የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሐዋርያት ሥራ 14:8-20

የሐዋርያት ሥራ 14:8-20 አማ05

በልስጥራ እግሩ የሰለለ አንድ ሰው ነበረ፤ ይህ ሰው ከተወለደ ጀምሮ ሽባ ስለ ነበር በእግሩ ሄዶ አያውቅም፤ ይህ ሰው ጳውሎስ በሚናገርበት ጊዜ ተቀምጦ ያዳምጥ ነበር፤ ጳውሎስ ሰውየውን ትኲር ብሎ ተመለከተና ለመዳን የሚያበቃው እምነት እንዳለው ባየ ጊዜ፥ “ቀጥ ብለህ በእግርህ ቁም!” ሲል በታላቅ ድምፅ ተናገረ፤ ሰውየውም ብድግ አለና መራመድ ጀመረ። ሰዎቹም ጳውሎስ ያደረገውን ባዩ ጊዜ፥ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “አማልክት በሰው አምሳል ሆነው ወደ እኛ ወርደዋል!” በማለት በሊቃኦንያ ቋንቋ ተናገሩ። በርናባስንም “ድያ” አሉት፤ ዋናው ተናጋሪ ጳውሎስ ስለ ነበረ እርሱን “ሄርሜን” አሉት። ከከተማው ውጪ ያለው የድያ ቤተ መቅደስ ካህን ኮርማዎችንና የአበባ ጒንጒኖችን ወደ ከተማው በር አምጥቶ ከሕዝቡ ጋር በመተባበር ለጳውሎስና ለበርናባስ መሥዋዕት ሊያቀርብላቸው ፈለገ። ሐዋርያቱ ጳውሎስና በርናባስ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ በሐዘን ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ወደ ሕዝቡ ሮጡና እየጮኹ እንዲህ አሉ፦ “እናንተ ሰዎች ለምን ይህን ታደርጋላችሁ? እኛም እንደ እናንተ ሰዎች ነን፤ እኛ እዚህ የመጣነው እናንተ ከዚህ ከከንቱ ነገር ሁሉ ርቃችሁ ሰማይን፥ ምድርን፥ ባሕርንና በውስጣቸው የሚገኙትን ሁሉ ወደ ፈጠረው ወደ ሕያው አምላክ እንድትመለሱ መልካም ዜና ልናበሥርላችሁ ነው፤ ባለፉት ዘመኖች ሕዝቦች ሁሉ በገዛ ራሳቸው መንገድ እንዲሄዱ እግዚአብሔር ትቶአቸዋል፤ ይሁን እንጂ እርሱ እንዴት ያለ ቸር አምላክ መሆኑን የሚመሰክር መልካም ሥራ ማድረጉን አላቋረጠም፤ ከሰማይ ዝናብን አዘነበላችሁ፤ የመከር ወራትንም ሰጣችሁ፤ በምግብና በደስታ ልባችሁን አረካ።” ሐዋርያት ይህን ያኽል ቢናገሩም እንኳ ሕዝቡ ለእነርሱ መሥዋዕት እንዳያቀርብ ያስተዉት በብዙ ችግር ነው። አይሁድ ግን ከአንጾኪያና ከኢቆንዮን ወደዚያ መጥተው ሕዝቡን አሳደሙና ጳውሎስን በድንጋይ እንዲወግሩት አደረጉ፤ የሞተ መስሎአቸውም ጐትተው ከከተማ አወጡት። ነገር ግን ደቀ መዛሙርቱ መጥተው በዙሪያው በቆሙ ጊዜ ጳውሎስ ተነሣና ወደ ከተማ ገባ፤ በማግስቱም ከበርናባስ ጋር ወደ ደርቤ ሄደ።