እንደ ሞኝ ተናገርኩ! ታዲያ፥ እንዲህ እንድናገር ያደረጋችሁኝ እናንተ ናችሁ፤ እኔን ማመስገን የሚገባችሁ እናንተ ነበራችሁ፤ እኔ ማንነቴ ያልታወቀ ሰው ብሆንም እንኳ ታላላቅ ከተባሉት ሐዋርያት በምንም አላንስም። እኔ እውነተኛ ሐዋርያ መሆኔን የሚያስረዱት ነገሮች እኔ በመካከላችሁ ሳለሁ በትዕግሥት የፈጸምኳቸው ሥራዎች ናቸው፤ እነዚህም ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች ተአምራትም ናቸው። በእናንተ ላይ ሸክም ሳልሆን ከመቅረቴ በቀር ከሌሎች አብያተ ክርስቲያን እናንተን ያሳነስኳችሁ በምንድን ነው? ይህም ጥፋት ሆኖ ከተቈጠረ ይቅር በሉኝ! ወደ እናንተ ለመምጣት ስዘጋጅ አሁን ሦስተኛዬ ጊዜዬ ነው፤ እኔ ሸክም ልሆንባችሁ አልፈልግም፤ እኔ የምፈልገው እናንተን እንጂ ገንዘባችሁን አይደለም። ለልጆቻቸው ሀብት ማከማቸት የሚገባቸው ወላጆች ናቸው እንጂ ልጆች ለወላጆቻቸው ሀብት አያከማቹም። ስለ እናንተ እንኳን ገንዘቤን ራሴንም አሳልፌ ብሰጥ እጅግ በጣም ደስ ይለኛል፤ ታዲያ፥ እኔ ይህን ያኽል አብዝቼ ስወዳችሁ እናንተ የምትወዱኝ እንዲህ በጥቂቱ ነውን? ያም ሆነ ይህ ሸክም አልሆንኩባችሁም፤ ለመሆኑ በተንኰልና በማታለል የያዝኳችሁም ይመስላችኋል። ከላክሁላችሁ ሰዎች በአንዱ እንኳ አማካይነት ተጠቀምኩባችሁን? ቲቶ ወደ እናንተ እንዲመጣ ለመንኩት፤ ያንን ወንድማችንንም ከእርሱ ጋር ላክሁት፤ ታዲያ፥ ቲቶስ ተጠቀመባችሁን? እኔና እርሱ ያገለገልናችሁ በአንድ መንፈስ አልነበረምን? አካሄዳችንስ አንድ አልነበረምን? ሁላችሁም እስከ አሁን የምታስቡት እኛ በእናንተ ፊት ስለ ራሳችን እንደምንከላከል አድርጋችሁ ነውን? እኛ በክርስቶስ ሆነን የምንናገረው በእግዚአብሔር ፊት ነው፤ ወዳጆቼ ሆይ! እኛ ይህን ሁሉ የምንናገረው እናንተን ለማነጽ ብለን ነው። እኔ ወደዚያ በምመጣበት ጊዜ ምናልባት ልትሆኑ እንደምፈልገው ሳትሆኑ፥ እኔም እናንተ እንደምትፈልጉት ሳልሆን እንገናኝ ይሆናል ብዬ እፈራለሁ፤ እንዲሁም በእናንተ ዘንድ ጥል፥ ቅናት፥ ቊጣ፥ ራስ ወዳድነት፥ የሰው ስም ማጥፋት፥ ሐሜት፥ ትዕቢትና ሁከት ይኖሩ ይሆናል ብዬ እፈራለሁ። እንደገና ወደ እናንተ ስመጣ አምላኬ ምናልባት በእናንተ ፊት ያዋርደኛል ብዬ እፈራለሁ፤ ከዚህ ቀደም ኃጢአት ሠርተው በዚሁ በሠሩት ርኲሰት፥ ዝሙትና፥ ስድነት ንስሓ ስላልገቡት ሰዎች ሐዘን ላይ እወድቃለሁ ብዬ እፈራለሁ።
2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 12 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 12:11-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos