ከዚህ በኋላ ጳውሎስ ከአቴና ተነሥቶ ወደ ቆሮንቶስ ሄደ፤ እዚያ የጳንጦስ ተወላጅ የሆነውን አቂላ የሚባል አንድ አይሁዳዊ ሰው አገኘ፤ የሮም ንጉሠ ነገሥት ቀላውዴዎስ አይሁድ ሁሉ ከሮም እንዲወጡ አዞ ስለ ነበረ አቂላ ከሚስቱ ከጵርስቅላ ጋር ከኢጣልያ ገና መምጣቱ ነበር፤ ስለዚህ ጳውሎስ ወደ እነርሱ ሄዶ ተዋወቃቸው፤ የእርሱ ሥራ ልክ እንደ እነርሱ ድንኳን መስፋት ስለ ነበር ከእነርሱ ጋር ተቀምጦ አብሮአቸው ይሠራ ነበር። በየሰንበቱም በምኲራብ እየተገኘ ንግግር በማድረግ ለአይሁድና ለግሪኮች ያስረዳ ነበር። ሲላስና ጢሞቴዎስ ከመቄዶንያ በመጡ ጊዜ ጳውሎስ “ኢየሱስ መሲሕ ነው” በማለት ለአይሁድ በትጋት እየመሰከረ በማስተማር ጊዜውን ሁሉ ያሳልፍ ነበር። ነገር ግን አይሁድ በተቃወሙትና በሰደቡት ጊዜ የልብሱን ትቢያ አራግፎ “እንግዲህ ቢፈረድባችሁ በራሳችሁ ጥፋት ነው! እኔ ኀላፊነት የለብኝም፤ ከእንግዲህ ወዲህ ወደ አሕዛብ እሄዳለሁ!” አላቸው። ስለዚህ ከእነርሱ ተለይቶ ቲቶስ ኢዮስጦስ ወደተባለው ሰው ቤት ሄደ፤ ይህ ሰው እግዚአብሔርን የሚያመልክ ነበር፤ ቤቱም በምኲራብ አጠገብ ነበር። ቀርስጶስ የሚባል የምኲራብ አለቃ ከቤተሰቡ ሁሉ ጋር በጌታ አመነ፤ ብዙ የቆሮንቶስ ሰዎችም ጳውሎስ ሲናገር ሰምተው አመኑና ተጠመቁ። ጌታም ጳውሎስን ሌሊት በራእይ እንዲህ አለው፦ “አትፍራ፤ ተናገር፤ ዝም አትበል፤ እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፤ በዚህች ከተማ ብዙ ሰዎች አሉኝና ጒዳት ሊያደርስብህ የሚችል ማንም የለም።” ስለዚህ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ቃል ለሕዝቡ እያስተማረ አንድ ዓመት ተኩል እዚያ ቈየ። ጋልዮስ የአካይያ ገዢ ሆኖ በተሾመ ጊዜ አይሁድ በአንድነት ተባብረው በጳውሎስ ላይ ተነሡ፤ ወደ ፍርድ ሸንጎ ወሰዱትና፥ “ይህ ሰው ሕግን በሚቃወም መንገድ ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ ያደርጋል!” አሉ። ጳውሎስ መልስ ለመስጠት ተዘጋጅቶ ሳለ ጋልዮስ አይሁድን እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የአይሁድ ወገኖች! በደል ወይም ከባድ ወንጀል ተፈጽሞባችሁ ቢሆን ኖሮ ክሳችሁን በትዕግሥት በሰማሁ ነበር፤ ነገር ግን ስለ ቃላትና ስለ ስሞች ስለ ሕጋችሁም የምትከራከሩ ከሆነ የራሳችሁ ጉዳይ ነው፤ እኔ በእነዚህ ነገሮች ላይ መፍረድ አልፈልግም።” እንዲህም ብሎ ከፍርድ ሸንጎው አስወጣቸው። በዚህ ጊዜ ሁሉም የምኲራብ አለቃውን ሶስቴንስን ይዘው በሸንጎው ፊት ደበደቡት፤ ይህ ሁሉ ሲሆን ጋልዮስ ደንታ አልነበረውም። ጳውሎስ ከወንድሞች ጋር ብዙ ቀኖች በቆሮንቶስ ከቈየ በኋላ ተሰናብቶአቸው ወደ ሶርያ ሄደ፤ ጵርስቅላና አቂላም ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ ነገር ግን ስለት ስለ ነበረበት ከመሄዱ በፊት ክንክሪያ በሚባል ቦታ ራሱን ተላጨ።
የሐዋርያት ሥራ 18 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 18:1-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች