ኦሪት ዘዳግም 25
25
1“ሁለት ሰዎች ተጣልተው ክርክር በማንሣት ወደ ፍርድ አደባባይ ቢመጡ ተገፊውን ነጻ፥ ገፊውን ግን በደለኛ አድርገው ይፍረዱ፤ 2በደል የፈጸመው ሰው በግርፋት እንዲቀጣ ቢያስፈልግ፥ በደረቱ መሬት ላይ አስተኝተው ጀርባውን እንዲገርፉት ዳኛው ይዘዝ፤ የሚገረፈውም ዳኛው ባለበትና የግርፋቱም ቊጥር የሚወሰነው ወንጀለኛው በሠራው በደል መጠን ይሆናል። 3እስከ አርባ ጅራፍ ሊገርፈው ይችላል፤ ከአርባ ግን መብለጥ የለበትም፤ ከዚያ በላይ ቢገረፍ ወገንህ በፊትህ የተዋረደ ይሆናል። #2ቆሮ. 11፥24።
4“እህል በምታበራይበት ጊዜ የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር። #1ቆሮ. 9፥9፤ 1ጢሞ. 5፥18።
ልጅ ሳይወልድ ለሞተ ሰው ወንድም ሊፈጽምለት የሚገባ ተግባር
5“ወንድማማቾች በአንድ ርስት ላይ ቢኖሩና አንደኛው ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፥ የሟቹ ሚስት ከቤተሰብ ውጪ የሆነ ሌላ ሰው ማግባት አይኖርባትም፤ የባልዋ ወንድም እርስዋን በማግባት የዋርሳነት ግዴታውን ይፈጽምላት። 6ይህም በሚሆንበት ጊዜ በመጀመሪያ የሚወለደው ወንድ ልጅ በሟቹ ስም ይጠራ፤ በዚህም ዐይነት በእስራኤል የሟቹ የትውልድ ሐረግ ሳይጠፋ መቀጠል ይችላል። #ማቴ. 22፥24፤ ማር. 12፥19፤ ሉቃ. 20፥28። 7ነገር ግን የሟቹ ወንድም እርስዋን ለማግባት ባይፈልግ፥ ወደ ከተማይቱ መሪዎች ዘንድ ሄዳ ‘የባሌ ወንድም ግዴታውን ለመፈጸም ፈቃደኛ አልሆነም፤ ለሟቹ ወንድም በእስራኤል ሕዝብ መካከል ዘር ለመተካት ፈቃደኛ አልሆነም’ በማለት ታስረዳ፤ 8ከዚህ በኋላ የከተማይቱ መሪዎች ሰውየውን ጠርተው ያነጋግሩት፤ አሁንም እርስዋን ለማግባት ፈቃደኛ ባይሆን 9የሟቹ ሚስት በከተማይቱ መሪዎች ፊት ወደ እርሱ ትቅረብ፤ ከእግሩ ጫማዎች አንዱን አውልቃ ምራቋን በፊቱ ላይ በመትፋት ‘ለወንድሙ ዘር ለመተካት እምቢ ለሚል ሰው ይህን ዐይነት አሳፋሪ ነገር ሊፈጸምበት ይገባል’ ትበል። 10የዚያም ሰው ቤተሰብ በእስራኤል ‘ጫማው የወለቀበት ሰው ቤተሰብ’ እየተባለ በመነቀፍ ሲጠራ ይኖራል። #ሩት 4፥7-8።
ሌሎች ትእዛዞች
11“ሁለት ሰዎች ተጣልተው በሚተናነቁበት ጊዜ የአንደኛው ሚስት ባልዋን ለማገዝ የሌላውን ሰው ብልት ብትጨብጥ፥ 12ምሕረት ሳይደረግላት እጅዋ ይቈረጥ።
13-14“ትልቅና ትንሽ ሚዛን ወይም መስፈሪያ በመያዝ ሰውን አታጭበርብር። 15እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ለረጅም ዘመን ትኖር ዘንድ እውነተኛና ታማኝ የሆነ ሚዛንና መስፈሪያ ብቻ ይኑርህ፤ 16እግዚአብሔር አምላክህ እንደዚህ አድርገው በማጭበርበር ተንኰል የሚሠሩትን ሰዎች ሁሉ ይጠላል። #ዘሌ. 19፥35-36።
ዐማሌቃውያንን ስለ መደምሰስ የተሰጠ ትእዛዝ
17“አንተ ከግብጽ በወጣህበት ጊዜ ዐማሌቃውያን የፈጸሙብህን በደል አትርሳ፤ 18እነርሱ እግዚአብሔርን የሚፈሩ አይደሉም፤ አንተ በጒዞ ላይ ደክሞህ በነበረ ጊዜ በኋላ በኩል አደጋ ጣሉብህ፤ ደክመው ወደ ኋላ ያዘግሙ የነበሩትንም ሁሉ ገደሉ። 19ስለዚህም እግዚአብሔር አምላክህ ምድሪቱን አውርሶህ በዙሪያህ ከሚኖሩ ጠላቶችህ ሁሉ በሚያሳርፍህ ጊዜ በምድር ላይ ማንም የሚያስታውሳቸው እስኪጠፋ ድረስ ዐማሌቃውያንን ሁሉ ደምስስ! ይህን ከቶ አትርሳ! #ዘፀ. 17፥8-14፤ 1ሳሙ. 15፥2-9።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 25: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997