ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 19
19
ኢዩ ተብሎ የሚጠራ ነቢይ ኢዮሣፍጥን መገሠጹ
1የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤተ መንግሥቱ በደኅና ተመለሰ፤ 2የሐናኒ ልጅ የሆነው ኢዩ ተብሎ የሚጠራው ነቢይ ንጉሥ ኢዮሣፍጥን ለመገናኘት መጥቶ እንዲህ ሲል ገሠጸው፤ “አንተ ክፉዎችን መርዳትና እግዚአብሔርን ከሚጠሉት ጋር መተባበር መልካም ይመስልሃልን? ይህ ያደረግኸው ክፉ ነገር የእግዚአብሔር ቊጣ በአንተ ላይ እንዲወርድ አድርጎአል፤ 3ይህም ሁሉ ሆኖ አንዳንድ መልካም ነገር አድርገሃል፤ ይኸውም ሕዝቡ ያመልካት የነበረችውን አሼራ ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ምስሎችን ሁሉ ከምድሪቱ አስወግደሃል፤ የእግዚአብሔርንም ፈቃድ ለይተህ ለመፈጸም ጥረት አድርገሃል።”
ኢዮሣፍጥ ያደረገው ማሻሻል
4ንጉሥ ኢዮሣፍጥ መኖሪያውን በኢየሩሳሌም ቢያደርግም እንኳ ሕዝቡ ወደ ቀድሞ አባቶቻቸው አምላክ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ለማድረግ በደቡብ ከቤርሳቤህ ጀምሮ በሰሜን እስከ ኰረብታማው የኤፍሬም አገር ዳርቻ ድረስ እየተመላለሰ በየጊዜው በሕዝቡ መካከል ተገኝቶአል፤ 5በተመሸጉት በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ዳኞችን ሾሞአል፤ 6እንዲህ የሚል መመሪያም ሰጣቸው፦ “ፍርድ በምትሰጡበት ጊዜ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር መሆኑን በመገንዘብ ብርቱ ጥንቃቄ አድርጉ፤ እናንተ የምትፈርዱት ሰውን ለማስደሰት ሳይሆን ለእግዚአብሔር ነው። 7ፍትሕ ማጓደል ወይም ማድላት ወይም ጉቦ መቀበል በአምላካችን በእግዚአብሔር ዘንድ የሌሉ ስለ ሆነ እግዚአብሔርን በመፍራት ትክክለኛ ፍርድ ስጡ።”
8ንጉሥ ኢዮሣፍጥ የእግዚአብሔርን ሕግ በመተላለፍ ወይም በከተማይቱ ኗሪዎች መካከል የሚነሣውን ሕግ ነክ ክርክር በሚመለከት ጉዳይ ሁሉ ይዳኙ ዘንድ ሌዋውያንን፥ ካህናትንና ከታወቁ የአገር ሽማግሌዎች አንዳንዶቹን በኢየሩሳሌም ሾመ፤ እነርሱም በኢየሩሳሌም ተቀመጡ። 9የሚከተለውንም መመሪያ ሰጣቸው፤ “እግዚአብሔርን በመፍራት በታማኝነትና በቅን ልቡና አገልግሉ፤ 10በከተሞች ከተቀመጡት ከወገኖቻችሁ ወደ እናንተ የሚመጣ ጉዳይ፥ የግድያ፥ ወይም ሌላ የሕግ ጉዳይ፥ ሕግን፥ ትእዛዞችን ወይም ድንጋጌና ሥርዓቶችን መተላለፍ ቢሆን በእግዚአብሔር ላይ በደል እንዳይፈጽሙ፥ ቊጣም በእናንተና በወንድሞቻችሁ ላይ እንዳይመጣ አስጠንቅቁአቸው፤ እንዲህም ብታደርጉ በደለኞች አትሆኑም። 11በመንፈሳዊ ጉዳይ ሁሉ ወሳኝ ሥልጣን የሚኖረው ሊቀ ካህናቱ አማርያ ነው፤ በሌላው ጉዳይ ሁሉ ወሳኝ ሥልጣን የሚኖረው የይሁዳ አስተዳዳሪ የሆነው የእስማኤል ልጅ ዘባድያ ነው፤ ሌዋውያን በፊታችሁ እንደ ባለሥልጣን ሆነው ያገለግላሉ፤ ያለ ፍርሀት በድፍረት ሥሩ! እግዚአብሔርም መልካም ሥራ ከሚሠሩት ጋር ይሁን!”
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 19: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997