርከብ ሠርተውሻል።
5ሳንቃሽ የተሠራው ከሔርሞን ተራራ በተገኘ ጥድ ነው፤
ምሰሶዎችሽ የተሠሩት በሊባኖስ ዛፍ ነው።
6መቅዘፊያዎችሽ የተሠሩት
ከባሳን በተገኘ የወርካ ዛፍ ነው፤
ወለልሽም የተሠራው ከቆጵሮስ በተገኘ
ልዩ በሆነ የጥድ ሳንቃ ነው፤
ዙሪያውም በዝሆን ጥርስ ተለብጦአል።
7የመርከብ ሸራሽ እንደ ዓላማ ሆኖ ከሩቅ ይታይ ዘንድ፥
በእጅ ሥራ ባጌጠ የግብጽ በፍታ ተሠርቶአል፤
መጋረጃዎችሽ ከቆጵሮስ ደሴት በተገኘ
እጅግ በሚያምር ሰማያዊ ሐምራዊ ጨርቅ ተሠርቶአል፤
8ቀዛፊዎችሽ ሲዶናና አርዋድ ከተባሉ ከተሞች የመጡ ናቸው፤
ጢሮስ ሆይ! ባለሙያዎችሽ
የመርከብ አዛዦችሽ ነበሩ።
9የተበላሸውን ለመጠገን በጌባል ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎች
በአንቺ መካከል ነበሩ፤ መርከበኞች በመርከባቸው ወደ ወደብሽ እየመጡ
ከአንቺ ጋር ይገበያዩ ነበር።’
10“ከፋርስ፥ ከልድያና ከሊቢያ የመጡ ወታደሮች በሠራዊትሽ ውስጥ ያገለግላሉ፤ ጋሻቸውንና የራስ ቊራቸውን በጦር ሰፈርሽ ሰቅለዋል፤ እነርሱ ለአንቺ ክብር ያስገኙ ሰዎች ናቸው። 11ከአርዋድ የመጡ ወታደሮች የቅጽር ግንቦችሽን ይጠብቁ ነበር፤ ከጋማድም የመጡ ሰዎች ምሽጎችሽን ይጠብቁ ነበር፤ ጋሻዎቻቸውን በግንቦችሽ ላይ ሰቀሉ፤ የተዋብሽ እንድትሆኚ ያደረጉሽ እነርሱ ናቸው።
12“ከብልጽግናሽ ብዛት የተነሣ ከተርሴስ ጋር ንግድ በመለዋወጥ በአንቺ ዕቃዎች ለውጥ ከእርስዋ ብር፥ ብረት፥ ቆርቆሮና እርሳስ ታገኚ ነበር። 13ከግሪኮች ከቱባልና ከሜሼክ ጋር የንግድ ሥራ ታካሂጂ ነበር፤ ባሪያዎችንና ከነሐስ የተሠሩ ዕቃዎችን ወስደሽ፥ በምትኩ ሸቀጥሽን ትሰጪአቸው ነበር፤ 14ከቤትቶጋርማ የበረሓ ፈረሶችን፥ የጦር ፈረሶችንና በቅሎዎችን ወስደሽ ሸቀጥሽን ለእነርሱ ትሸጪ ነበር። 15ከሮድ አገር ሰዎች ጋር የንግድ ሥራ ታካሂጂ ነበር፤ በባሕር ዳር የሚገኙ አገሮች ሕዝቦች ሸቀጥሽን ወስደው በምትኩ የዝሆን ጥርስና ዞጲ ያመጡልሽ ነበር። #27፥15 ሮድ ሌሎች ትርጒሞች ዴዳን ይሉታል። 16የሶርያ ሕዝብ የንግድ ሸቀጥሽን ሁሉና ሌሎችንም ብዙ ዕቃዎች ይገዙሽ ነበር፤ በወሰዱአቸውም ዕቃዎች ምትክ በሉር፥ ሐምራዊና በጥልፍ ያጌጠ ልብስ፥ ቀጭን ሐር፥ ከዛጎል የተሠሩ ጌጣጌጦችና ቀይ ዕንቊ ይሰጡሽ ነበር፤ 17የይሁዳና የእስራኤል ነጋዴዎች ለሸቀጥሽ ዋጋ የሚኒት አገር ስንዴ፥ ማሽላ፥ ማር፥ የወይራ ዘይትና ቅመማ ቅመም ይከፍሉሽ ነበር። 18የደማስቆ ሕዝብ ስለ ሸቀጥሽና ስለ ሌሎችም ዕቃዎችሽ ከሔልቦን የተገኘ የወይን ጠጅና ከሳሖር የተገኘ የበግ ጠጒር ይሰጡሽ ነበር። 19በኡዛል የሚኖሩ ዳናውያንና ግሪኮች አሞናውያን ያንቺን ዕቃዎች ለመግዛት የንግድ ስምምነት አደረጉ፤ እነርሱም በአንቺ ሸቀጦች ልዋጭ ቀልጦ የተሠራ ብረት፥ ቅመማ ቅመምና የጠጅ ሣር አቀረቡ። 20የደዳን ሕዝብ ስለ ሸቀጥሽ ልዋጭ የኮርቻ ልብስ ያመጣልሽ ነበር። 21ዐረቦችና የቄዳር ምድር አለቆች ሁሉ ስለ ንግድ ዕቃሽ ጠቦቶች፥ በጎችና ፍየሎች ያመጡልሽ ነበር፤ 22የሳባና የራዕማ ነጋዴዎች ለሸቀጥሽ ልዋጭ የከበሩ ድንጋዮች፥ ወርቅና ምርጥ የሆኑ ቅመማ ቅመሞች ያቀርቡልሽ ነበር። 23የካራን፥ የካኔህና የዔደን ከተሞች፥ የሳባ ነጋዴዎች፥ የአሹርና የኪልማድ ከተሞች፥ እነዚህ ሁሉ ከአንቺ ጋር ይነግዱ ነበር። 24የተዋቡ ልብሶችን፥ ሐምራዊ ጨርቆችንና፥ በእጅ ሥራ ያጌጡ ልብሶችን፥ ደማቅ የሆኑ ሥጋጃዎችን፥ በደንብ በተገመዱ ሲባጎዎችና ገመዶችን አጥብቀው በማሰር ይሸጡልሽ ነበር። 25የተርሴስ መርከቦች ዕቃዎችሽን ለመጫን ያገለግሉሽ ነበር።
“አንቺ በባሕር መካከል በከባድ ሸቀጣ ሸቀጥ ተሞልተሻል፤ #ራዕ. 18፥11-19።
26ቀዛፊዎችሽ አውጥተው ወደ ጥልቁ ባሕር ወሰዱሽ፤
ኀይለኛውም የምሥራቅ ነፋስ አንገላትቶ በባሕሩ ውስጥ ሰባበረሽ።
27የንግድ ሸቀጥ ሀብትሽ ሁሉ፥
መርከብ ነጂዎችሽ ሁሉ፥
በመርከብ ውስጥ የሚያገለግሉ
ጠጋኞችሽና ነጋዴዎችሽ ሁሉ፥
በመርከቢቱ ውስጥ የነበሩ ወታደሮች ሁሉ፥
መርከቦችሽ ሲሰባበሩ ሁሉም ወደ ጥልቁ ባሕር ይሰጥማሉ።
28መርከበኞቹ ወደ ባሕር ሲሰጥሙ ያሰሙት ጩኸት
በባሕር ዳር ያሉትን አገሮች አንቀጠቀጡ።
29“በዚህም ጊዜ የሌሎች መርከቦች ቀዛፊዎች
ነጂዎችና የመርከቦቹ አዛዦች ሁሉ
ወጥተው በባሕሩ ጠረፍ ቆሙ።
30ሁሉም በራሳቸው ላይ ትቢያ ነስንሰው
በዐመድ ላይ እየተንከባለሉ፥
ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ስለ አንቺ ምርር ብለው ያለቅሳሉ።
31ስለ አንቺም በማዘን ጠጒራቸውን ተላጭተው ማቅ ይለብሳሉ፤
ከልባቸው በማዘን ምርር ብለው ስለ አንቺ ያለቅሳሉ።
32በሐዘናቸውም ስምሽን እያነሡ ያለቅሳሉ።
ስለ አንቺም ሙሾ ያወጣሉ፤ እንዲህም ይላሉ፦
‘በባሕር መካከል ጠፍታ እንደ ቀረች
እንደ ጢሮስ ያለ ማን ነው?
33የሸቀጥ ዕቃሽ በየሀገሩ ሲሠራጭ፥
የየሀገሩን ሕዝብ ፍላጎት ያሟላ ነበር፤
ከአንቺ በተትረፈረፈ ሀብትና ሸቀጥ
የምድር ነገሥታትን አበልጽገሻል።
34አሁን ግን በጥልቁ ባሕር ውስጥ ተሰባብረሽ ቀርተሻል፤
የሸቀጥ ዕቃሽና ለአንቺ ያገለገሉ ሰዎች ሁሉ
ከአንቺ ጋር አብረው ጠፍተዋል፤’
35“በባሕር ጠረፍ የሚኖሩ ሁሉ አንቺን ከገጠመሽ መጥፎ ዕድል የተነሣ ደንግጠዋል፤ ንጉሦቻቸውም እንኳ ሳይቀሩ ተሸብረዋል፤ በያንዳንዳቸውም ፊት ላይ ፍርሀት ይነበባል። 36እነሆ የሕዝቦች ነጋዴዎች ያላግጡብሻል። መጨረሻሽ አስደንጋጭ ሆኖአል፤ ለዘለዓለምም አትገኚም።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ