የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 9

9
ለክርስቲያኖች የተደረገ መዋጮ
1በይሁዳ ላሉት ክርስቲያኖች ስለሚደረገው መዋጮ ልጽፍላችሁ አያስፈልግም፤ 2“የዐካይያ ሰዎች ከዐለፈው ዓመት ጀምረው ለመርዳት ዝግጁዎች ናቸው” ብዬ በመቄዶንያ ሰዎች ዘንድ ስለ እናንተ የምመካው ትጋታችሁን ስለማውቅ ነው፤ የእናንተም ትጋት ሌሎችን አነሣሥቶአል። 3በዚህ ነገር በእናንተ ላይ ያለን ትምክሕት ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር እነዚህን ወንድሞች እልካለሁ፤ እናንተም ልክ እኔ ከዚህ በፊት እንዳልኩት ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ። 4የመቄዶንያ ሰዎች ከእኔ ጋር ወደ እናንተ መጥተው ያልተዘጋጃችሁ ሆናችሁ ቢያገኙአችሁ በእናንተ በመመካታችን እናፍራለን፤ እናንተማ በጣም ታፍራላችሁ። 5ስለዚህ ልትሰጡ ቃል የገባችሁበትን የልግሥና ስጦታችሁ በቅድሚያ እንድታዘጋጁ እንዲያስታውሱአችሁ በማለት እነዚህ ወንድሞች ከእኔ ቀድመው ወደ እናንተ እንዲመጡ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፤ በዚህ ዐይነት እኔ በምመጣበት ጊዜ የልግሥና ስጦታችሁ ዝግጁ ይሆናል፤ እናንተም የምትሰጡት በግድ ሳይሆን በፈቃደኛነት መሆኑን ያሳያል።
6“ጥቂት የዘራ ጥቂት መከር ይሰበስባል፤ ብዙ የዘራ ብዙ መከር ይሰበስባል” የሚለውን አባባል አስታውሱ። 7ስለዚህ እግዚአብሔር የሚወደው በደስታ የሚሰጠውን ሰው ስለ ሆነ እያንዳንዱ ለመስጠት የፈለገውን በልቡ ፈቅዶ በደስታ ይስጥ እንጂ እያመነታ ወይም በግዴታ አይስጥ። 8ሁልጊዜ በሁሉ ነገር ራሳችሁን ችላችሁ ለመልካም ሥራ ሁሉ ለማዋል እንዲበቃችሁ እግዚአብሔር በብዛት በረከቱን ሊሰጣችሁ ይችላል። 9ይህም፦
“ለድኾች በልግሥና ሰጠ፤
ጽድቁም ለዘለዓለም ይኖራል”
ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። #መዝ. 112፥9።
10ለዘሪ ዘርን፥ ለምግብ እንጀራን የሚሰጥ አምላክ የምትዘሩትን ዘር አበርክቶ ይሰጣችኋል፤ የልግሥናችሁንም ፍሬ ያበዛላችኋል። #ኢሳ. 55፥10። 11ልግሥናችሁ በእኛ አማካይነት የሚደርሳቸው ሰዎች ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ዘንድ ሁልጊዜ እንድትለግሡ እግዚአብሔር በሁሉ ነገር ያበለጽጋችኋል። 12ይህ የምትፈጽሙት የልግሥና አገልግሎት የክርስቲያኖችን ችግር ከማስወገዱም በላይ ሰዎች ለእግዚአብሔር ብዙ ምስጋና እንዲያቀርቡ ያደርጋቸዋል። 13ይህ የእናንተ የልግሥና አገልግሎት እናንተ የክርስቶስን ወንጌል ተቀብላችሁ ታማኞች መሆናችሁንና ለእነርሱና ለሌሎችም መለገሣችሁን የሚያረጋግጥ ስለ ሆነ ሁሉም እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ። 14እነርሱም እግዚአብሔር ለእናንተ በሰጣችሁ በበለጠ ምክንያት ስለሚያፈቅሩአችሁ ይጸልዩላችኋል። 15በሰው ቃል ሊነገር ስለማይቻለው ስጦታው እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ