የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 5

5
የቃል ኪዳኑ ታቦት በፍልስጥኤማውያን መካከል መገኘት
1ፍልስጥኤማውያን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከማረኩ በኋላ ከአቤንዔዜር አሽዶድ ተብላ ወደምትጠራ ከተማቸው ወሰዱአት። 2ዳጎን ተብሎ ወደሚጠራውም አምላካቸው ቤተ ጣዖት አስገቡት፤ ከምስሉም ሐውልት ጐን አቆሙት። 3በማግስቱም ማለዳ የአሽዶድ ሰዎች ተነሥተው ሲመለከቱ የዳጎን ምስል ሐውልት በእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ፊት በግንባሩ መሬት ላይ ተደፍቶ አዩት፤ ከዚያም አንሥተው ቀድሞ በነበረበት ስፍራ አቆሙት፤ 4በተከታዩም ቀን ማለዳ ተነሥተው ሲመለከቱ የምስሉ ሐውልት በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት እንደገና ወድቆ አዩት፤ በዚህ ጊዜ ራሱና ሁለት እጆቹ ተሰባብረው በመግቢያው መድረክ ላይ ወድቀው ሌላው አካሉ ብቻ ቀርቶ ነበር። 5ዛሬም እንኳ ቢሆን የዳጎን ካህናትና በአሽዶድ እርሱን የሚያመልኩት ሁሉ ያን የመግቢያ መድረክ በእግራቸው ሳይረግጡ ተራምደው የሚሄዱበት ምክንያት ይኸው ነው።
6እግዚአብሔርም የአሽዶድን ሕዝብ በብርቱ አስጨነቃቸው፤ እነርሱንና በዙሪያቸው ያሉትን ሕዝብ ሁሉ በእባጭ መቅሠፍት ቀጣቸው። 7የአሽዶድ ኗሪዎች የሆነውን ነገር ሁሉ ባዩ ጊዜ “ቊጣው በእኛና በአምላካችን በዳጎን ላይ ስለ በረታ የእስራኤል አምላክ ታቦት እዚህ እኛ ዘንድ መቈየት የለበትም” አሉ። 8በዚህም ምክንያት ወደ አምስቱ የፍልስጥኤማውያን ነገሥታት መልእክተኞች ልከው በማስጠራት “ስለ እስራኤል አምላክ የቃል ኪዳን ታቦት ምን እናድርግ” ብለው ጠየቁአቸው።
እነርሱም “ወደ ጋት ውሰዱት” ብለው መለሱላቸው፤ ስለዚህም ጋት ተብላ ወደምትጠራው ወደ ሌላይቱ የፍልስጥኤማውያን ከተማ ወሰዱት፤ 9ነገር ግን የቃል ኪዳኑ ታቦት እዚያ ከደረሰ በኋላ እግዚአብሔር ያቺንም ከተማ ጭምር ቀጣ፤ ሕዝብዋንም በብርቱ አስጨነቀ። ሕፃኑንም ሽማግሌውንም ሳይለይ ሕዝቡን ሁሉ በአንድነት በእብጠት በሽታ ቀጣቸው፤ 10ስለዚህም የቃል ኪዳኑ ታቦት ዔቅሮን ተብላ ወደምትጠራው ወደ ሌላይቱ የፍልስጥኤማውያን ከተማ እንዲወሰድ አደረጉ፤ ነገር ግን እዚያ በደረሰ ጊዜ ኗሪዎቹ እየጮኹ በማልቀስ “የእስራኤልን አምላክ የቃል ኪዳን ታቦት ወደዚህ ያመጡብን እኛን ሁላችንን ለመፍጀት አስበው ነው!” አሉ። 11እንደገና ወደ ፍልስጥኤማውያን ነገሥታት ሁሉ መልእክተኞች ልከው “እኛንና ቤተሰባችንን ሁሉ ከመፍጀቱ በፊት የእስራኤልን የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ስፍራው መልሳችሁ ላኩ” አሉ፤ እግዚአብሔር በብርቱ ስለ ቀጣቸው በመላ ከተማይቱ የሚያስጨንቅ የሞት ፍርሀት ነበር፤ 12ከሞት የተረፉትም የእባጩ በሽታ በርትቶባቸው ስለ ነበር ሕዝቡ ርዳታ ለማግኘት ወደ አማልክታቸው በማልቀስ ጮኹ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ