ትንቢተ ሕዝቅኤል 17
17
የንስርና የወይን ተክል ምሳሌ
1እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 2“የሰው ልጅ ሆይ! ለእስራኤላውያን እንቆቅልሽ አቅርብላቸው፤ በምሳሌም አብራርተህ ግለጥላቸው፤ 3-4እኔ ልዑል እግዚአብሔር ለእነርሱ የምለውን ያውቁ ዘንድ ይህን ንገራቸው፤ የተዋቡ ላባዎችና ታላላቅ ክንፎች ያሉት አንድ ግዙፍ ንስር ነበረ፤ ይህም ንስር ወደ ሊባኖስ ተራራዎች በረረ፤ በአንድ የሊባኖስ ዛፍ ላይ አርፎም ጫፉን በመቊረጥ የንግድ ሥራ ወደ ተስፋፋበት ወደ አንድ አገር አምጥቶም ነጋዴዎች በበዙባት ከተማ አኖረው። 5ከዚያም በኋላ ከእስራኤል ምድር ዘር ወስዶ በቂ ውሃ እያገኘ በሚያድግበት በአንድ ለም ስፍራ ተከለው። 6ተክሉም አደገና ከምድር ብዙ ከፍ ሳይል በሰፊው የተንሰራፋ የወይን ተክል ሆነ፤ ቅርንጫፎቹ ወደ ንስሩ ከፍ ብለው አደጉ፤ ሥሮቹም ወደ መሬት ዘልቀው ገቡ፤ የወይን ተክሉ ብዙ ቅርንጫፎችና ቅጠሎች አብቅሎ ነበር።
7“እንዲሁም ታላላቅ ክንፎችና ብዙ ላባዎች ያሉት ሌላ ግዙፍ ንስር ነበረ፤ አሁን እንግዲህ የወይን ተክሉ ሥሮቹንና ቅርንጫፎቹን ወደ ንስሩ ዘረጋ፤ ይህንንም ያደረገው ከተተከለበት መደብ ውሃ ያጠጣው ዘንድ ነው። 8ነገር ግን የወይኑ ተክል እንደገና የተተከለው ቅጠሉ በሚገባ ለምልሞ ፍሬ በማፍራት የተዋበ ተክል መሆን በሚችልበት በቂ ውሃ ባለበት ስፍራ ነበር።
9“ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ተናገር፦ ይህ የተተከለው የወይን ተክል ይጸድቃልን? የመጀመሪያው ንስር ሥሩን ነቅሎ ፍሬው እንዲበሰብስና እንዲደርቅ እንዲሁም ለምለም ቅጠሉ እንዲጠወልግ አያደርገውምን? ሥሩን ለመንቀል ጠንካራ የጦር መሣሪያ ወይም ኀይለኛ ሠራዊት አያስፈልገውም። 10የወይኑ ተክል ተተክሏል። ታዲያ ጸድቆ ማደግ ይችላልን? ኀይለኛው የበረሓ ነፋስ በሚመታው ጊዜ ባደገበት በመደቡ ላይ እንዳለ ፈጽሞ አይደርቅምን?”
የምሳሌው ትርጒም
11እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 12“የምሳሌውን ትርጒም ያውቁ እንደ ሆነ እስቲ እነዚህን ዐመፀኞች ጠይቃቸው፤ የባቢሎን ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ንጉሡንና መሳፍንቱን ወደ ባቢሎን የወሰዳቸው መሆኑን ንገራቸው፤ #2ነገ. 24፥15-20፤ 2ዜ.መ. 36፥10-13። 13ከንጉሡም ቤተሰብ አንዱን ወስዶ ከእርሱ ጋር የስምምነት ውል አደረገ፤ ለእርሱም ታማኝ እንዲሆንለት በመሐላ ቃል አስገባው፤ ሌሎቹንም የታወቁ ሰዎች ወሰዳቸው። 14ይህንንም ያደረገው የይሁዳ መንግሥት በትሕትናና በታዛዥነት በቃል ኪዳኑ ጸንቶ እንዲኖር ለማድረግ ነው። 15ነገር ግን የይሁዳ ንጉሥ ዐምፆ ፈረሶችንና ታላቅ ሠራዊት እንዲያመጡለት መልእክተኞችን ወደ ግብጽ ላከ፤ ታዲያ ይህ ዕቅዱ ይሳካለታልን? በዚህስ ሊያመልጥ ይችላልን? ውሉን የሚያፈርስ ከሆነ ከቅጣት ከቶ ያመልጣልን?
16“ልዑል እግዚአብሔር ሕያው አምላክ እንደ መሆኔ ይህ ንጉሥ በዙፋን ላይ ካስቀመጠው ከባቢሎን ንጉሥ ጋር በመሐላ የገባውን የስምምነት ውል በማፍረሱ ምክንያት በባቢሎን ይሞታል። 17ባቢሎናውያን ብዙ ሰዎችን ለመግደል ቦይ ቆፍረው ዐፈር በመደልደል ምሽግ በሚሠሩበት ጊዜ፥ የግብጽ ንጉሥ ብዙ ተዋጊና ብርቱ ሠራዊት እንኳ መጥቶ በመዋጋት ሊረዳው አይችልም። 18እርሱ መሐላውን በመናቅ ቃል ኪዳኑን ስላፈረሰና እጁን ከሰጠ በኋላ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ስላደረገ አያመልጥም።”
19ስለዚህ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔ ሕያው እንደ መሆኔ በእኔ ስም የማለውን መሐላ ንቆ ቃል ኪዳኑን በማፍረሱ መሐላው በራሱ ላይ እንዲደርስ አደርጋለሁ። 20መረቤን በእርሱ ላይ ዘርግቼ በወጥመድ እንዲያዝ አደርጋለሁ፤ በእኔ ላይ ስለ ፈጸመው ክሕደት ወደ ባቢሎን አምጥቼ እፈርድበታለሁ። 21ምርጥ የሆኑ ወታደሮቹ በጦር ሜዳ ይገደላሉ፤ ከሞት የሚያመልጡትም በየአቅጣጫው ይበተናሉ፤ በዚያን ጊዜ ይህን የተናገርኩት እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።”
እግዚአብሔር የሰጠው የተስፋ ቃል
22ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“ከሊባኖስ ዛፍ ጫፍ ላይ አንድ ቅርንጫፍ እወስዳለሁ፤
ከዚያም ላይ ከለጋዎቹ ቀንበጦች አንዱን እቀነጥባለሁ፤
እኔው ራሴ በከፍተኛ ተራራ ላይ እተክለዋለሁ።
23የምተክለው በእስራኤል በሚገኝ በከፍተኛ ተራራ ላይ ነው፤
ይህንንም የማደርገው ቅርንጫፎችን አስገኝቶ
ፍሬ በማፍራት የተዋበ የሊባኖስ ዛፍ እንዲሆን ነው።
በሥሩም የተለያዩ ወፎች ይኖሩበታል፤
በቅርንጫፎቹም ጥላ ሥር ክንፍ ያላቸው ፍጥረቶች ሁሉ ጎጆዎቻቸውን ይሠሩበታል።
24በምድሪቱ ያሉ ዛፎች ሁሉ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ፤
እኔ ረጃጅም ዛፎችን አሳጥራለሁ፤
አጫጭር ዛፎችንም ከፍ ብለው እንዲያድጉ አደርጋለሁ፤
እኔ ለምለም ዛፎችን አደርቃለሁ፤
ደረቅ ዛፎችንም አለመልማለሁ፤
እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ፤
አደርጋለሁ ያልኩትንም ሁሉ እፈጽማለሁ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 17: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997