መጽሐፈ መክብብ 5:1-7

መጽሐፈ መክብብ 5:1-7 አማ05

ወደ እግዚአብሔር ቤት በምትገባበት ጊዜ ለአረማመድህ ጥንቃቄ አድርግ፤ እዚያ ሄዶ ደጉን ከክፉ ለይተው የማያውቁ ሞኞች ሰዎች እንደሚያደርጉት መሥዋዕት ከማቅረብ ይልቅ የምክር ቃላትን ለመስማት ዝግጁ ሆኖ መገኘት ይበልጣል። ከመናገርህ በፊት አስብ፤ ለእግዚአብሔር አንድ ነገር ለመስጠት በችኰላ ስእለት አታድርግ፤ እግዚአብሔር በሰማይ አንተ ግን በምድር መሆንህን በማሰብ የምትናገረው ቃል የተመጠነ ይሁን። ስለ አንድ ነገር ብታስብ ስለ እርሱ ታልማለህ፤ ብዙ ከመናገር የተነሣ ትሳሳታለህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በሞኞች አይደሰትም፤ ለእግዚአብሔር አንድ ነገር ለመስጠት በተሳልክ ጊዜ ወዲያውኑ የተሳልከውን ለመፈጸም ዝግጁ ሁን፤ ተስለህ የማትፈጽመው ከሆነ ግን ቀድሞውንም ባትሳል የተሻለ ነው። ወደ ኃጢአት እንዳይመራህ ለአንደበትህ ከገደብ ያለፈ ነጻነት አትስጠው፤ በዚህ ዐይነት “ይህን የተናገርኩት ሳላውቅ ነው” ብለህ በእግዚአብሔር አገልጋይ ፊት ይቅርታ ከመጠየቅ ትድናለህ፤ አለበለዚያ ግን የደከምክበትን ያጠፋ ዘንድ የእግዚአብሔርን ቊጣ በገዛ እጅህ እንደ መጋበዝ ይሆንብሃል። ብዙ ሕልምና ብዙ ልፍለፋ ከንቱ ነው፤ ከዚህስ ይልቅ እግዚአብሔርን ፍራ።