1 ወደ ጢሞቴዎስ 6:6-19

1 ወደ ጢሞቴዎስ 6:6-19 አማ05

“ያለኝ ይበቃኛል” ለሚል ሰው እግዚአብሔርን ማምለክ ትልቅ ጥቅም ያስገኝለታል። መንፈሳዊነትን ስለሚያተርፍበት ሃይማኖት የሀብት ምንጭ ነው። ወደዚህ ዓለም ምንም ይዘን አልመጣንም፤ ከዚህም ዓለም ይዘነው የምንሄድ ምንም ነገር የለም። የምንበላውንና የምንለብሰውን ካገኘን ይበቃናል። ሀብታሞች ለመሆን የሚፈልጉ ግን በፈተና ይወድቃሉ፤ ሰዎችን በሚያበላሽና በሚያጠፋ ከንቱና አደገኛ በሆነ በብዙ ምኞት ወጥመድ ይያዛሉ። ይህም የሚሆነው የገንዘብ ፍቅር የክፋት ሁሉ ምንጭ ስለ ሆነ ነው። የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! አንተ ግን ከዚህ ሁሉ ሽሽ፤ ጽድቅን፥ መንፈሳዊነትን፥ እምነትን፥ ፍቅርን፥ በትዕግሥት መጽናትን፥ ገርነትን ተከታተል። የእምነትን መልካም ጦርነት ተዋጋ፤ አንተ ወደ እርሱ በተጠራህ ጊዜ በብዙ ምስክሮች ፊት ትክክለኛ ምስክርነትን የሰጠኸውን ዘለዓለማዊውን ሕይወት ያዝ። ለሁሉ ነገር ሕይወት በሚሰጠው በእግዚአብሔርና በጴንጤናዊው ጲላጦስ ፊት በመልካም መታመን በመሰከረው በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት አዝሃለሁ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከሚገለጥበት ቀን ድረስ ይህን ትእዛዝ ያለ ስሕተትና ያለ ነቀፋ ጠብቅ። የክርስቶስም መገለጥ፥ የተባረከና፥ ብቻውን ገዢ የሆነ፥ የነገሥታት ንጉሥ፥ የጌቶች ጌታ በወሰነው ቀን ይሆናል፤ እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ እርሱን ከቶ ማንም አላየውም፤ ማንም ሊያየውም አይችልም፤ ክብርና ዘለዓለማዊ ኀይል ለእርሱ ይሁን፤ አሜን። የዚህ ዓለም ሀብታሞች እንዳይታበዩ ወይም ተስፋቸውን አስተማማኝ ባልሆነ ሀብት ላይ እንዳያደርጉ እዘዛቸው፤ እንዲሁም ተስፋቸው እኛን ደስ እንዲለን ሁሉን ነገር አትረፍርፎ በሚሰጠን በእግዚአብሔር ላይ እንዲሆን እዘዛቸው። ደግሞም መልካም ሥራ እንዲሠሩ፥ በመልካም ሥራ ሀብታሞች እንዲሆኑ፥ ለመለገሥና ያላቸውንም ለማካፈል ዝግጁዎች እንዲሆኑ እዘዛቸው። በዚህ ዐይነት እውነተኛውን ሕይወት ለማግኘት መሠረቱ ጽኑ የሆነውን ሀብት በሚመጣው ዘመን ለራሳቸው ያከማቻሉ።