የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 23

23
ዳዊት የቀዒላን ከተማ ከጥፋት እንደ አዳነ
1ፍልስጥኤማውያን በቀዒላ ከተማ ላይ አደጋ መጣላቸውንና በቅርቡ የተሰበሰበውንም የአዲሱን መከር እህል ዘርፈው መውሰዳቸውን ዳዊት ሰማ፤ 2ስለዚህም ዳዊት “ሄጄ በፍልስጥኤማውያን ላይ አደጋ ልጣልባቸውን?” ሲል የእግዚአብሔርን ፈቃድ ጠየቀ።
እግዚአብሔርም “አዎ! በፍልስጥኤማውያን ላይ አደጋ በመጣል ቀዒላን ከጥፋት አድን” ሲል መለሰለት።
3ነገር ግን የዳዊት ተከታዮች “በዚህ በይሁዳ ስንኖር የምንፈራው ብዙ ነገር አለ፤ አሁን ደግሞ ወደ ቀዒላ ሄደን በፍልስጥኤማውያን ሠራዊት ላይ አደጋ ብንጥል ችግራችን የባሰ ችግር ይገጥመናል!” አሉት። 4ከዚህም የተነሣ ዳዊት እንደገና የእግዚአብሔርን ፈቃድ ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም “እኔ በፍልስጥኤማውያን ላይ ድልን ስለማቀዳጅህ ሄደህ በቀዒላ ላይ አደጋ ጣል” አለው። 5ስለዚህም ዳዊትና ተከታዮቹ ወደ ቀዒላ ሄደው በፍልስጥኤማውያን ላይ አደጋ ጣሉባቸው፤ ከእነርሱም ብዙዎቹን ገድለው የከብትና የበግ መንጋዎቻቸውን ዘርፈው ወሰዱ፤ በዚህም ዐይነት ዳዊት ከተማይቱን ከጥፋት አዳናት።
6የአቤሜሌክ ልጅ አብያታር አምልጦ በቀዒላ ከዳዊት ጋር በተባበረ ጊዜ ወደዚያ የመጣው ኤፉዱን እንደ ያዘ ነበር።
7ለሳኦልም ዳዊት ወደ ቀዒላ መምጣቱ በተነገረው ጊዜ “እግዚአብሔር እርሱን በእጄ ሊጥልልኝ ነው፤ ዳዊት የግንብ ቅጽርና የተመሸጉ የቅጽር በሮች ወዳሉአት ከተማ በመዝለቁ ራሱን በወጥመድ ውስጥ አስገብቶአል” አለ። 8ስለዚህም ሳኦል ወታደሮቹን ለጦርነት ጠርቶ ወደ ቀዒላ በመዝመት ዳዊትንና ተከታዮቹን እንዲከቡ አዘዘ።
9ዳዊትም ሳኦል አደጋ ሊጥልበት ማቀዱን በሰማ ጊዜ ካህኑን አብያታርን “ኤፉዱን ይዘህ ና!” አለው። 10ከዚህም በኋላ ዳዊት እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! በአገልጋይህ በእኔ ሰበብ ሳኦል መጥቶ ቀዒላን ለመደምሰስ ማቀዱን ሰምቻለሁ። 11ታዲያ፥ የቀዒላ ከተማ ነዋሪዎች እኔን ለሳኦል አሳልፈው ይሰጡኝ ይሆን? ሳኦልስ እኔ እንደ ሰማሁት ወደዚህ መምጣቱ እውነት ነውን? የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! መልስ እንድትሰጠኝ እለምንሃለሁ!”
እግዚአብሔርም “አዎ፥ ሳኦል በእርግጥ ይመጣል” ሲል መለሰለት።
12ዳዊትም “የቀዒላ ከተማ ነዋሪዎችስ ተከታዮቼንና እኔን ለሳኦል አሳልፈው ይሰጡን ይሆን?” ሲል እንደገና ጠየቀ።
እግዚአብሔርም “አዎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል” ሲል መለሰ።
13ስለዚህም ዳዊትና ስድስት መቶ የሚሆኑ ተከታዮቹ በሙሉ ወዲያውኑ ቀዒላን ለቀው ለመሄድ ተንቀሳቀሱ፤ ሳኦልም ዳዊት ከቀዒላ አምልጦ መሄዱን በሰማ ጊዜ የነበረውን ዕቅድ ተወ።
ዳዊት በኮረብታማው አገር የነበረበት ሁኔታ
14ዳዊት በዚፍ አጠገብ ባለው ምድረ በዳ ውስጥ በኮረብታማው አገር ተሸሽጎ ኖረ፤ ሳኦልም እርሱን ለማግኘት ዘወትር ይፈልገው ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ዳዊትን ለሳኦል አሳልፎ አልሰጠውም፤ 15ዳዊትም ሳኦል ሊገድለው መምጣቱን ተመለከተ።
ዳዊት በዚፍ አጠገብ ባለው ምድረ በዳ ውስጥ በሖሬሽ ይገኝ ነበር፤ 16የሳኦል ልጅ ዮናታንም እዚያው ድረስ ወደ ዳዊት ሄዶ እግዚአብሔር በአስተማማኝ ሁኔታ የሚጠብቀው መሆኑን በመግለጥ እንዲህ እያለ አበረታታው፤ 17“አይዞህ አትፍራ፤ አባቴ ሳኦል በአንተ ላይ ጒዳት ማድረስ ከቶ አይችልም፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ እንደምትሆንና እኔም ከአንተ የምቀጥል ሁለተኛ ማዕርግ እንደሚኖረኝ አባቴ በደንብ ያውቃል።” 18ስለዚህ ሁለቱም እርስ በርሳቸው የወዳጅነት ቃል ኪዳን አደረጉ፤ ከዚህም በኋላ ዳዊት በሖሬሽ መኖሩን ቀጠለ፤ ዮናታንም ወደ ቤቱ ተመልሶ ሄደ። #1ሳሙ. 18፥3።
19ከዚፍ ነዋሪዎች አንዳንዶቹ በጊብዓ ወደሚገኘው ወደ ሳኦል ሄደው እንዲህ አሉ፥ “ዳዊት በእኛ ግዛት ውስጥ ከይሁዳ ምድረ በዳ በስተ ደቡብ ባለው በሐኪላ ተራራ ላይ በምትገኘው በሖሬሽ ተሸሽጎ ይገኛል። #መዝ. 54። 20ንጉሥ ሆይ፥ አንተ እርሱን በምትፈልግበት ጊዜ ወደ እኛ ና፤ እኛም እርሱን ለአንተ ለንጉሡ አሳልፈን ለመስጠት ኀላፊነትን እንወስዳለን።”
21ሳኦልም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “ለእኔ ይህን ያኽል ቸርነት ስላደረጋችሁልኝ እግዚአብሔር ይባርካችሁ! 22አሁንም እንደገና ሄዳችሁ አረጋግጡ፤ ያለበትን ስፍራ ያየውም ማን እንደ ሆነ መርምራችሁ አግኙ፤ እኔ እርሱ ዘዴኛ መሆኑን ሰምቻለሁ፤ 23የሚሸሸግባቸውን ስፍራዎች በትክክል አግኙ፤ ያገኛችሁትንም ማስረጃ ወዲያው ይዛችሁልኝ ኑ፤ ከዚያም በኋላ እኔ አብሬአችሁ እሄዳለሁ፤ አሁንም በዚያው ግዛት ውስጥ የሚኖር ከሆነ መላውን የይሁዳ ግዛት ማሰስ ቢያስፈልገኝም እንኳ እርሱን በማደን እይዘዋለሁ።”
24ስለዚህም እነርሱ ሳኦል ከመሄዱ በፊት ወደ ዚፍ ተመለሱ፤ በዚህን ጊዜ ዳዊትና ተከታዮቹ ከይሁዳ ምድረ በዳ በስተ ደቡብ በኩል በሚገኘው በማዖን በረሓ ነበሩ፤ 25ሳኦልና ወታደሮቹም ዳዊትን ለማሳደድ ወጥተው ሄዱ፤ ዳዊትም ይህን ስላወቀ በማዖን ምድረ በዳ አለት ወደበዛበት አንድ ኮረብታ አልፎ በዚያ ተቀመጠ፤ ሳኦልም ይህን በሰማ ጊዜ ዳዊትን የመከታተል ተግባሩን ቀጠለ፤ 26ሳኦልና ወታደሮቹ ከኮረብታው በአንድ በኩል ሲሆኑ፥ ዳዊትና ተከታዮቹም ከኮረብታው በሌላ በኩል ነበሩ፤ ዳዊትና ተከታዮቹም ሊማርኩአቸው ከተቃረቡት ከሳኦልና ከወታደሮቹ ለማምለጥ በመጣደፍ ላይ ነበሩ። 27ይህ በዚህ እንዳለ ወዲያውኑ አንድ መልእክተኛ ደርሶ ሳኦልን “ፍልስጥኤማውያን አገሪቱን በመውረር ላይ ናቸውና አሁኑኑ ፈጥነህ ተመልሰህ ና!” አለው። 28ስለዚህም ሳኦል ዳዊትን የማሳደድ ተግባሩን አቁሞ ፍልስጥኤማውያንን ለመውጋት ሄደ፤ ያም ቦታ “የማምለጥ አለት” ተብሎ የተጠራበት ምክንያት ይኸው ነው። 29ዳዊትም ከዚያ በመነሣት ተሸሽጎ ወደቈየበት ዔንገዲ ተብሎ ወደሚጠራው ስፍራ ሄደ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ