የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሐዋርያት ሥራ 13:13-25

የሐዋርያት ሥራ 13:13-25 አማ05

ከዚህ በኋላ ጳውሎስና ጓደኞቹ በመርከብ ተሳፍረው ከጳፉ በጵንፍልያ ወደምትገኘው ወደ ጴርጌ ሄዱ፤ ማርቆስ የተባለው ዮሐንስ ግን ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ ሄደ። እነርሱ ግን ከጴርጌ ተነሥተው በጲስድያ ወደምትገኘው ወደ አንጾኪያ ሄዱ፤ በሰንበት ቀን ወደ አንድ ምኲራብ ገብተው ተቀመጡ። የሕግና የነቢያት መጻሕፍት ከተነበቡ በኋላ የምኲራቡ አለቆች “ወንድሞች ሆይ፥ ሕዝቡን የሚያጽናና የምክር ቃል ካላችሁ ተናገሩ” ብለው ወደነጳውሎስ ሰው ላኩ። ስለዚህ ጳውሎስ ተነሣና ሕዝቡን በእጁ ጠቀሰ፤ እንዲህም ሲል ተናገረ፤ “የእስራኤል ሰዎችና እግዚአብሔርን የምትፈሩ እናንተ አሕዛብ! ስሙ! የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ የቀድሞ አባቶቻችንን መረጠ፤ በግብጽ አገር በነበሩበት ጊዜም ትልቅ ሕዝብ አደረጋቸው፤ በታላቅ ኀይሉም ከዚያ አገር አወጣቸው። ለአርባ ዓመትም ያኽል በበረሓ ታገሣቸው ከዚያም በኋላ በከነዓን አገር ሰባት መንግሥታትን አጥፍቶ የእነርሱን ምድር አወረሳቸው፤ ከዚህም በኋላ ለአራት መቶ ኀምሳ ዓመት ያኽል እስከ ነቢዩ ሳሙኤል ድረስ መሳፍንትን ሰጣቸው። “ከዚያም ቀጥሎ ንጉሥ እንዲያነግሥላቸው እግዚአብሔርን ለመኑ፤ እግዚአብሔርም ከብንያም ወገን የሆነውን የቂስን ልጅ ሳኦልን ለአርባ ዓመት አነገሠላቸው። ሳኦልንም ከሻረው በኋላ ዳዊትን አነገሠላቸው፤ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት ሲመሰክር፦ ‘እንደ ፍላጎቴ የሚሆንልኝን፤ ፈቃዴንም የሚፈጽመውን፥ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ’ ብሎአል። ከዚህ ሰው ዘር እግዚአብሔር በገባው የተስፋ ቃል መሠረት የእስራኤልን አዳኝ ኢየሱስን አስነሣላቸው። ኢየሱስ ከመምጣቱ በፊት ዮሐንስ ለእስራኤል ሰዎች ሁሉ የንስሓን ጥምቀት ሰብኮ ነበር። ዮሐንስ ሥራውን በጨረሰ ጊዜ ‘እኔ ማን መሰልኳችሁ? እኔ መሲሕ አይደለሁም፤ ነገር ግን የጫማውን ማሰሪያ ለመፍታት እንኳ የማልበቃ ከእኔ በኋላ ሌላ ይመጣል’ ይል ነበር።