ትንቢተ ዳንኤል 8:1-27

ትንቢተ ዳንኤል 8:1-27 አማ05

ብልጣሶር በነገሠ በሦስተኛው ዓመት እኔ ዳንኤል ከዚህ በፊት ካየሁት ሌላ ራእይ አየሁ፤ በዔላም አውራጃ በግንብ በታጠረው በሱሳ ከተማ ሆኜ ራሴን በራሴ በራእይ አየሁ፤ በኡላይ ወንዝ አጠገብም ቆሜ ነበር። በዚያም ወንዝ ዳር ሁለት ረጃጅም ቀንዶች ያሉት አንድ አውራ በግ ቆሞ ነበር፤ ከሁለቱ ቀንዶች አንደኛው ዘግይቶ የበቀለ ቢሆንም ከሌላው ቀንድ ይረዝም ነበር። ያም በግ በቀንዶቹ ለመጐሸም ወደ ምዕራብ፥ ወደ ሰሜን፥ ወደ ደቡብ ሲቃጣ አየሁ፤ በፊቱ ቀርቦ የሚቋቋመው ወይም ከኀይሉ ማምለጥ የሚችል አውሬ አልነበረም፤ የፈለገውን ሁሉ ያደርግ ነበር፤ ይበልጥም እየበረታ ሄደ። ይህንንም ራእይ በማሰላሰል ላይ ሳለሁ በዐይኖቹ መካከል ትልቅ ቀንድ ያለው አንድ አውራ ፍየል ምድርን አቋርጦ እግሮቹ መሬት ሳይነኩ ከምዕራብ በኩል እየበረረ መጣ። እርሱም በወንዙ አጠገብ ቆሞ ወዳየሁት ሁለት ቀንዶች ወዳሉት በግ በታላቅ ቊጣ ተንደርድሮ መጣበት። ወደ በጉም ሲጠጋ አየሁት፤ እርሱም በበጉ ላይ በመቈጣት መቶት ሁለት ቀንዶቹን ሰባበረበት፤ በጉም ለመቋቋም የሚያበቃው ኀይል አላገኘም፤ ስለዚህ ፍየሉ ወደ መሬት ጥሎ ረገጠው፤ ከኀይሉም ሊያድነው የሚችል አልነበረም። አውራው ፍየል እጅግ እየበረታ ሄደ፤ ከኀያልነቱም የተነሣ ታላቅ የነበረው ቀንዱ ተሰበረ፤ በቦታውም አራት ታላላቅ ቀንዶች ተተኩ፤ እያንዳንዱም ቀንድ ወደተለያየ አራት አቅጣጫ ያመለክት ነበር፤ ከነዚህ ከአራቱ ቀንዶች በአንደኛው ላይ ሌላ ትንሽ ቀንድ በቀለ፤ የዚህም የትንሽ ቀንድ ኀይል ወደ ደቡብና ወደ ምሥራቅ ወደ መልካሚቱ ምድር ተስፋፋ። ወደ ሰማይ ሠራዊት እስከሚደርስ ድረስ ከፍ አለ፤ እጅግ ብርቱ ሆነ፤ ከእነርሱም ጥቂቱን ወደ መሬት አውርዶ ረገጣቸው። የሰማይ ሠራዊትን አለቃ ሳይቀር ተፎካከረው፤ በየቀኑ ለእርሱ የሚቀርብለትን መሥዋዕት እንዲቀር አደረገ፤ መቅደሱንም አረከሰ። በክፋት ምክንያት ሠራዊቱና መደበኛው የሚቃጠል መሥዋዕት ለእርሱ ተሰጠ፤ እርሱም እውነትን ወደ መሬት ጣለ፤ የሚያደርገውም ነገር ሁሉ እየተሳካለት ሄደ። ከዚያ በኋላ አንድ ቅዱስ ሲናገር ሰማሁ፤ ሌላው ቅዱስ ደግሞ ለተናገረው ቅዱስ እንዲህ አለው፦ “እነዚህ በራእዩ የታዩት ነገሮች የሚፈጸሙበት ጊዜ መቼ ነው? ጥፋትን የሚያስከትለው ዐመፅና የዘወትርን መሥዋዕት ተክቶ የሚቈየው እስከ መቼ ነው? ቤተ መቅደሱና የሰማይ ሠራዊት ተላልፈው በመሰጠት ተረግጠው የሚቈዩትስ እስከ መቼ ነው?” የተጠየቀውም ቅዱስ “የጠዋትና የማታ መሥዋዕት የማይቀርብባቸው ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ቀኖች ይሆናሉ፤ ከዚያን በኋላ ቤተ መቅደሱ ይነጻል” ብሎ ሲመልስለት ሰማሁ። እኔ ዳንኤል የራእዩ ትርጒም ምን እንደ ሆነ በማሰላሰል ላይ ሳለሁ በድንገት አንድ ሰው የሚመስል አካል በፊቴ ቆመ። ከኡላይ ወንዝ ማዶ “ገብርኤል ሆይ! ይህ ሰው የራእዩን ትርጒም እንዲረዳው አድርግ!” የሚል የሰው ድምፅ ሰማሁ። ገብርኤልም መጥቶ በአጠገቤ በቆመ ጊዜ ደንግጬ ወደ መሬት ወደቅኹ። እርሱም “የሰው ልጅ ሆይ! ራእዩ የሚያመለክተው ስለ ዓለም መጨረሻ መሆኑን ተረዳ” አለኝ። እርሱም በሚናገርበት ጊዜ ኅሊናዬን ስቼ በግንባሬ ወደ መሬት ተደፋሁ፤ እርሱ ግን ዳሰሰኝና ከመሬት አንሥቶ በእግሮቼ አቆመኝ። እንዲህም አለኝ፦ “ራእዩ የሚያመለክተው ስለ ዓለም መጨረሻ ስለ ሆነ በቊጣ ቀን ምን እንደሚሆን አስረዳሃለሁ። “ሁለት ቀንዶች ያሉት አውራ በግ የሜዶንንና የፋርስን ነገሥታት ያመለክታል፤ አውራው ፍየል የሚያመለክተው የግሪክን ንጉሥ ነው፤ በዐይኖቹ መካከል ያለው ትልቅ ቀንድ ደግሞ የመጀመሪያውን የግሪክ ንጉሥ ያመለክታል። የመጀመሪያው ቀንድ ሲሰበር የወጡት አራት ቀንዶች ያ መንግሥት ለአራት መከፈሉን ያመለክታሉ፤ እያንዳንዱም መንግሥት የመጀመሪያውን መንግሥት ያኽል ብርቱ አለመሆኑን ይገልጣል። “የእነዚያ ነገሥታት ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ ሲደርስ ጨካኝና ተንኰለኛ የሆነ ንጉሥ ይነሣል። ይህም ንጉሥ እጅግ ብርቱ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ በራሱ ኀይል አይደለም፤ እጅግ አሠቃቂ የሆነ ጥፋት ይፈጽማል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል፤ በኃያላን ሰዎችና በተቀደሱት ሕዝብ ላይ ጥፋትን ያስከትላል። እጅግም ተንኰለኛ ስለ ሆነ በማታለል ይበለጽጋል፤ ራሱንም ከሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ ብዙ ሰዎችን ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ ይገድላል፤ የልዑላንን ልዑል እንኳ ይፈታተናል፤ በመጨረሻም እርሱ ራሱ ይጠፋል፤ የሚጠፋውም በሰው ኀይል አይደለም። ስለ ጠዋትና ስለ ማታ መሥዋዕት የተነገረው ራእይ እውነት ነው፤ አንተ ግን ይህ ራእይ የሚፈጸምበት ጊዜ ሩቅ ስለ ሆነ በምሥጢር ያዘው” አለኝ። እኔ ዳንኤል እጅግ ደከመኝና ሕመም ስለ ተሰማኝ ለብዙ ቀኖች ተኛሁ፤ ከዚያም በኋላ ተነሥቼ ንጉሡ በመደበልኝ ሥራ ላይ ተሰማራሁ፤ በራእዩ እጅግ ተጨነቅሁ፤ ላስተውለውም አልቻልኩም ነበር።