አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 4
4
የቃል ኪዳኑ ታቦት መማረክ
1እስራኤላውያን ፍልስጥኤማውያንን ለመውጋት ወጡ፤ ስለዚህም እስራኤላውያን አቤንዔዜር ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ሰፈሩ፤ ፍልስጥኤማውያንም አፌቅ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ሰፈሩ፤ #4፥1 አበንዔዜር፦ የረድኤት ድንጋይ። 2ፍልስጥኤማውያንም አደጋ መጣል ጀመሩ፤ ከከባድ ጦርነት በኋላ እስራኤላውያንን ድል በመንሣት በጦር ሜዳ አራት ሺህ ሰው ገደሉባቸው፤ 3ከጦርነት የተረፉት ወደ ሰፈራቸው በተመለሱ ጊዜ የእስራኤል መሪዎች እንዲህ አሉ፤ “ዛሬ ፍልስጥኤማውያን እኛን ድል ያደርጉ ዘንድ እግዚአብሔር ስለምን ፈቀደላቸው? ከእኛ ጋር በመሄድ ከጠላቶቻችን እጅ ያድነን ዘንድ እንግዲህ እንሂድና የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ከሴሎ እናምጣ።” 4ስለዚህም ወደ ሴሎ መልእክተኞች ልከው በታቦቱ ላይ ባሉ ኪሩቤል ዙፋኑን ያደረገ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ግርማውን የሚገልጥበትን የቃል ኪዳኑን ታቦት አስመጡ፤ ሁለቱ የዔሊ ልጆች ሖፍኒና ፊንሐስም የቃል ኪዳኑን ታቦት አጅበው መጡ። #ዘፀ. 25፥22።
5የቃል ኪዳኑም ታቦት በዚያ ቦታ በደረሰ ጊዜ እስራኤላውያን ምድር እስክትናወጥ ድረስ ታላቅ የእልልታና የሆታ ድምፅ አሰሙ። 6ፍልስጥኤማውያንም ያንን የእልልታ ድምፅ ሰምተው “በዕብራውያን ሰፈር የምንሰማው ይህ ታላቅ የእልልታ ድምፅ ምን ይሆን?” ተባባሉ፤ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ዕብራውያን ሰፈር መምጣቱንም ባወቁ ጊዜ፥ 7ፈርተው እንዲህ አሉ፦ “ከአማልክት አንዱ ወደ እነርሱ ሰፈር መጥቶአል፤ እንግዲህ ወዮልን! ከዚህ በፊት እንዲህ ያለ ሁኔታ ደርሶብን አያውቅም፤ 8ወዮልን! ከእነዚህ ኀያላን አማልክት እጅ ማን ያድነናል? እነርሱ ግብጻውያንን በበረሓ በተለያዩ መቅሠፍቶች የመቱ ናቸው። 9ፍልስጥኤማውያን ሆይ! እንግዲህ በርቱ! ጠንክሩ! ይህ ካልሆነ ቀድሞ እነርሱ የእኛ ባሪያዎች እንደ ነበሩ ሁሉ እኛም ደግሞ የዕብራውያን ባርያዎች ሆነን መቅረታችን ነው፤ ስለዚህ በወንድነት ጠንክራችሁ ተዋጉ!”
10ፍልስጥኤማውያንም በብርቱ ተዋግተው እስራኤላውያንን ድል ነሡ፤ እስራኤላውያንም ወደየድንኳናቸው ሸሹ፤ ታላቅ እልቂት ሆኖ ሠላሳ ሺህ እስራኤላውያን ወታደሮች ተገደሉ፤ 11የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦትም ተማረከ፤ ሁለቱ የዔሊ ልጆች ሖፍኒና ፊንሐስም ተገደሉ።
የዔሊ መሞት
12ነገዱ ከብንያም ወገን የሆነ አንድ ሰው ከጦር ሜዳ ተነሥቶ በመገሥገሥ በዚያኑ ዕለት ሴሎ ደረሰ፤ ሐዘኑንም ለማሳወቅ ልብሱን ቀዶ በራሱ ላይ ትቢያ ነስንሶ ነበር፤ 13ሰውዬው በደረሰ ጊዜ ልቡ ለእግዚአብሔር ታቦት ተጨንቆ የነበረው ዔሊ በመንገድ ዳር በወንበር ተቀምጦ ይመለከት ነበር። ሰውዬውም ወደ ከተማ መጥቶ ወሬውን በተናገረ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ከፍተኛ ጩኸት አስተጋቡ። 14ዔሊም የጩኸቱን ድምፅ ሰምቶ “ይህ ሁሉ ጩኸት ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀ፤ ያም ሰው ወሬውን ለዔሊ ለመንገር ቸኲሎ ሄደና ነገረው፤ 15በዚያን ዘመን ዔሊ የዘጠና ስምንት ዓመት ሽማግሌ ነበር፤ ዐይኑም ፈዞ ነበር። 16ሰውየውም ቀርቦ “እኔ ከጦርነቱ አምልጬ መጣሁ፤ ዛሬም እዚህ የደረስኩት በብርቱ ሩጫ ነው” አለ።
ዔሊም “ልጄ ሆይ! ታዲያ እንዴት ሆነ?” አለው።
17ወሬ ነጋሪውም “እስራኤላውያን ድል ሆነው ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ ይህም ሽንፈት በእኛ ላይ መድረሱ እጅግ አሠቃቂ ነው፤ ከዚህም ሁሉ ጋር ልጆችህ ሖፍኒና ፊንሐስ ተገደሉ፤ የእግዚአብሔርም የቃል ኪዳን ታቦት ተማረከች” ሲል መለሰለት።
18ወሬ ነጋሪው የቃል ኪዳኑን ታቦት መማረክ ባወሳ ጊዜ ዔሊ በቅጽሩ በር አጠገብ ከተቀመጠበት ወንበር ላይ ተገልብጦ ወደ ኋላው ወደቀ፤ እርሱም ሽማግሌ ከመሆኑም በላይ በውፍረቱ ግዙፍ ስለ ነበር ከአወዳደቁ የተነሣ አንገቱ ተሰብሮ ሞተ፤ ዔሊም በእስራኤል መሪ ሆኖ የቈየበት ዘመን አርባ ዓመት ነበር።
የሟቹ ፊንሐስ ሚስት አሟሟት
19የፊንሐስ ሚስት የነበረችው የዔሊ ምራት ነፍሰ ጡር ነበረች፤ የምትወልድበትም ጊዜ ተቃርቦ ነበር፤ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት መማረኩን፤ ዐማትዋና ባልዋ መሞታቸውን በሰማች ጊዜ በድንገተኛ ምጥ ተይዛ ወለደች፤ ምጡም ጸንቶባት ነበር፤ 20እርስዋም ለመሞት በምታጣጥርበት ጊዜ በማዋለድ የምትረዳት ሴት “አይዞሽ በርቺ! ወንድ ልጅ ወልደሻል!” አለቻት፤ ነገር ግን አዳምጣ መልስ አልሰጠቻትም፤ አላተኰረችበትምም። 21እርስዋም በእግዚአብሔር ታቦት መማረክ፥ በዐማትዋና በባልዋ መሞት ምክንያት ክብር ከእስራኤል ተለየ ስትል ልጅዋን ኢካቦድ ብላ ሰየመችው። #4፥21 ኢካቦድ፦ በዕብራይስጥ “ክብር አልባ” ማለት ነው። 22ቀጥላም “የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት በመማረኩ ምክንያት የእግዚአብሔር ክብር ከእስራኤል ተለየ” አለች።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 4: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997