ወደ ቆላስይስ ሰዎች 2:1-19

ወደ ቆላስይስ ሰዎች 2:1-19 አማ05

ስለ እናንተና በሎዶቅያ ስላሉት ሰዎች እንዲሁም ፊቴን እንኳ አይተውት ስለማያውቁ ሰዎች ሁሉ ምን ያኽል ብርቱ ትግል እንደማደርግ ልታውቁ እወዳለሁ። የምታገለውም ልባቸው ተጽናንቶና በፍቅር ተሳስረው፥ ፍጹም ማስተዋልን ሁሉ በማትረፍ የእግዚአብሔር ምሥጢር የሆነውን ክርስቶስን እንዲያውቁ ነው። የጥበብና የዕውቀት ሀብት ተሰውሮ የሚገኘው በክርስቶስ ዘንድ ነው። ይህንንም የምላችሁ ማንም በሽንገላ ቃል እንዳያታልላችሁ ብዬ ነው፤ በሥጋ ከእናንተ ብርቅም እንኳ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ፤ በመልካም ሥነ ሥርዓት መኖራችሁንና በክርስቶስ ላይ ያላችሁን ጽኑ እምነት በማየትም ደስ ይለኛል። ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደተቀበላችሁት በእርሱ ኑሩ፤ በእርሱ ተመሥርታችሁና ታንጻችሁ፥ በተማራችሁት መሠረት፥ በእምነታችሁ ጸንታችሁ ኑሩ፤ ሞልቶ የሚተርፍ ምስጋናም አቅርቡ። በክርስቶስ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በሰው ሠራሽ ወግና በዓለማዊ ተራ ሥርዓት ላይ በተመሠረተ በፍልስፍናና በከንቱ ሽንገላ ማንም እንዳያጠምዳችሁ ተጠንቀቁ። የአምላክነት ፍጹም ሙላት በአካል ተገልጦ የሚኖረው በክርስቶስ ነው። እናንተም ሙሉ ሕይወትን ያገኛችሁት በፍጥረቱ ሁሉ ላይ የግዛትና የሥልጣን ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ነው። በእርሱም በማመናችሁ ተገርዛችኋል፤ ይህም መገረዛችሁ ኃጢአተኛውን የሥጋ ባሕርይ ለማስወገድ በክርስቶስ የተደረገ ነው እንጂ በሰው እጅ የተደረገ አይደለም። በተጠመቃችሁ ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ተቀበራችሁ፤ ከእርሱም ጋር ከሞት ተነሥታችኋል፤ ከሞት የተነሣችሁትም ክርስቶስን ከሞት ባስነሣው በእግዚአብሔር ኀይል በማመናችሁ ነው። ኃጢአት በመሥራታችሁና የኃጢአተኛው ሥጋችሁ በክርስቶስ በማመን ባለመገረዙ ምክንያት ሙታን ነበራችሁ፤ አሁን ግን እግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ሕያዋን አድርጓችኋል፤ ኃጢአታችሁንም ሁሉ ይቅር ብሎላችኋል። እርሱ ያንን ይከሰንና ይቃወመን የነበረውን በሕግ ያለውን የዕዳ ጽሑፍ ደመሰሰው፤ በመስቀል ላይ ቸንክሮም ከእኛ አስወገደው። ኀይሎችንና ባለሥልጣኖችን በመስቀሉ ድል ነሥቶ ትጥቃቸውን ካስፈታ በኋላ ምርኮኞች ሆነው በይፋ እንዲታዩ አደረጋቸው። እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ፥ በዓላትን ወይም የወር መባቻን፥ ወይም ሰንበትን በማክበር ምክንያት ማንም አይፍረድባችሁ። እነዚህ ሁሉ ወደፊት ይመጡ ለነበሩት ነገሮች እንደ ጥላ ናቸው፤ እውነቱ የሚገኘው ግን በክርስቶስ ነው። በአጉል ትሕትናና መላእክትን በማምለክ የሚመካ ማንም ሰው ያለ ዋጋ እንዳያስቀራችሁ ተጠንቀቁ፤ እንዲህ ዐይነቱ ሰው ስለሚያየው ራእይ እየተመጻደቀ ከንቱና ሥጋዊ በሆነ አስተሳሰብ ይታበያል። እንዲህ ያለ ሰው ራስ ከሆነው ከክርስቶስ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፤ አካልን በሙሉ በመገጣጠሚያና በጅማት አያይዞ የሚመግበው ራስ ነው። እግዚአብሔር ለአካል ሙሉ ዕድገት የሚሰጠውም በዚህ ዐይነት ነው።