የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሐዋርያት ሥራ 13:26-41

የሐዋርያት ሥራ 13:26-41 አማ05

“እናንተ ከአብርሃም ዘር የተወለዳችሁ ወንድሞችና እናንተም እግዚአብሔርን የምትፈሩ አሕዛብ! ይህ የመዳን ቃል የተላከው ለእኛ ነው። በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሰዎችና አለቆቻቸው ኢየሱስ አዳኝ መሆኑን አላወቁም፤ በየሰንበቱም የሚነበቡትን የነቢያት መጻሕፍት ባለማስተዋላቸው በእርሱ ላይ በፈረዱበት ጊዜ ትንቢቱ ተፈጻሚ እንዲሆን አድርገዋል። ምንም እንኳ ለሞት የሚያበቃ ምክንያት ባያገኙበት እርሱን እንዲገድልላቸው ጲላጦስን ለመኑት። ስለ እርሱ የተጻፈውን ሁሉ ከፈጸሙበት በኋላ ከመስቀል አውርደው ቀበሩት፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ከሞት አስነሣው። ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም ከእርሱ ጋር ለመጡትም ብዙ ቀን ታያቸው፤ እነርሱም አሁን በሕዝብ ፊት ምስክሮቹ ናቸው። እኛም ይዘንላችሁ የመጣነው እግዚአብሔር ለአባቶቻችን በተስፋ የሰጠውን መልካም ዜና ነው። እግዚአብሔር ኢየሱስን ከሞት በማስነሣቱ ይህንኑ ተስፋ ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞታል፤ ይህም በሁለተኛው መዝሙር፥ ‘አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፤’ ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። መበስበስ እንዳይደርስበት እግዚአብሔር ከሞት እንዳስነሣው ለማስረዳት፥ ‘ቅዱሱን የታመነ በረከትን ለዳዊት የተሰጠውን ተስፋ እሰጣችኋለሁ’ ብሎ ተናግሮአል። ደግሞም በሌላ መዝሙር፥ ‘ቅዱሱ ልጅህ መበስበስ እንዲደርስበት አታደርገውም’ ይላል። ነገር ግን ዳዊት በሕይወቱ ዘመን አገልግሎቱን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ከፈጸመ በኋላ ሞቶአል፤ ከአባቶቹም ጋር ተቀብሮአል፤ መበስበስም ደርሶበታል። እግዚአብሔር ከሞት ያስነሣው ግን መበስበስ አልደረሰበትም። እንግዲህ ወንድሞች ሆይ! የኃጢአት ይቅርታ የሚገኘው በኢየሱስ መሆኑ እንደ ተሰበከላችሁ ዕወቁ፤ በእርሱ የሚያምን ሁሉ በሙሴ አማካይነት የተሰጠው ሕግ ነጻ ሊያወጣው ከማይችለው ኃጢአት ሁሉ ነጻ ይወጣል። ስለዚህ በነቢያት እንዲህ ተብሎ የተነገረው እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ፤ ‘እናንተ ፌዘኞች እዩ! ተደነቁ! ጥፉም! ማንም ሰው ቢያወራላችሁ የማታምኑትን ሥራ በዘመናችሁ እሠራለሁ።’ ”