ኦሪት ዘዳግም 31
31
የኢያሱ በሙሴ እግር መተካት
1ሙሴም ይህን ሁሉ ቃል ለእስራኤል ሕዝብ ተናግሮ ከፈጸመ በኋላ፥ 2እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ፥ የእኔ ዕድሜ መቶ ኻያ ዓመት ስለ ሆነ ከእንግዲህ ወዲህ እናንተን መምራት አይቻለኝም፤ ከዚህም በላይ እኔ ዮርዳኖስን እንደማልሻገር እግዚአብሔር ነግሮኛል፤ #ዘኍ. 20፥12። 3አምላካችሁ እግዚአብሔር በፊታችሁ እየሄደ ይመራችኋል፤ በዚያ የሚኖሩትንም ሕዝቦች ደምስሶ ምድራቸውን ትወርሳላችሁ፤ እግዚአብሔር በተናገረውም መሠረት ኢያሱ መሪያችሁ ይሆናል። 4እግዚአብሔር የአሞራውያንን ነገሥታት ሲሖንንና ዖግን ድል ነሥቶ አገራቸውን እንዳጠፋ ሁሉ በእነርሱም ላይ እንዲሁ ያደርጋል። #ዘኍ. 21፥21-35። 5እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ድልን ያጐናጽፋችኋል፤ ስለዚህ ልክ እኔ ያዘዝኳችሁን ትእዛዝ በእነርሱ ላይ ትፈጽማላችሁ። 6ቈራጥነትና ድፍረት ይኑራችሁ፤ ከእነርሱም የተነሣ ከቶ አትፍሩ፤ አትደንግጡም፤ ራሱ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ነው፤ አይጥላችሁም፤ አይተዋችሁም።”
7ከዚህም በኋላ ሙሴ ኢያሱን ጠርቶ በእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ፊት እንዲህ አለው፤ “በርታ ድፍረትም ይኑርህ፤ እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶቻቸው በመሐላ ቃል በገባላቸው መሠረት ምድሪቱን ይወርሱ ዘንድ ሕዝቡን መርተህ የምታስገባ አንተ ነህ፤ 8ራሱ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር በመሆን ይመራሃል፤ አይጥልህም ከቶም አይተውህም፤ ስለዚህ አትፍራ፤ ተስፋም አትቊረጥ።” #ኢያሱ 1፥5፤ ዕብ. 13፥5።
ሕጉ በየሰባት ዓመት መነበብ እንዳለበት
9ከዚያ በኋላ ሙሴ የእግዚአብሔርን ሕግ ጽፎ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት አገልጋዮች ለሆኑት ለሌዋውያን ካህናትና ለእስራኤል ሕዝብ አለቆች ሰጣቸው። 10እነርሱንም እንዲህ ሲል አዘዘ፤ “ዕዳ ሁሉ በሚሰረዝበት በየሰባቱ ዓመት መጨረሻ ላይ በሚከበረው የዳስ በዓል፥ #ዘዳ. 15፥1፤ 16፥13-15። 11እስራኤላውያን ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት እርሱ በሚመርጠው ቦታ በሚሰበሰቡበት ጊዜ ይህን ሕግ በፊታቸው አንብብ። 12ሁሉም ሰምተውት አምላካችሁን እግዚአብሔርን መፍራት እንዲማሩና የዚህን ሕግ ቃላት ሁሉ በጥንቃቄ እንዲጠብቁ ወንዶችንም፥ ሴቶችንም፥ ልጆችንም፥ በከተሞቻችሁ የሚኖሩ መጻተኞችንም በአንድነት ሰብስቡ። 13በዚህም ዐይነት የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ሕግ ሰምተው የማያውቁ ዘሮቻችሁ ሁሉ ሊያዳምጡት ይችላሉ፤ ስለዚህም ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ በምትወርሱአት ምድር በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ ለእግዚአብሔር መታዘዝን ይማራሉ።”
እግዚአብሔር ለሙሴና ለኢያሱ የሰጣቸው መመሪያ
14ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “አንተ የመሞቻህ ጊዜ ደርሶአል፤ የሚመራበትን ትእዛዝ እሰጠው ዘንድ ኢያሱን ጠርተህ አንተና እርሱ ወደ መገናኛው ድንኳን ቅረቡ፤” ሙሴና ኢያሱም አብረው ወደ መገናኛው ድንኳን ቀረቡ፤ 15እግዚአብሔርም በድንኳኑ ደጃፍ በቆመ በደመና ዐምድ ተገለጠላቸው።
16እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አንተ በቅርብ ጊዜ እንደ ቀድሞ አባቶችህ ትሞታለህ፤ ከዚያ በኋላ ይህ ሕዝብ ከእርሱ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን ያፈርሳል። እኔንም በመተው በሚወርሰው ምድር የሚገኙትን ጣዖቶች ያመልካል። 17ይህም በሚሆንበት ጊዜ እኔ በእነርሱ ላይ ተቈጥቼ እለያቸዋለሁ፤ ፊቴን ከእነርሱ እሰውራለሁ፤ እነርሱም ይደመሰሳሉ፤ በእነርሱም ላይ ብዙ አሠቃቂ መቅሠፍት ይመጣባቸዋል፤ በዚያን ጊዜ፥ ‘ይህ ችግር የመጣብን አምላካችን በመካከላችን ስለሌለ አይደለምን?’ ይላሉ። 18ባዕዳን አማልክትን በማምለክ በሠሩት ኃጢአት እኔ በዚያ ጊዜ ፈጽሞ አልረዳቸውም።
19“ይህን መዝሙር ጽፈህ ለእስራኤላውያን አስተምራቸውና እንዲዘምሩት አድርግ፤ ይህም መዝሙር በእነርሱ ላይ ማስረጃ ይሆንልኛል። 20ለቀድሞ አባቶቻቸው በመሐላ ቃል ኪዳን በገባሁላቸው መሠረት በማርና በወተት ወደ በለጸገችው ምድር አስገባቸዋለሁ፤ በዚያም በልተው በጠገቡና በወፈሩ ጊዜ እኔን ይተዋሉ፤ ቃል ኪዳኔንም አፍርሰው ሌሎች አማልክትን ያመልካሉ። 21ብዙ ከባድ ችግሮች ሲደርሱባቸው ይህ በልጆቻቸው የማይረሳ መዝሙር ሲዘመር ምስክር ይሆንባቸዋል። በመሐላ ቃል ወደገባሁላቸው ምድር ከማስገባቴ በፊት አሁን እንኳ ምን ዐይነት ዝንባሌ እንዳላቸው ዐውቃለሁ።”
22በዚያኑ ዕለት ሙሴ መዝሙሩን ጽፎ ለእስራኤል ሕዝብ አስተማረ።
23ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር የነዌን ልጅ ኢያሱን እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “በርታ ደፋርም ሁን፤ እኔ ልሰጣቸው በመሐላ ቃል ወደገባሁላቸው ምድር የእስራኤልን ሕዝብ መርተህ ታገባለህ፤ እኔም ከአንተ ጋር እሆናለሁ።” #ዘኍ. 27፥23፤ ኢያሱ 1፥6።
24ሙሴም የዚህን ሕግ ቃላት እስከ መጨረሻ በመጽሐፍ ጽፎ ከጨረሰ በኋላ፥ 25የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት የሚሸከሙትን ሌዋውያንን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፤ 26“የእግዚአብሔር ሕግ የተጻፈበትን ይህን መጽሐፍ ወስዳችሁ፥ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት አጠገብ አኑሩት፤ በዚህም ዐይነት በሕዝቡ ላይ ምስክር ይሆንባቸዋል። 27የእስራኤል ሕዝብ ምን ያኽል ዐመፀኞችና አንገተ ደንዳኖች እንደ ሆኑ ዐውቃለሁ፤ በእኔ ሕይወት ዘመን ከእነርሱ ጋር ሳለሁ እንኳ በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፁ ናቸው፤ ከሞትሁ በኋላማ ከዚህ ይበልጥ ያምፃሉ፤ 28ስለዚህም ይህን ሁሉ እነግራቸው ዘንድ የነገድ መሪዎቻችሁንና የሕዝብ አለቆችን ሰብስቡልኝ፤ እኔ ሰማይንና ምድርን በእነርሱ ላይ ምስክሮች አድርጌ እጠራለሁ። 29እኔ ከሞትሁ በኋላ ካዘዝኳቸው ትእዛዝ በመውጣት የርኲሰትን ሥራ እንደሚፈጽሙ ዐውቃለሁ፤ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ በመሥራት ስለሚያስቈጡት መቅሠፍት ያመጣባቸዋል።”
የሙሴ መዝሙር
30ከዚህ በኋላ ሙሴ በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት የዚህን መዝሙር ቃሎች ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ አነበበ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 31: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997