ትንቢተ ዳንኤል 3
3
ናቡከደነፆር ያቆመው የወርቅ ምስል
1ንጉሥ ናቡከደነፆር ቁመቱ ሥልሳ ክንድ፥ ወርዱ ስድስት ክንድ የሚያኽል ምስል ከወርቅ አሠራ፤ በባቢሎንም ግዛት በዱራ ሜዳ ላይ አቆመው። 2የቆመው ምስል በሚመረቅበት ክብረ በዓል ላይ እንዲገኙ አገረ ገዢዎችን መኳንንትን፥ ሹማምንትን፥ አማካሪዎችን፥ የግምጃ ቤት ኀላፊዎችን፥ ዳኞችን፥ ሌሎችንም የየክፍለ ሀገሩ ባለሥልጣኖችን አስጠራ። 3እነዚህ ሁሉ ባለሥልጣኖች ለምረቃው በዓል በአንድነት ተሰብስበው በምስሉ ፊት ለፊት ቆሙ፤ 4በዚያን ጊዜ አንድ ዐዋጅ ነጋሪ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፦ “እናንተ ከልዩ ልዩ ሀገር የመጣችሁ ሕዝቦችና ልዩ ልዩ ቋንቋ የምትናገሩ ነገዶች ሆይ! 5የመለከት የእንቢልታ የመሰንቆ የክራር፥ የበገና፥ የዋሽንት፥ የሙዚቃ ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ በምድር ላይ ተደፍታችሁ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል እንድትሰግዱ ታዛችኋል። 6በምድር ላይ ተደፍቶ የማይሰግድ ሰው ቢኖር በሚነደው የእሳት ነበልባል ውስጥ ወዲያውኑ ይጣላል።” 7ስለዚህ ወገኖች፥ ከልዩ ልዩ ሀገር የመጡ ሕዝቦችና ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ነገዶች ሁሉ የመለከትና፥ የእንቢልታ፥ የመሰንቆና፥ የክራር፥ የበገና፥ የዋሽንትና የሙዚቃ ሁሉ ድምፅ በሰሙ ጊዜ በመሬት ላይ ተደፍተው ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል ሰገዱ።
ሦስቱ የዳንኤል ጓደኞች ለወርቁ ምስል ባለመስገዳቸው እንደ ተከሰሱ
8በዚያን ጊዜ አንዳንድ የባቢሎን ጠቢባን ቀርበው አይሁድን ከሰሱ። 9ንጉሡን ናቡከደነፆርንም እንዲህ አሉት፦ “ንጉሥ ሆይ! ለዘለዓለም ኑር! 10ንጉሥ ሆይ! አንተ የመለከት፥ የእንቢልታ፥ የመሰንቆ፥ የክራር፥ የበገናና የዋሽንት፥ የሙዚቃ ሁሉ ድምፅ የሚሰማ ማናቸውም ሰው በመሬት ላይ ተደፍቶ ለወርቁ ምስል እንዲሰግድ ዐዋጅ አውጥተህ ነበር። 11በመሬት ላይ ተደፍቶ የማይሰግድ ሰው ቢኖር በሚነደው የእሳት ነበልባል ውስጥ እንዲጣል ትእዛዝ ሰጥተሃል። 12እነሆ፥ በባቢሎን አውራጃዎች ላይ ገዢዎች አድርገህ የሾምካቸው ሲድራቅ፥ ሚሳቅና አብደናጎ የተባሉ የአይሁድ ወገኖች የአንተን ትእዛዝ አይፈጽሙም፤ አማልክትህን አያመልኩም፤ ላቆምከውም ምስል አይሰግዱም።”
13ንጉሡ ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጥቶ ሲድራቅ፥ ሚሳቅና አብደናጎ እንዲጠሩ አዘዘ፤ እነርሱም መጥተው በንጉሡ ፊት ቀረቡ። 14ናቡከደነፆርም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ሲድራቅ፥ ሚሳቅና አብደናጎ! አማልክቴን አለማምለካችሁና ላቆምኩትም የወርቅ ምስል አለመስገዳችሁ እርግጥ ነውን? 15እንግዲህ የመለከት፥ የእንቢልታ፥ የመሰንቆ፥ የክራር፥ የበገና፥ የዋሽንትና፥ የሙዚቃም ሁሉ ድምፅ ስትሰሙ ላቆምኩት ምስል በመሬት ላይ ተደፍታችሁ ብትሰግዱ መልካም ነው፤ ባትሰግዱ ግን በሚነደው የእሳት ነበልባል ጒድጓድ ውስጥ ወዲያውኑ ትጣላላችሁ፤ ከእጄም የሚያድናችሁ አምላክ እንደሌለ ዕወቁ።”
16ሲድራቅ፥ ሚሳቅና አብደናጎም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “ንጉሥ ሆይ! በዚህ ጉዳይ ላይ ራሳችንን የምንከላከልበት መልስ ልንሰጥህ አያስፈልገንም። 17እኛ የምናገለግለው አምላክ ከዚህ ከሚነደው ከእሳት ነበልባልም ሆነ ከአንተ እጅ ሊያድነን ይችላል፤ 18ንጉሥ ሆይ! እርሱ ሊያድነን ፈቃዱ ባይሆን እንኳ አማልክትህን እንደማናመልክና ላቆምከውም የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ ዕወቅ።”
ሦስቱ የዳንኤል ጓደኞች በእሳቱ ነበልባል ውስጥ እንዲጣሉ የተፈረደባቸው መሆኑ
19በዚያን ጊዜ ናቡከደነፆር በሲድራቅ፥ በሚሳቅና በአብደናጎ ላይ እጅግ ተቈጥቶ መልኩ ተለዋወጠ፤ ስለዚህ እሳቱ ከቀድሞው ይበልጥ በሰባት እጥፍ ከፍ ብሎ እንዲነድ ትእዛዝ ሰጠ። 20ሦስቱንም ሰዎች አስረው ወደሚነደው የእሳት ነበልባል ጒድጓድ ውስጥ ይጥሉአቸው ዘንድ ከሠራዊቱ መካከል ብርቱ የሆኑትን አዘዘ። 21ስለዚህ ቀሚሳቸው፥ ሱሪያቸውና መጠምጠሚያቸው ሳይቀር ሙሉ ልብሳቸውን እንደ ለበሱ አስረው ወደሚነደው ወደ የእሳት ነበልባል ጒድጓድ ውስጥ ጣሉአቸው። 22ንጉሡ በሰጠው ጥብቅ ትእዛዝ መሠረት እሳቱ በኀይል ተቀጣጥሎ ይነድ ስለ ነበር ሲድራቅን፥ ሚሳቅንና አብደናጎን ወደ እሳቱ የጣሉአቸውን ሰዎች የእሳቱ ወላፈን አቃጥሎ ገደላቸው። 23ሦስቱ ሰዎች ግን በጥብቅ እንደ ታሰሩ በእሳቱ ነበልባል ላይ ወደቁ።
24ከዚያን በኋላ ንጉሡ ናቡከደነፆር በመደነቅ ፈጥኖ ተነሣና “አስረን በሚነደው የእሳት ነበልባል ውስጥ የጣልናቸው ሰዎች ሦስት ብቻ አልነበሩምን?” ሲል አማካሪዎቹን ጠየቀ። እነርሱም “አዎ፥ ንጉሥ ሆይ!” አሉት።
25ንጉሡም “እነሆ፥ እኔ እሳቱ ምንም ሳይጐዳቸው ከእስራት ተፈተው በነበልባሉ ውስጥ የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፤ አራተኛውም የአማልክትን ልጅ ይመስላል” አለ።
ሦስቱ ሰዎች ከእሳት ውስጥ ወጥተው መሾማቸው
26ናቡከደነፆር ወደሚነደው የእሳት ነበልባል ጒድጓድ ተጠግቶ “የልዑል አምላክ አገልጋዮች የሆናችሁ እናንተ ሲድራቅ፥ ሚሳቅና አብደናጎ ሆይ! ወጥታችሁ ወደዚህ ኑ!” በማለት ተጣራ፤ እነርሱም ከእሳቱ ወጡ። 27ከዚህ በኋላ አገረ ገዢዎቹ፥ መኳንንቱ፥ አማካሪዎቹ ሁሉ በእነርሱ ዙሪያ ተሰበሰቡ፤ እሳቱ ሰውነታቸውን እንዳልጐዳው፥ ከራስ ጠጒራቸውም አንዲቱን እንኳ እንዳላቃጠለ፥ የመጐናጸፊያቸው መልክ እንዳልተለወጠና ሌላው ቀርቶ የእሳቱ ሽታ እንኳ እንዳልደረሰባቸው ተመለከቱ።
28ከዚህም በኋላ ንጉሡ ናቡከደነፆር እንዲህ አለ፦ “የሲድራቅ፥ የሚሳቅና የአብደናጎ አምላክ የተመሰገነ ይሁን! እርሱ መልአኩን ልኮ እነዚህን አገልጋዮቹን አድኖአል፤ እነርሱ በአምላካቸው ተማምነው ለእርሱ ካልሆነ በቀር ለሌሎች አማልክት አንሰግድም በማለት የንጉሡን ትእዛዝ በማፍረስ ሕይወታቸውን በአደጋ ላይ ጥለውት ነበር።
29“እንደዚህ የሚታደግ ሌላ አምላክ የለም፤ ስለዚህ በአገሮች ሁሉ በሚኖሩና ልዩ ልዩ ቋንቋዎችን በሚናገሩ ሕዝቦች ሁሉ መካከል በሲድራቅ፥ በሚሳቅና በአብደናጎ አምላክ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ቢኖር ሰውነቱ ተቈራርጦ እንዲጣልና ቤቱም የፍርስራሽ ክምር እንዲሆን ዐውጃለሁ።”
30ይህንንም ካወጀ በኋላ ንጉሡ ሲድራቅን፥ ሚሳቅንና አብደናጎን በባቢሎን ግዛት ከፍ ከፍ አድርጎ ሾማቸው።
Currently Selected:
ትንቢተ ዳንኤል 3: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997