የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 24:10-17

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 24:10-17 አማ05

በናቡከደነፆር የጦር አዛዦች የሚመራው የባቢሎን ሠራዊት በኢየሩሳሌም ላይ ዘምቶ የከበባትም በዚሁ በዮአኪን ዘመነ መንግሥት ነበር። በከበባውም ጊዜ ናቡከደነፆር ራሱ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ ንጉሥ ኢኮንያን ከእናቱ፥ ከልዑላን መሳፍንቱ፥ ከጦር አዛዦቹና ባለሟሎቹ ከሆኑት ባለሥልጣኖች ጋር ቀርቦ ለባቢሎናውያን እጁን ሰጠ፤ ናቡከደነፆር በነገሠ በስምንተኛው ዓመት ኢኮንያንን እስረኛ አድርጎ ያዘው፤ በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥት የነበረውን ሀብት ሁሉ ጠራርጎ ወደ ባቢሎን ወሰደ። ቀደም ሲል እግዚአብሔር በተናገረውም ቃል መሠረት ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አሠርቶት የነበረውን የወርቅ ዕቃ ሁሉ ሰባበረው። ናቡከደነፆር የኢየሩሳሌምን ሕዝብ፥ ልዑላን መሳፍንቱን ሁሉና ሌሎችንም ታላላቅ ሰዎችን ጭምር በድምሩ ዐሥር ሺህ ሰዎች ማርኮ ወሰደ፤ ከእነርሱም ጋር የእጅ ጥበብ ዐዋቂዎችንና የብረት አንጣሪዎችን ሁሉ ወሰደ፤ በይሁዳ እንዲቀሩ ያደረገው የመጨረሻዎችን ድኾች ብቻ ነበር። ናቡከደነፆር ኢኮንያንን አስሮ ከነእናቱ ከሚስቶቹ፥ ባለሟሎቹ ከሆኑ ባለሥልጣኖችና ከይሁዳ ታላላቅ ሰዎች ጋር በአንድነት ሰብስቦ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው። የባቢሎን ንጉሥ ሰባት ሺህ ለውጊያ ብቃት ያላቸው ወንዶችን፥ እንዲሁም አንድ ሺህ ብረት ቀጥቃጮችንና እደ ጥበበኞችን ወደ ባቢሎን ወሰደ። ናቡከደነፆር በኢኮንያን ምትክ ማታንያ ተብሎ የሚጠራውን የዮአኪንን አጐት በይሁዳ አነገሠ፤ ስሙንም በመለወጥ ሴዴቅያስ ብሎ ጠራው።