የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘዳግም 16

16
የፋሲካ በዓል
(ዘፀ. 12፥1-20)
1“አንተን ከግብጽ ምድር ያወጣህ ከአቢብ ወር ውስጥ በአንዱ ሌሊት ስለ ሆነ በዚህ ወር የፋሲካን በዓል በማድረግ እግዚአብሔር አምላክህን አክብር። 2እግዚአብሔር አምላክህ ለስሙ መጠሪያ እንዲሆን በሚመርጠው ስፍራ እርሱን ለማክበር ከበጎችህና ከከብቶችህ መንጋዎች መርጠህ አንዳንድ ሠዋ፤ 3ያንንም ራት በምትመገብበት ጊዜ እርሾ የነካው እንጀራ አትብላ፤ በዚያ ዐይነት አስቸኳይ ሁኔታ ግብጽን ለቀህ በወጣህበት ጊዜ እንዳደረግኸው ሰባት ቀን ሙሉ እርሾ ያልነካው ቂጣ ትበላለህ፤ ይህን ቂጣ ብላ፤ እርሱም የሥቃይ እንጀራ ተብሎ ይጠራል፤ ይኸውም በምትኖርበት ዘመን ሁሉ ብዙ ሥቃይ ከተቀበልክበት ከግብጽ ምድር የወጣህበትን ቀን ታስታውሳለህ። 4እስከ ሰባት ቀን ድረስ በምድርህ በማንኛውም ሰው ቤት እርሾ አይገኝ፤ በመጀመሪያው ቀን ማታ ለመሥዋዕት የታረደው እንስሳ ሥጋው በሙሉ በዚያው ሌሊት ተበልቶ ማለቅ አለበት።
5“ለፋሲካ የተመደበውንም እንስሳ ማረድ የሚገባህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ምድር በማንኛውም ከተማ አይደለም። 6ነገር ግን የመሥዋዕቱን እንስሳ የምታርደው እግዚአብሔር አምላክህ ለስሙ መጠሪያ በመረጠው ስፍራ ብቻ ነው። ይኸውም ፀሐይ ስትጠልቅ ከግብጽ በወጣህበት ቀን የወጣህበትን ሰዓት በመጠበቅ ነው። 7ሥጋውን ቀቅለህ እግዚአብሔር አምላክህ በሚመርጠው ቦታ ብላው፤ በማግስቱ ወደ ድንኳኖችህ ተመለስ። 8በሚከተሉት ስድስት ቀኖች ደግሞ እርሾ ሳይነካው የተዘጋጀ ቂጣ ትበላለህ፤ በሰባተኛው ቀን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ትሰግድ ዘንድ ጉባኤ ይሁን፤ በዚያ ቀን ሥራ አትሥራበት።
የመከር በዓል
(ዘፀ. 34፥22ዘሌ. 23፥15-21) #ዘሌ. 23፥5-8ዘኍ. 28፥16-25
9“የእህል አጨዳ ከጀመርክበት ጊዜ አንሥቶ ሰባት ሳምንት ቊጠር፤ 10ከዚያም እግዚአብሔር አምላክህ በሰጠህ በረከት መጠን የበጎ ፈቃድ መሥዋዕትህን በማቅረብ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የመከር በዓል አድርግ። 11ከወንዶችና ከሴቶች ልጆችህ፥ ከወንዶችና ከሴቶች አገልጋዮችህ በከተሞችህ ከሚኖሩት ሌዋውያን፥ በአገርህ የሚኖሩ መጻተኞች፥ እናትና አባት ከሌላቸው ድኻ አደጎችና ባሎቻቸው ከሞቱባቸው ሴቶች ጋር በእግዚአብሔር ፊት እርሱ ለስሙ መጠሪያ እንዲሆን በመረጠው ቦታ በአንድነት ተሰብስበህ ደስ ይበልህ። 12እነዚህን ድንጋጌዎች በጥንቃቄ ጠብቅ፤ አንተም ቀድሞ በግብጽ ባሪያ እንደ ነበርክ አስታውስ። #ዘኍ. 28፥26-31።
የዳስ በዓል
(ዘሌ. 23፥33-43)
13“የእህልህን መከር ከሰበሰብክና የወይን ፍሬህን ከጨመቅህ በኋላ እስከ ሰባት ቀን ድረስ የዳስ በዓል ታከብራለህ፤ 14እርሱንም ከወንዶችና ከሴቶች ልጆችህ፥ ከወንዶችና ከሴቶች አገልጋዮችህ፥ በከተሞችህ ከሚኖሩት ሌዋውያን፥ በአገርህ ከሚኖሩ መጻተኞች፥ እናትና አባት ከሌላቸው ድኻ አደጎችና ባሎቻቸው ከሞቱባቸው ሴቶች ጋር አብረህ በመሆን ተደሰት። 15አምላክህ እግዚአብሔር በሚመርጠው ቦታ ለሰባት ቀን ለእርሱ በዓል ታደርጋለህ፤ እግዚአብሔር አምላክህ፥ በምርትህና በምታደርጋቸው ድርጊቶች ሁሉ ስለሚባርክህ በዓሉን በደስታ ታከብራለህ። #ዘኍ. 29፥12-38።
16“በዓመት ሦስት ጊዜ ወንዶች ሁሉ የፋሲካን፥ የመከርንና የዳስ በዓልን ለማክበር እግዚአብሔር አምላክህ በሚመርጠው ቦታ ይሰብሰቡ፤ በዓሉን ለማክበር በሚወጡበት ጊዜ ባዶ እጃቸውን አይምጡ፤ 17እያንዳንዱም የሚያመጣው ስጦታ እግዚአብሔር በሰጠው በረከት መጠን ይሁን።
የትክክለኛ ፍርድ አሰጣጥ ሁኔታ
18“አምላክህ እግዚአብሔር ለየነገድህ በሚሰጠው ምድር በእያንዳንዱ ከተማ ዳኞችና ሌሎችንም ባለሥልጣኖች ትሾማለህ፤ እነዚህም ሰዎች ለሕዝቡ ያለ አድልዎ መፍረድ ይገባቸዋል፤ 19ፍርድን አታጣምም፤ ፊት አይተህ አታድላ፤ አታታል፤ ጉቦ የጥበበኞችን ዐይን ስለሚያሳውርና የተጣመመ ፍርድ ስለሚያሰጥ ጉቦ አትቀበል። #ዘፀ. 23፥6-8፤ ዘሌ. 19፥15። 20እግዚአብሔር የሚሰጥህን ምድር ወርሰህ በሕይወት መኖር ትችል ዘንድ ሁልጊዜ ቅንና ትክክለኛ ሁን።
የተከለከሉ አምልኮዎች
21“ለአምላክህ ለእግዚአብሔር መሠዊያ በምትሠራበት አጠገብ የማምለኪያ ዐፀድ (ዛፍ) አትትከል። #ዘፀ. 34፥13። 22ደግሞም አምላክህ እግዚአብሔር የሚጠላውን የማምለኪያ የድንጋይ ምሰሶ አታቁም። #ዘሌ. 26፥1።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ