የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘዳግም 17

17
1“ከከብት ወይም ከበግ መንጋዎች መካከል አንዳች ነውር ያለበትን እንስሳ ለእግዚአብሔር ለአምላክህ መሥዋዕት አድርገህ አታቅርብ፤ ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነው።
2“እግዚአብሔር አምላክህ ከሚሰጥህ ከተሞች በአንድዋ የሚገኝ ወንድ ወይም ሴት በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር አድርጎ ቃል ኪዳኑን ያፈርስ ይሆናል፤ 3እንዲሁም እኔ የከለከልኳቸውን፦ ፀሐይን፥ ጨረቃን፥ ከዋክብትን ያመልክ ይሆናል፤ #ዘፀ. 22፥20። 4እንዲህ ያለውን ወሬ በምትሰማበት ጊዜ በጥብቅ መርምር፤ እንደዚህ ያለውም ክፉ ነገር በእስራኤል መደረጉ እርግጠኛ ሆኖ ከተገኘ፥ 5ያን ሰው ወይም ያቺን ሴት ከከተማ ወደ ውጪ አውጥተህ በድንጋይ ወግረህ ግደል። 6ሆኖም በዚህ ሁኔታ በሞት መቀጣት የሚገባው ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች በእርሱ ላይ ከመሰከሩበት በኋላ ነው፤ ምስክሩ አንድ ብቻ ከሆነ ግን ያ ሰው አይገደል። #ዘኍ. 35፥30፤ ዘዳ. 19፥15፤ ማቴ. 18፥16፤ 2ቆሮ. 13፥1፤ 1ጢሞ. 5፥19፤ ዕብ. 10፥28። 7ምስክሮቹ የመጀመሪያዎቹን ድንጋዮች ይወርውሩ፤ ከዚያም ቀጥሎ ሌላው ሕዝብ በድንጋይ ይውገረው፤ በዚህም ዐይነት እንደዚህ ያለውን ክፉ ነገር ሁሉ ከመካከልህ ታስወግዳለህ። #1ቆሮ. 5፥13።
አስቸጋሪ የፍርድ ጉዳዮች
8“በደም ማፍሰስ፥ በሰብአዊ መብት፥ በግድያ ወይም እነዚህን በመሳሰሉ ጉዳዮች በከተሞችህ በሚነሡ ክርክሮች የፍርድ አሰጣጡ አስቸጋሪ ቢሆንብህ አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚመርጠው ቦታ ፈጥነህ በመሄድ 9ከሌዋውያን ወገን ካህናት ለሆኑትና በዚያን ጊዜ ዳኛ ለሆነው ጉዳዩን አቅርብ፤ ጉዳዩንም እነርሱ ይወስኑ። 10እግዚአብሔር በሚመርጠው ቦታ ሆነው የሚሰጡህን ውሳኔ በትክክል እሥራ ላይ አውል፤ እነርሱም የሚነግሩህን በጥንቃቄ ጠብቅ። 11በሚሰጡአችሁ መመሪያና ሕግ መሠረት ሁሉን አድርጉ፤ ከዚያም ወደ ግራ ወይም ወደ ቀኝ ፈቀቅ አትበሉ። 12ዳኛውን ወይም አምላክህን እግዚአብሔርን በማገልገል ላይ ያለውን ካህን ባለመታዘዝ የሚዳፈር ሰው ቢኖር በሞት ይቀጣ። በዚህም ዐይነት እንደዚህ ያለውን ክፉ ነገር ሁሉ ከእስራኤል ታስወግዳለህ። 13ከዚያን በኋላ ሰው ሁሉ ይህን ሰምቶ ይፈራል፤ ይህንንም የመሰለ ክፉ ነገር ለመፈጸም የሚዳፈር አይኖርም።
ስለ ንጉሥ የተሰጠ መመሪያ
14“እግዚአብሔር አምላክህ ወደሚሰጥህ ምድር በመግባት ምድሩን ወርሰህ ከተደላደልክ በኋላ በዙሪያዬ እንዳሉት ሕዝቦች ንጉሥ ላንግሥ ብትል፥ #1ሳሙ. 8፥5። 15እግዚአብሔር አምላክህ የሚመርጥልህን ንጉሥ ልታነግሥ ትችላለህ፤ በአንተም ላይ የምታነግሠው ንጉሥ ከወገንህ መካከል ይሁን፥ ከወገንህ ያልሆነውን የውጪ አገር ሰው ልታነግሥ አይገባህም። 16ያም ንጉሥ ለሠራዊቱ ብዙ ፈረሶች ያሉት መሆን የለበትም፤ እግዚአብሔር ሕዝቡ ወደ ግብጽ እንዳይመለሱ ስለ አዘዘ ፈረሶችን ለመግዛት ወደ እዚያ ሰዎችን አይላክ። #1ነገ. 10፥28፤ 2ዜ.መ. 1፥16፤ 9፥28። 17ደግሞም ንጉሡ ብዙ ሚስቶች እንዲኖሩት ማድረግ እግዚአብሔርን ከመከተል ስለሚገታው ንጉሡ ብዙ ሚስቶች እንዲኖሩት አያስፈልገውም፤ ወርቅና ብርም በብዛት አያከማች። #1ነገ. 10፥14-22፤27፤ 11፥1-8፤ 2ዜ.መ. 1፥15፤ 9፥27። 18ይልቅስ ንጉሥ በሚሆንበት ጊዜ እነዚህ በሌዋውያን ካህናት ተጠብቀው የሚኖሩት የእግዚአብሔር ሕግጋት የተጻፉበትን መጽሐፍ አንድ ቅጅ እንዲኖረው ያድርግ። 19ይህን መጽሐፍ አጠገቡ በማኖር በዘመኑ ሁሉ ያንብበው፤ ይህንንም ቢያደርግ እግዚአብሔርን ማክበርና በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተጻፉትንም ሕጎችና ደንቦች በጥንቃቄና በታማኝነት መፈጸምን ይማራል። 20ራሱንም ከወገኖቹ ከእስራኤላውያን እበልጣለሁ ብሎ እንዳይታበይና ከእግዚአብሔርም ትእዛዞች እንዳይርቅ ይጠብቀዋል። ይህን ቢያደርግ ለብዙ ዘመን ይነግሣል፤ ልጆቹም በእስራኤል ላይ ለብዙ ዘመን ይነግሣሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ