ኦሪት ዘዳግም 15
15
ዕዳ የሚሰረዝበት ዓመት
(ዘሌ. 25፥1-7)
1“ገንዘብ ያበደርካቸውን ሰዎች ሁሉ በየሰባተኛው ዓመት መጨረሻ ላይ ዕዳቸውን በመሰረዝ ትተውላቸዋለህ፤ 2አፈጻጸሙም እንደሚከተለው ነው፤ ለእስራኤላዊ ወገኑ ገንዘብ ያበደረ ሁሉ ያበደረውን ብድር ይሰርዝለት፤ እግዚአብሔር የዕዳ መሰረዣ ዓመት ነው ብሎ ያወጀበት ዓመት ስለ ሆነ ከእስራኤላዊ ወገኑ ያበደረውን ገንዘብ ለመቀበል አይፈልግ። 3ለውጪ አገር ሰው ያበደርከው ብድር እንዲመለስልህ መጠየቅ ትችላለህ፤ ለማንኛውም እስራኤላዊ ወገንህ ያበደርከው ገንዘብ ግን እንዲመለስልህ መጠየቅ የለብህም።
4-5“እኔ ዛሬ በማዝህ ትእዛዞች ሁሉ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ታዛዥ ሆነህ ብትገኝ፥ እግዚአብሔር አብዝቶ ስለሚባርክህ እርሱ በርስትነት በሚሰጥህ ምድር በመካከልህ ድኻ አይኖርም፤ 6እግዚአብሔር በሰጠው የተስፋ ቃል መሠረት ይባርክሃል፤ አንተ ለብዙ ሕዝቦች ገንዘብ ታበድራለህ፤ ነገር ግን ከእነርሱ ከማንኛውም ሰው አትበደርም፤ አንተ በብዙ ሕዝቦች ላይ የበላይነት ይኖርሃል፤ በአንተ ላይ ግን ማንም የበላይ አይሆንም።
7“አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ምድር በምትኖርባቸው ከተሞች ሁሉ አንድ እስራኤላዊ ችግረኛ ሆኖ ቢገኝ የገዛ ወገንህ ስለ ሆነ አትጨክንበት፤ ገንዘብህንም አትንፈገው። 8ይልቅስ እጅህን ዘርግተህ የሚያስፈልገውን ሁሉ አበድረው። #ዘሌ. 25፥35። 9የዕዳ መሰረዣ ሰባተኛ ዓመት ደርሶአል በማለት ችግረኛ ወገንህን ብድር አትከልክለው፤ እንዲህ ያለ ክፉ ሐሳብም ወደ ልብህ አይግባ፤ ብድር መስጠትን ብትከለክል ችግረኛው ወገንህ ወደ እግዚአብሔር ይጮኻል፤ ስለዚህ በአንተ ላይ እንደ በደል ይቈጠርብሃል። 10ይልቅስ ያለ ቅርታ በለጋሥነት ስጥ፤ ይህን ብታደርግ አምላክህ እግዚአብሔር በምትሠራው ሥራና በምታደርገው ድርጊት ሁሉ ይባርክሃል። 11መቼም ቢሆን በምድር ላይ ችግረኛና ድኻ መኖሩ ስለማይቀር በአገርህ ለሚገኙ ድኾችና ችግረኞች ጐረቤቶችህ እጅህን እንድትዘረጋ አዝሃለሁ። #ማቴ. 26፥11፤ ማር. 14፥7፤ ዮሐ. 12፥8።
ለባሮች ሊደረግላቸው የሚገባ አያያዝ
(ዘፀ. 21፥1-11)
12“ወንድም ሆነ ሴት ከእስራኤላውያን ወገን አንድ ሰው ራሱን ባሪያ አድርጎ ለአንተ ቢሸጥልህ፥ ከስድስት ዓመት አገልግሎት በኋላ በሰባተኛው ዓመት ነጻ ታወጣዋለህ፤ 13ነጻ በምታወጣው ጊዜ ባዶ እጁን አትስደደው፤ 14እግዚአብሔር አምላክህ ከሰጠህ በረከት፥ ማለት፥ ከበጎች፥ ከእህልና ከወይን በልግሥና ስጠው። 15አንተም በግብጽ ምድር ባሪያ እንደ ነበርክና እግዚአብሔር አምላክህ ነጻ ያወጣህ መሆኑን አስታውስ፤ እኔም ዛሬ ይህን ትእዛዝ የማዝህ በዚህ ምክንያት ነው።
16“ነገር ግን ባሪያህ አንተንና ቤተሰብህን በመውደዱና ከአንተም ጋር ስምምነት ስላለው ለመሄድ አይፈልግም ይሆናል፤ 17ይህም ከሆነ ወደ ቤትህ ደጃፍ ወስደህ ጆሮውን በወስፌ ብሳው፤ ከዚያም በኋላ እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ የአንተ ባሪያ ይሆናል፤ ለሴት ባሪያህም ቢሆን ይህንኑ አድርግ። 18እርሱንም ነጻ ባወጣኸው ጊዜ አንድ ተቀጣሪ ለስድስት ዓመት ከሚሰጥህ እጥፍ አገልግሎት ስለ ሰጠህ ቅር አይበልህ። እንግዲህ ይህን አድርግ፤ እግዚአብሔርም በምትሠራው ሁሉ ይባርክሃል። #ዘሌ. 25፥39-46።
የእንስሶች በኲር
19“ከከብትህ ወይም ከበግህ መንጋ የሚወለደውን ወንድ የሆነ በኲር ሁሉ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የተለየ እንዲሆን አድርግ፤ በኲር የሆኑትን በሬዎች ለማንኛውም ተግባር አትጠቀምባቸው፤ እንዲሁም ከበጎች መንጋ በኲሮችን ጠጒራቸውን አትሸልት፤ #ዘፀ. 13፥12። 20እነርሱንም እግዚአብሔር በሚመርጠው ቦታ በየዓመቱ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ከቤተሰብህ ጋር ትበላቸዋለህ። 21ነገር ግን እንስሶቹ እንከን ቢገኝባቸው ይኸውም ሽባ ወይም ዕውር ቢሆኑ፥ ወይም ደግሞ የባሰ ነውር ቢኖርባቸው፥ እነርሱን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርገህ አታቅርብ። 22እንደነዚህ ያሉትን እንስሶች በቤታችሁ መመገብ ትችላላችሁ፤ የነጻችሁ ወይም ያልነጻችሁ ብትሆኑም አጋዘንንና ድኲላን እንደምትበሉ ሁላችሁም እነዚህን ትበላላችሁ። 23ደማቸውን እንደ ምግብ አድርጋችሁ አትመገቡት፤ ነገር ግን ደሙን እንደ ውሃ በምድር ላይ አፍስሱት። #ዘፍ. 9፥4፤ ዘሌ. 7፥26-27፤ 17፥10-14፤ 19፥26፤ ዘዳ. 12፥16፤ 23።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 15: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997