ከዕለታት አንድ ቀን ንጉሥ ብልጣሶር በሺህ ለሚቈጠሩ መኳንንት ታላቅ ግብዣ አደረገ፤ ከእነርሱ ጋር የወይን ጠጅ እየጠጣ ነበር። የወይን ጠጅ እየጠጡ ሳለ ብልጣሶር ሞቅ ባለው ጊዜ አባቱ ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ያመጣቸውን ከወርቅና ከብር የተሠሩ ጽዋዎችን እንዲያመጡ አገልጋዮቹን አዘዘ፤ ንጉሡ ይህን ያደረገው እርሱና መኳንንቱ፥ ሚስቶቹና ቁባቶቹ በእነዚያ የወርቅ ጽዋዎች እንዲጠጡባቸው ፈልጎ ነው። አገልጋዮቹም እነዚያን ከኢየሩሳሌም ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የተወሰዱትን የወርቅና የብር ጽዋዎች ወዲያውኑ አመጡ፤ ንጉሡና መኳንንቱ፥ ሚስቶቹና ቁባቶቹ በእነዚህ ጽዋዎች የወይን ጠጅ ጠጡ። እየጠጡም ከወርቅ፥ ከብር፥ ከነሐስ፥ ከብረት፥ ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩ አማልክትንም አመሰገኑ። የሰው እጅ ጣቶች በድንገት ታይተው በቤተ መቅደሱ መቅረዝ ፊት ለፊት ባለው በተለሰነው የቤተ መንግሥቱ ግድግዳ ላይ መጻፍ ጀመሩ፤ እነዚያም ጣቶች በሚጽፉበት ጊዜ ንጉሡ አየ። ወዲያውኑ ፊቱ ገረጣ፤ ከድንጋጤውም ብዛት የተነሣ ጒልበቱ ተብረከረከ፤ የሰውነቱ መገጣጠሚያዎች ከዱት። አስማተኞችን፥ ጠንቋዮችንና ኮከብ ቈጣሪዎችን እንዲያስገቡለት በከፍተኛ ድምፅ ትእዛዝ ሰጠ፤ እነርሱም ተጠርተው በመጡ ጊዜ ንጉሡ “ይህን ጽሕፈት አንብቦ ትርጒሙን ሊነግረኝ የሚችል ሰው፥ ሐምራዊ መጐናጸፊያ ይለብሳል፤ የወርቅ ኒሻንም ይደረግለታል፤ በመንግሥቴም ሥልጣን ሦስተኛውን ማዕርግ ይይዛል” አለ። ጥበበኞቹም ወደ ንጉሡ ቀረቡ፤ ነገር ግን ጽሑፉን ማንበብም ሆነ ትርጒሙን ለንጉሡ ማስረዳት የቻለ ከእነርሱ መካከል የተገኘ ማንም አልነበረም። ንጉሥ ብልጣሶር እጅግ ስለ ጨነቀው ፊቱ ይብሱን እየገረጣ ሄደ፤ መኳንንቱም ግራ ገብቶአቸው የሚያደርጉትን አጡ። ቀድሞ ንግሥት የነበረችው የንጉሡ እናት የንጉሡንና የመኳንንቱን ሁካታ ሰምታ ወደ ግብዣው አዳራሽ በመግባት እንዲህ አለች፦ “ንጉሥ ሆይ! ለዘለዓለም ኑር! በዚህ ጉዳይ ይህን ያኽል ልትጨነቅና ፊትህም ሊገረጣ አይገባም፤ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት አንድ ሰው በመንግሥትህ አለ፤ ይህ ሰው በአባትህ ዘመነ መንግሥት እንደ አማልክት የሆነ ዕውቀት፥ ጥበብና ማስተዋል የሞላበት ሆኖ ተገኝቶአል፤ በዚህም ምክንያት አባትህ ንጉሥ ናቡከደነፆር የጠንቋዮች፥ የአስማተኞች፥ የጠቢባንና የኮከብ ቈጣሪዎች ሁሉ አለቃ አድርጎ ሾሞት ነበር። እርሱ ሕልምን በመተርጐም፥ እንቆቅልሽን በመፍታትና የተሰወረውን ምሥጢር ገልጦ በማስረዳት ልዩ ችሎታ ያለው ጥበበኛና ብልኅ ሰው ነው፤ ስለዚህ ያንን አባትህ ናቡከደነፆር ‘ብልጣሶር’ ብሎ የሠየመውን ዳንኤልን አስጠራ፤ እርሱ ይህን ሁሉ ነገር ተርጒሞ ያስረዳሃል።” በዚያኑ ጊዜ ዳንኤል በንጉሡ ፊት ቀረበ፤ ንጉሡም እንዲህ አለው፦ “አባቴ ንጉሥ ናቡከደነፆር ማርኮ ካመጣቸው ከይሁዳ ስደተኞች መካከል አንዱ የሆንክ ዳንኤል አንተ ነህን? የቅዱሳን አማልክት መንፈስ በአንተ እንዳለና ብልኀት፥ ዕውቀትና ጥበብ የተሰጠህ መሆኑን ሰምቼአለሁ። እነሆ፥ ጠቢባን አማካሪዎቼና አስማተኞች ሁሉ ይህን ጽሕፈት አንብበው እንዲተረጒሙልኝ ተጠርተው ወደ እኔ መጥተው ነበር፤ ነገር ግን ተርጒመው ሊያስረዱኝ አልቻሉም፤ አንተ ግን የተሰወረውን ነገር የመተርጐምና አስቸጋሪ የሆነውን ነገር ሁሉ የመፍታት ችሎታ እንዳለህ ሰምቻለሁ፤ ስለዚህ ይህን ጽሕፈት አንብበህ ትርጒሙን ብትነግረኝ፥ ሐምራዊ መጐናጸፊያ እንድትለብስ፤ የወርቅ ኒሻን በአንገትህ እንድታደርግና በመንግሥቴም ሥልጣን ሦስተኛውን ማዕርግ እንድትይዝ አደርጋለሁ።” ዳንኤልም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ንጉሥ ሆይ! ስጦታው ለአንተ ይሁን፤ ሽልማቱንም ለሌላ ስጥ፤ ይሁን እንጂ ጽሕፈቱን አንብቤ ትርጒሙን እነግርሃለሁ። “ንጉሥ ሆይ! ልዑል እግዚአብሔር ለአባትህ ለናቡከደነፆር ንጉሥነትንና ታላቅነትን፥ ክብርንና ገናናነትን ሰጠው፤ ከገናናነቱም የተነሣ በልዩ ልዩ አገሮች የሚኖሩ ሕዝቦችና ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ነገዶች ሁሉ በፊቱ በፍርሃት ይንቀጠቀጡ ነበር፤ የፈለገውን መግደልና የፈለገውን ማዳን፥ የፈለገውን መሾምና ያልፈለገውን መሻር ይችል ነበር። ነገር ግን ትዕቢተኛ፥ እልኸኛና ጨካኝ ሆኖ በተገኘ ጊዜ ክብሩንና ማዕርጉን ተገፎ ከዙፋኑ ወረደ፤ ከሕዝብ መካከል ተባረረ፤ አእምሮውም ተለውጦ እንደ እንስሳ ሆነ፤ እንደ በሬም ሣር እየበላ ከሜዳ አህዮች ጋር ሆኖ ለመኖር ተገደደ፤ መጠለያ አጥቶ ሰውነቱ በሰማይ ጠል ረሰረሰ፤ ይህም የሆነው ልዑል እግዚአብሔር በመንግሥታት ሁሉ ላይ ሥልጣን እንዳለውና መንግሥትን ሁሉ ለፈለገው መስጠት እንደሚችል እስከሚረዳበት ጊዜ ድረስ ነበር። “አንተም ብልጣሶር የእርሱ ልጅ በመሆንህ ይህን ሁሉ ስታውቅ ራስህን ዝቅ በማድረግ ትሕትና አላሳየህም። ይልቁንም በሰማይ አምላክ ላይ በመታበይ ራስህን ከፍ ከፍ አደረግህ፤ ከቤተ መቅደሱ ተዘርፈው የመጡትን የወርቅ ዕቃዎች አስመጥተህ አንተና መኳንንቶችህ፥ ሚስቶችህና ቁባቶችህ የወይን ጠጅ መጠጫ አደረጋችኋቸው፤ ከጠጣችሁም በኋላ ማየት ወይም መስማት የማይችሉትንና ምንም ነገር የማያውቁትን ከወርቅ፥ ከብር፥ ከነሐስ፥ ከብረት፥ ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩትን አማልክት አመሰገናችሁ፤ መግደል ወይም ማዳን የሚችለውንና አካሄድህን የሚቈጣጠረውን ሕያው አምላክ ግን አላከበርከውም። እንግዲህ እግዚአብሔር በሰው እጅ ጣቶች ልኮ እነዚህን ቃላት እንዲጽፉ ያደረገው ስለዚህ ነው። “የጽሑፉም ንባብ ‘ማኔ! ማኔ! ቴቄል! ኡፋርሲን’ የሚል ነው። ትርጒሙም የሚከተለው ነው፤ ማኔ ‘እግዚአብሔር የመንግሥትህን ዘመን ቈጥሮ እንዲፈጸም አደረገው’ ማለት ነው። ቴቄል ‘በሚዛን ተመዝነህ፥ ቀለህ ተገኘህ’ ማለት ነው፤ ፋርስ ‘መንግሥትህ ተከፍሎ ለሜዶናውያንና ለፋርስ ሰዎች ተሰጠ’ ማለት ነው።” ከዚህም በኋላ ብልጣሶር ወዲያውኑ ዳንኤልን መጐናጸፊያ እንዲያለብሱት፥ የወርቅ ኒሻን በአንገቱ እንዲያደርጉለትና በመንግሥቱም ሥልጣን ሦስተኛውን ማዕርግ እንዲይዝ እንዲያደርጉት በዐዋጅ አዘዘ። በዚያኑ ሌሊት የባቢሎን ንጉሥ ብልጣሶር ተገደለ፤
ትንቢተ ዳንኤል 5 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ዳንኤል 5:1-30
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos