የሐዋርያት ሥራ 2
2
መንፈስ ቅዱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ መውረዱ
1የጰንጠቆስጤ በዓል በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ በአንድነት በአንድ ቦታ ተሰብስበው ነበር፤ #ዘሌ. 23፥15-21፤ ዘዳ. 16፥9-11። 2በድንገት ብርቱ ዐውሎ ነፋስ የመሰለ ድምፅ ከሰማይ መጣ፤ የነበሩበትንም ቤት ሞላው። 3የእሳት ነበልባሎች የሚመስሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ ተከፋፍለውም በእያንዳንዳቸው ላይ ዐረፉባቸው። 4ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ መንፈስ ቅዱስ እንዲናገሩ በሰጣቸው ችሎታ መጠን በሌሎች ቋንቋዎች መናገር ጀመሩ።
5በዓለም ካሉት አገሮች ሁሉ የመጡ፥ በጸሎት የተጉ አይሁድ በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር። 6ይህንንም ድምፅ በሰሙ ጊዜ ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ በየቋንቋቸውም ሲናገሩ ስለ ሰሙአቸው ተደነቁ። 7በመገረምና በመደነቅም እንዲህ አሉ፤ “እነዚህ እንዲህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? 8ታዲያ፥ እኛ በየትውልድ አገራችን ቋንቋ ሲናገሩ የምንሰማቸው እንዴት ነው? 9እኛ በጳርቴ፥ በሜድ፥ በዔላም፥ በመስጴጦምያ፥ በይሁዳ፥ በቀጰዶቅያ፥ በጳንጦስ፥ በእስያ፥ 10በፍርግያ፥ በጵንፍልያ፥ በግብጽ፥ በቀሬና አጠገብ ባሉት በሊቢያ አውራጃዎች የምንኖር ነን፤ ከሮምም የመጣን አይሁድና ወደ አይሁድነትም የገባን እንገኛለን፤ 11እንዲሁም የቀርጤስና የዐረብ ሰዎች ይገኛሉ፤ እነሆ፥ እነዚህ ሁሉ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በየቋንቋችን ሲናገሩ እንሰማለን!” 12ስለዚህ ሁሉም ተገርመውና የሚሉትን አጥተው “ይህ ነገር ምን ይሆን!” ተባባሉ።
13አንዳንዶቹ ግን “አዲስ የወይን ጠጅ ጠጥተው ሰክረዋል!” እያሉ አፌዙባቸው።
የጴጥሮስ ንግግር
14በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ከዐሥራ አንዱ ጋር ቆመና ድምፁን ከፍ አድርጎ ለሕዝቡ እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “እናንተ የይሁዳ ምድር ሰዎችና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ፥ ይህን የሆነውን ነገር ለማወቅ ንግግሬን አዳምጡ፤ 15ከጠዋቱ ገና ሦስት ሰዓት ስለ ሆነ እናንተ እንዳሰባችሁት እነዚህ ሰዎች አልሰከሩም። 16ነገር ግን ይህ የሆነው ነቢዩ ኢዩኤል እንዲህ ሲል የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው፤
17‘እግዚአብሔር በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል ይላል፤
መንፈሴን በሰው ሁሉ ላይ አፈሳለሁ፤
ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤
ጐልማሶቻችሁም ራእይ ያያሉ፤
ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ። #ኢዩ. 2፥28-32።
18እንዲሁም በእነዚያ ቀኖች
በወንዶችና በሴቶች አገልጋዮቼ ላይ
መንፈሴን አፈሳለሁ፤
እነርሱም ትንቢት ይናገራሉ።
19በላይ በሰማይ ድንቅ ነገሮችን፥
በታች በምድር ተአምራትን አሳያለሁ፤
ደም፥ እሳት፥ የጢስ ጭጋግም ይታያል።
20ታላቁና አስገራሚው
የጌታ ቀን ከመምጣቱ በፊት፥
ፀሐይ ይጨልማል፤
ጨረቃም ደም ትመስላለች።
21የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።’
22“የእስራኤል ሰዎች ሆይ! ይህን ቃል አዳምጡ፤ እናንተ ራሳችሁ እንደምታውቁት የናዝሬቱ የኢየሱስ ማንነት እግዚአብሔር በእናንተ መካከል በእርሱ አማካይነት በፈጸማቸው ታላላቅ ሥራዎች፥ ተአምራትና ምልክቶች ተረጋግጦአል። 23እርሱም ራሱ እግዚአብሔር አስቀድሞ ባቀደውና ባወቀው አሠራር መሠረት ለእናንተ ተላልፎ ተሰጠ፤ እናንተም በዐመፀኞች እጅ እንዲሰቀልና እንዲሞት አደረጋችሁት። #ማቴ. 27፥35፤ ማር. 15፥24፤ ሉቃ. 23፥33፤ ዮሐ. 19፥18። 24እግዚአብሔር ግን የሞትን ኀይል አስወግዶ ከሞት አስነሣው፤ ስለዚህም ሞት ይዞ ሊያስቀረው አልቻለም። #ማቴ. 28፥5-6፤ ማር. 16፥6፤ ሉቃ. 24፥5። 25ዳዊትም ስለ እርሱ እንዲህ ይላል፦
‘ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየዋለሁ፤
እንዳልናወጥም እርሱ በቀኜ ነው
26ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፤
አንደበቴም በደስታ ተሞላ፤
እንዲሁም ሟች የሆነው ሥጋዬ በተስፋ ይኖራል፤
27ነፍሴን በሲኦል አትተዋትም፤
ቅዱስህንም በመቃብር በስብሶ እንዲቀር አታደርገውም።
28የሕይወትን መንገድ አስታወቅኸኝ፤
ከእኔም ጋር በመሆንህ ደስታዬ ፍጹም ይሆናል።’ #መዝ. 16፥8-11።
29“ወንድሞቼ ሆይ! ከቀድሞ አባቶች አንዱ የሆነው ዳዊት እንደ ሞተና እንደ ተቀበረ፥ መቃብሩም እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ እንዳለ በግልጥ ልንገራችሁ። 30ነገር ግን ዳዊት ይህን የተናገረው ነቢይ ስለ ነበረና እግዚአብሔር ‘ከዘርህ አንዱን በዙፋንህ ላይ አስቀምጥልሃለሁ’ ሲል በመሐላ የሰጠውን የተስፋ ቃል ያውቅ ስለ ነበር ነው፤ #መዝ. 132፥11፤ 2ሳሙ. 7፥12-13። 31በዚህም ምክንያት መሲሕ በሲኦል እንደማይቀርና ሥጋውም በመቃብር በስብሶ እንደማይቀር አስቀድሞ አይቶ ስለ ትንሣኤው ተናገረ። 32ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር ከሞት አስነሣው፤ እኛም ሁላችን ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን። 33በእግዚአብሔር ቀኝ ለመቀመጥ ከፍ ባለ ጊዜና የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ከአብ በተቀበለ ጊዜ ይህን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው። 34-35እንግዲህ ወደ ሰማይ የወጣው ዳዊት ባለመሆኑ ዳዊት ራሱ እንዲህ ሲል ተናግሮአል፤
‘ጌታ ለጌታዬ (ለመሲሑ)
ጠላቶችህን በሥልጣንህ ሥር እስካደርግልህ ድረስ
በቀኜ ተቀመጥ’ ብሎታል። #መዝ. 110፥1።
36“እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታና መሲሕ እንዳደረገው የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ በእርግጥ ይወቅ!”
37ሰዎቹም ይህን በሰሙ ጊዜ ልባቸው በሐዘን ተነክቶ ጴጥሮስንና ሌሎቹን ሐዋርያት፥ “ወንድሞች ሆይ! እንግዲህ ምን እናድርግ?” አሉአቸው።
38ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፤ “ንስሓ ግቡ፤ ኃጢአታችሁም ይቅር እንዲባልላችሁ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የእግዚአብሔር ስጦታ የሆነውን መንፈስ ቅዱስንም ትቀበላላችሁ፤ 39የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ፥ ጌታ አምላካችን ወደ እርሱ ለሚጠራቸው፥ በሩቅ ላሉትም ሁሉ ነው።”
40በሌላም በብዙ ቃል እየመሰከረ፥ “በዚህ ጠማማ ትውልድ ላይ ከሚመጣው ቅጣት ራሳችሁን አድኑ!” በማለት መከራቸው። 41ከእነርሱ ብዙዎቹ ቃሉን ተቀብለው ተጠመቁ፤ በዚያን ቀን ሦስት ሺህ የሚያኽሉ አማኞች ተጨመሩ። 42እነርሱም የሐዋርያትን ትምህርት በመስማት፥ በኅብረት በመኖር፥ ማዕድን አብሮ በመብላትና በጸሎት ይተጉ ነበር።
የአማኞች የወንድማማችነትና የኅብረት ኑሮ
43በዚያን ጊዜ በሐዋርያት እጅ ብዙ ተአምራትና ድንቅ ነገሮች ይደረጉ ስለ ነበር በሁሉም ላይ ፍርሀት ዐደረባቸው። 44አማኞች ሁሉ በአንድነት አብረው ይኖሩ ነበር፤ ያላቸውም ነገር ሁሉ የጋራ ነበር። #ሐ.ሥ. 4፥32-35። 45ዕርሻቸውንና ሀብታቸውን እየሸጡ ገንዘቡን ለእያንዳንዱ እንደሚያስፈልገው ያከፋፍሉ ነበር። 46በየቀኑ በቤተ መቅደስ በአንድነት ይሰበሰቡ ነበር፤ በቤታቸውም እንጀራ እየቈረሱ በደስታና በጥሩ ልብ ይመገቡ ነበር፤ 47ጌታንም ያመሰግኑ ነበር፤ ሰውም ሁሉ ያከብራቸው ነበር፤ እግዚአብሔርም የሚድኑትን ሰዎች በየቀኑ ወደ ማኅበራቸው ይጨምር ነበር።
Currently Selected:
የሐዋርያት ሥራ 2: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997