ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 5:1-10

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 5:1-10 አማ05

ከዚህ በኋላ የእስራኤል ነገዶች ሁሉ በኬብሮን ወደነበረው ወደ ዳዊት ሄደው እንዲህ አሉት፦ “እነሆ እኛ የአጥንትህ ፍላጭ፥ የሥጋህ ቊራጭ የሆንን ወገኖችህ ነን። ከአሁን በፊት ሳኦል የእኛ ንጉሥ በነበረ ጊዜ እንኳ በጦርነት እስራኤልን የምትመራ አንተ ነበርክ፤ እንዲሁም ሕዝቡን እስራኤልን እንድትመራና በእስራኤልም ላይ እንድትነግሥ እግዚአብሔር ቃል ገብቶልሃል።” እንግዲህ የእስራኤል መሪዎች ሁሉ በኬብሮን ወደ ነበረው ወደ ዳዊት የመጡት በዚህ ዐይነት ነበር፤ እርሱም ከእነርሱ ጋር በእግዚአብሔር ፊት የቃል ኪዳን ስምምነት አደረገ፤ እነርሱም ቀብተው በእስራኤል ላይ አነገሡት። ዳዊት በነገሠበት ጊዜ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበር፤ በጠቅላላ የነገሠበት ዘመን አርባ ዓመት ነበር። ይኸውም በኬብሮን ሳለ በይሁዳ ላይ ሰባት ዓመት ተኩል፥ በኢየሩሳሌም ሆኖ በይሁዳና በመላው እስራኤል ላይ ሠላሳ ሦስት ዓመት ነገሠ። ንጉሡና ሰዎቹ ከኢያቡሳውያን ጋር ለመዋጋት በኢየሩሳሌም ላይ ዘመቱ፤ ዳዊት ወደዚያ የማይገባ መስሎአቸው የምድሪቱ ነዋሪዎች ዳዊትን “አንተ ወደዚህ ልትገባ አትችልም፤ ዕውሮችና አንካሶች እንኳ ይመልሱሃል” አሉት። ዳዊት ግን በጽዮን የሠሩትን ምሽጋቸውን ያዘ፤ እርስዋም “የዳዊት ከተማ” ተብላ ተጠራች። በዚያን ቀን ዳዊት አንዲህ አለ፦ “ኢያቡሳውያንን የሚመታ ዳዊት በሚጠላቸው በዕውሮችና በአንካሶች ላይ አደጋ ለመጣል በውሃው መተላለፊያ ይውጣ፤” ስለዚህም ዕውሮችና አንካሶች ወደ ቤተ መንግሥት አይገቡም ተባለ። ዳዊት ምሽጉን ከያዘ በኋላ መኖሪያውን በዚያው ስፍራ አደረገ፤ እርስዋንም “የዳዊት ከተማ” ብሎ ጠራት፤ ከኮረብታው በስተ ምሥራቅ በኩል በዐፈር ከተደለደለው ስፍራ አንሥቶ በኮረብታው ዙሪያ ከተማይቱንም ሠራ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ነበር ዳዊት በየጊዜው እየበረታ ሄደ።