ኢዮአቄም በይሁዳ ላይ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ከበባት። እግዚአብሔር የይሁዳን ንጉሥ ኢዮአቄምንና የቤተ መቅደሱንም ንዋያተ ቅድሳት በከፊል ለናቡከደነፆር አሳልፎ ሰጣቸው፤ ንጉሡም ንዋያተ ቅድሳቱን በባቢሎን ባሉት የጣዖት አማልክቱ ቤተ መቅደስ ውስጥ አኖረ። ከዚህ በኋላ ንጉሥ ናቡከደነፆር አሽፈናዝ የተባለውን የባለሟሎቹን አለቃ ከእስራኤል ምርኮኞች መካከል የንጉሣዊ ቤተሰቦችና የመሳፍንት ልጆች ከሆኑት ወጣቶች መካከል ጥቂቶቹን መርጦ እንዲያመጣ አዘዘው፤ የሚመረጡትም ወጣቶች በቤተ መንግሥት ለማገልገል በቂ ችሎታ እንዲኖራቸው፥ መልከ መልካሞች፥ ጥበብን ሁሉ ማስተዋልና ሁሉን ነገር በፍጥነት መረዳት የሚችሉ፥ የአካል ጒድለት የሌለባቸው መሆን ይገባቸዋል፤ እንዲሁም የባቢሎናውያንን ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ያስተምራቸውም ዘንድ አዘዘው። ምግባቸውና የሚጠጡት የወይን ጠጅ ከንጉሡ ማእድ እንዲሆን ታዘዘላቸው፤ በዚህ ዐይነት ለሦስት ዓመት ከሠለጠኑ በኋላ በንጉሡ ፊት ቀርበው የቤተ መንግሥት ሥራቸውን እንዲጀምሩ ተወሰነ። ከተመረጡትም መካከል ነገዳቸው ከይሁዳ ወገን የሆነ ዳንኤል፥ ሐናንያ፥ ሚሳኤልና ዐዛርያ ነበሩ። የንጉሡም ባለሟሎች አለቃ ስማቸውን በመለወጥ ዳንኤልን ብልጣሶር፤ ሐናንያን ሲድራቅ፤ ሚሳኤልን ሚሳቅ፤ ዐዛርያን አብደናጎ ብሎ ጠራቸው። ዳንኤል ከንጉሡ ምግብ በመመገብና የወይን ጠጁንም በመጠጣት ራሱን ላለማርከስ ወሰነ፤ በዚህም ሐሳብ እንዲስማማለት አሽፈናዝን ለመነው። እግዚአብሔርም ለዳንኤል በሹሙ ፊት ሞገስን ሰጥቶ ልቡን አራራለት። ይሁን እንጂ ንጉሡን ስለ ፈራ አሽፈናዝ ዳንኤልን “ምግባችሁንና መጠጣችሁን ያዘዘ ንጉሡ ራሱ ነው፤ እናንተ ከሌሎቹ ወጣቶች ይልቅ ከስታችሁና ተጐሳቊላችሁ ብትገኙ ጌታዬ ንጉሡ በሞት ይቀጣኛል ብዬ እፈራለሁ” አለው። ከዚህ በኋላ ዳንኤል ራሱንና ጓደኞቹን ሐናንያን፥ ሚሳኤልንና አዛርያን እንዲጠብቅ አሽፈናዝ ወደ መደበው ጠባቂ ሄዶ እንዲህ አለው፤ “አትክልት እየተመገብንና ውሃ እየጠጣን እንድንቈይ በማድረግ እኛን አገልጋዮችህን ለዐሥር ቀን ያኽል ፈትነን፤ ከዚያ በኋላ የእኛን ሁኔታ ከቤተ መንግሥት የታዘዘውን ምግብ ከሚመገቡ ወጣቶች ጋር ታስተያየዋለህ፤ በምታገኘውም ግንዛቤ መሠረት እኛን አገልጋዮችህን በተመለከተ የመሰለህን ታደርጋለህ።” ጠባቂውም በዚህ ሐሳብ ተስማምቶ ለዐሥር ቀን ፈተናቸው። ዐሥሩም ቀን ከተፈጸመ በኋላ ከንጉሡ ምግብ ከሚመገቡት ወጣቶች ሁሉ ይልቅ እነርሱ ፊታቸው አምሮ፥ ሰውነታቸው ወፍሮ ተገኙ። ከዚያን ጊዜ አንሥቶ ጠባቂው ከቤተ መንግሥት የሚላክላቸውን ምርጥ ምግብና የወይን ጠጅ አስቀርቶ ለእነርሱ የአትክልት ምግብ ይሰጣቸው ጀመር። እግዚአብሔርም ለእነዚህ ለአራት ወጣቶች በማናቸውም ጥበብና ሥነ ጽሑፍ ዕውቀትና ማስተዋል ሰጣቸው፤ ዳንኤል ግን በተጨማሪ ራእይንና ሕልምን የመተርጐም ችሎታ ነበረው። ንጉሡ የወሰነው ሦስት ዓመት ሲፈጸም አሽፈናዝ ወጣቶቹን ሁሉ ወስዶ በናቡከደነፆር ፊት አቀረባቸው። ንጉሡ ሁሉንም ባነጋገራቸው ጊዜ ከእነርሱ መካከል ዳንኤልን፥ ሐናንያን፥ ሚሳኤልንና ዐዛርያን የሚወዳደር አልተገኘም፤ ስለዚህ እነርሱ በንጉሡ ፊት እንዲያገለግሉ ተመረጡ። ጥበብና ማስተዋልን በተመለከቱ ጉዳዮች ንጉሡ በሚጠይቃቸው ነገሮች በንጉሠ ነገሥቱ ግዛት ከሚገኙ ጠንቋዮችና አስማተኞች ሁሉ ዐሥር ጊዜ ብልጫ ያላቸው ሆነው አገኛቸው።
ትንቢተ ዳንኤል 1 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ዳንኤል 1:1-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos