የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘዳግም 22

22
1“የእስራኤላዊ ወገንህ ንብረት የሆነ በሬ ወይም በግ ጠፍቶ ሲባዝን ብታገኝ ዝም ብለህ አትለፈው፤ ወደ ባለቤቱ መልሰህ ውሰድለት፤ 2ነገር ግን ባለቤቱ የሚኖርበት ቦታ ሩቅ ቢሆን፥ ወይም ባለቤቱ ማን እንደ ሆነ ካላወቅህ እንስሳውን ወደ ቤትህ ውሰደው፤ እርሱን ሊፈልግ በሚመጣበት ጊዜ ለባለቤቱ ስጠው፤ 3እንዲሁም አህያም ሆነ ልብስ ወይም ማንኛውንም ሌላ ነገር ከእስራኤላዊ ወገንህ ጠፍቶ ብታገኝ ችላ ሳትል መልሰህ ስጠው።
4“የእስራኤላዊ ወገንህ አህያ ወይም በሬ መንገድ ላይ ወድቆ ብታይ ዝም ብለህ አትለፍ፤ ቆሞ እንዲሄድ እንስሳውን በማንሣት እርዳው። #ዘፀ. 23፥4-5።
5“እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደዚህ የሚያደርጉትን ስለሚጠላ ሴቶች የወንዶችን፥ ወንዶችም የሴቶችን ልብስ አይልበሱ።
6“አንዲት ወፍ በዛፍ ወይም በመሬት ላይ ጫጩቶችዋንም ሆነ እንቊላሎችዋን ዐቅፋ የተቀመጠችበትን ጎጆ ብታገኝ፥ እናቲቱን ወፍ ከነጫጩቶችዋ አትውሰድ፤ 7ጫጩቶቹን መውሰድ ትችላለህ፤ እናቲቱን ወፍ ግን እንድትበር ልቀቃት፤ ይህን ብታደርግ ሀብታም ሆነህ ለረጅም ዘመን ትኖራለህ።
8“አዲስ ቤት በምትሠራበት ጊዜ በጣራው ክፈፍ ዙሪያ መከታ አድርግለት፤ አለበለዚያ አንድ ሰው ከጣራው ላይ ቢወድቅ ለደሙ ተጠያቂ ትሆናለህ።
9“በወይን ተክልህ ውስጥ ሌላ ዘር አትዝራ፤ ይህን ብታደርግ በወይኑ ፍሬም ሆነ በሌላው ሰብል መጠቀም አትችልም። #ዘሌ. 19፥19።
10“በሬንና አህያን በአንድ ቀንበር ጠምደህ አትረስ።
11“ሱፍና በፍታ ተቀላቅሎ አብሮ የተሠራ ልብስ አትልበስ።
12“በልብስህ ላይ በአራቱም ማእዘን ዘርፍ አብጅለት። #ዘኍ. 15፥37-41።
የጋብቻ ግንኙነትን በንጽሕና ስለ መጠበቅ
13“አንድ ሰው ሚስት ካገባ በኋላ ቢጠላትና፥ 14‘ይህችን ሴት አግብቼ ክብረ ንጽሕናዋን አላገኘሁም’ ብሎ በሐሰት ክስ ስምዋን ቢያጠፋ፥ 15የልጅትዋ ወላጆች ልጅቱ ድንግል መሆንዋን የሚያረጋግጥላትን ማስረጃ አምጥተው በከተማይቱ ሸንጎ ለሚገኙት መሪዎች ያሳዩ። 16የልጅቱም አባት እንዲህ ብሎ ያስረዳ፦ ‘እኔ ሴት ልጄን ለዚህ ሰው ድሬለት ነበር፤ እነሆ፥ አሁን እርሱ የጠላት መሆኑን ገልጦአል። 17የልጅህን ድንግልና የሚያመለክት ማስረጃ አላገኘሁም ብሎ የልጄን ስም አጐደፈ፤ ለልጄ የድንግልናዋ ማረጋገጫ ምልክት ይኸውና!’ በማለት በመሪዎቹ ፊት የማስረጃውን ሻሽ ይዘርጋ። 18የከተማይቱም መሪዎች ባልየውን ወስደው በመግረፍ ይቅጡት። 19በተጨማሪም አንድ መቶ ጥሬ ብር መቀጫ አስከፍለው ገንዘቡን ለልጅትዋ አባት ይስጡት፤ ያ ሰው ድንግል የሆነችውን የአንዲት እስራኤላዊት ልጃገረድ ስም አጒድፎአል፤ ከዚህም በቀር የእርሱ ሚስት ሆና ትኖራለች፤ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ሊፈታት አይገባም።
20“ነገር ግን ክሱ እውነት ሆኖ ቢገኝና ድንግል ስለ መሆንዋ የሚያስረዳ ነገር ባይኖር፥ 21በአባትዋ ቤት እያለች አሳፋሪ የሆነውን የዝሙት ሥራ በእስራኤል መካከል ስለ ሠራች ወደ አባትዋ ቤት ደጃፍ ይውሰዱአት፤ በዚያም እርስዋ የምትኖርበት ከተማ ሰዎች በድንጋይ ወግረው ይግደሉአት፤ በዚህም ዐይነት ይህን ክፉ ነገር ከመካከላችሁ አስወግዱ።
22“አንድ ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ተኝቶ ቢገኝ ሁለቱም ይገደሉ። በዚህም ዐይነት ይህን ክፉ ነገር ከእስራኤል አስወግዱ።
23“አንድ ሰው በአንዲት ከተማ ለሌላ ሰው ከታጨች ድንግል ጋር ተኝቶ ቢገኝ፥ 24ሁለቱንም ከከተማይቱ ወደ ውጪ አውጥታችሁ በድንጋይ ወግራችሁ ግደሉ፤ ልጃገረዲቱ መሞት የሚገባት ሰው ሊሰማ በሚችልበት ከተማ ውስጥ እያለች ርዳታ እንዲደረግላት የጩኸት ድምፅ ባለማሰማትዋ ነው፤ ሰውየውም የሚሞትበት ምክንያት ለሌላ ሰው ከታጨች ልጃገረድ ጋር በመተኛት ሕግን በማፍረሱ ነው፤ በዚህ ዐይነት ይህን ክፉ ነገር ከመካከላችሁ አስወግዱ።
25“አንድ ሰው ለሌላ ሰው የታጨችውን ልጃገረድ ከከተማዋ ውጪ በዋለችበት አግኝቶ በመድፈር ድንግልናዋን ቢገሥ ብቻውን ይገደል። 26እርስዋ ለሞት የሚያበቃ በደል ስላልፈጸመች በልጃገረዲቱ ላይ ምንም ነገር አይድረስባት፤ ይህ ፍሬ ነገር አንድ ሰው በሌላ ሰው ላይ አደጋ ጥሎ በመግደል የሚፈጽመውን ወንጀል ይመስላል። 27ይህም የሚሆንበት ምክንያት ያ ሰው ያቺን ለሌላ ሰው ታጭታ የነበረች ልጃገረድ ከከተማ ውጪ በዋለችበት አግኝቶአት ስለ ነበርና ርዳታ ለማግኘት ብትጮኽም የሚደርስላት በማጣትዋ ነው።
28“አንድ ሰው ለሌላ ሰው ያልታጨችውን ልጃገረድ አግኝቶ በመውሰድ ሲደርስባት ቢያዝ፥ 29ለልጃገረዲቱ አባት ኀምሳ ጥሬ ብር ይክፈል፤ እርስዋም ለዚያ ሰው ሚስት ሆና ትኑር፤ አስገድዶ በመድፈር ከእርስዋ ጋር ስለ ተኛ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ሊፈታት አይችልም። #ዘፀ. 22፥16-17።
30“ማንም ሰው የአባቱ ሚስት ከሆነችው ከማንኛይቱም ሴት ጋር ግንኙነት በማድረግ አባቱን አያሳፍር። #ዘሌ. 18፥8፤ 20፥11፤ ዘዳ. 27፥20።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ