እግዚአብሔር በምሕረቱ ይህን አገልግሎት ስለ ሰጠን ተስፋ አንቈርጥም። ስውርና አሳፋሪ የሆነውን ነገር አስወግደናል፤ በተንኰልም አንሠራም፤ የእግዚአብሔርንም ቃል አንለውጥም፤ ይልቅስ እውነትን በይፋ እናሳያለን፤ ራሳችንንም ለሰው ሁሉ ኅሊና በእግዚአብሔር ፊት ግልጥ እናደርጋለን። ያስተማርነው የወንጌል ቃል ምናልባት የተሰወረ ቢሆንም የተሰወረው ለሚጠፉት ነው። የዚህ ዓለም ገዢ የሆነው ሰይጣን የማያምኑትን ሰዎች ልብ አሳወረው፤ በዚህም በእግዚአብሔር መልክ የተገለጠው የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል የሚያበራላቸውን ብርሃን እንዳያዩ አደረጋቸው። እኛ የምናስተምረው ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ መሆኑንና እኛም ራሳችን ስለ ኢየሱስ የእናንተ አገልጋዮች መሆናችንን ነው እንጂ ስለ ራሳችንስ አንሰብክም። “ብርሃን በጨለማ ውስጥ ይብራ!” ብሎ የተናገረ እግዚአብሔር በክርስቶስ መልክ የሚያበራውን የእግዚአብሔርን ክብር የማወቅ ብርሃን እንዲሰጠን ብርሃኑን በልባችን ውስጥ እንዲበራ አደረገ። ነገር ግን ይህ ከሁሉ የሚበልጠው ኀይል የእግዚአብሔር እንጂ የእኛ አለመሆኑ እንዲታወቅ ይህን ክቡር ነገር እንደ ሸክላ ዕቃ ሆነን ይዘነዋል። በየአቅጣጫው መከራ ይደርስብናል፤ ግን አንሸነፍም፤ ብዙ ጊዜ ግራ ይገባናል፤ ግን ተስፋ አንቈርጥም፤ ጠላቶች ያሳድዱናል፤ ግን ወዳጆች አጥተን አናውቅም፤ ተመተን እንወድቃለን፤ ግን አንሞትም፤ የኢየሱስ ሕይወት በእኛ ሰውነት እንዲገለጥ በኢየሱስ ላይ የደረሰው ሞት በእኛም ሰውነት ላይ ዘወትር ተሸክመን እንዞራለን። የኢየሱስ ሕይወት በሟች ሰውነታችን ይገለጥ ዘንድ እኛ ሕያዋኑ ስለ ኢየሱስ ሁልጊዜ ለሞት ተላልፈን እንሰጣለን። ስለዚህ እኛ መላልሰን ለሞት ስንጋለጥ እናንተ ግን ለሕይወት ትጋለጣላችሁ።
2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos