እነርሱ ግን መታዘዝ አልፈለጉም፤ በአምላካቸው በእግዚአብሔር እንዳልታመኑ እንደ ቀድሞ አባቶቻቸው እልኸኞች ሆኑ፤ የሰጣቸውንም ድንጋጌ አልተቀበሉም፤ ከቀድሞ አባቶቻቸው ጋር የገባውንም ቃል ኪዳን አልጠበቁም፤ የሰጣቸውንም ማስጠንቀቂያዎች ሁሉ ቸል አሉ፤ ለከንቱ ጣዖቶች በመስገድ ራሳቸውም ከንቱዎች ሆኑ፤ የእነርሱን መጥፎ ምሳሌነት እንዳይወርሱ እግዚአብሔር የሰጣቸውን ትእዛዝ በመሻር በዙሪያቸው የሚኖሩ የአሕዛብን ልማድ ሁሉ ተከተሉ። የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ትእዛዞች ሁሉ በመጣስ የሚሰግዱላቸውን ከወርቅ የተሠሩ ሁለት ጥጆችን አቆሙ፤ እንዲሁም አሼራ ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ምስል ሠሩ፤ ለከዋክብት ሰገዱ፤ ባዓል ተብሎ ለሚጠራውም ባዕድ አምላክ አገልጋዮች ሆኑ። ለእነዚያም አሕዛብ አማልክት ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ፤ ከሙታን ጠሪዎችና ከጠንቋዮችም ምክር ጠየቁ፤ እግዚአብሔር ለሚጠላው ክፉ ነገር ሁሉ ራሳቸውን አሳልፈው በመስጠት የእግዚአብሔርን ቊጣ አነሣሡ። እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ተቈጥቶ የይሁዳን መንግሥት ብቻ በመተው እስራኤላውያንን ከፊቱ አስወገደ። ነገር ግን የይሁዳ ሰዎችም ቢሆኑ፥ አምላካቸው እግዚአብሔር የሰጣቸውን ትእዛዞች አልጠበቁም ነበር፤ እነርሱም የእስራኤል ሕዝብ የተቀበሉትን ልማድ ተከታዮች ነበሩ። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ሁሉ ተዋቸው፤ ከፊቱም እስኪወገዱ ድረስ በዝባዞች ለሆኑት ጠላቶቻቸው አሳልፎ በመስጠት ቀጣቸው። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከይሁዳ ከለየ በኋላ እስራኤላውያን የናባጥን ልጅ ኢዮርብዓምን መርጠው አነገሡ፤ ኢዮርብዓምም እግዚአብሔርን እንዲተዉ በማድረግ አሠቃቂ ወደ ሆነ ኃጢአት መራቸው፤ በአገልጋዮቹ በነቢያት ሁሉ አማካይነት እግዚአብሔር እስራኤልን ከፊቱ እስኪያስወግድ ድረስ እስራኤላውያን የኢዮርብዓምን ኃጢአት ሲሠሩ ኖሩ እንጂ ከዚያ አልራቁም። ስለዚህ እስራኤላውያን ከሀገራቸው ተማርከው በመወሰድ እስከ ዛሬ ድረስ በአሦር ይኖራሉ።
ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 17 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 17:14-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos