የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 17:32-51

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 17:32-51 አማ05

ዳዊትም ሳኦልን “ንጉሥ ሆይ! ከዚህ ፍልስጥኤማዊ የተነሣ ማንም ሰው መፍራት የለበትም! እኔ ያንተ አሽከር ሄጄ እርሱን እዋጋዋለሁ” አለው። ሳኦልም ዳዊትን፦ “አንተ ገና ልጅ ነህ፤ እርሱም ከልጅነቱ ጀምሮ ጦረኛ ስለ ሆነ ይህን ፍልስጥኤማዊ ለመውጋት ትሄድ ዘንድ አትችልም” አለው። ዳዊትም እንዲህ አለ፤ “ንጉሥ ሆይ! እኔ ያንተ አሽከር የአባቴን በጎች የምጠብቅ እረኛ ነኝ፤ አንበሳም ሆነ ድብ መጥቶ ጠቦት በሚነጥቅበት ጊዜ፥ ተከትዬው ሄጄ አደጋ በመጣል የወሰደውን ጠቦት አስጥለው ነበር፤ አንበሳው ወይም ድቡ ወደ እኔ ተመልሶ በሚመጣበትም ጊዜ ጉሮሮውን አንቄ በመምታት እገድለው ነበር። እኔ ያንተ አሽከር አንበሳና ድብ ገድያለሁ፤ ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ የሕያው እግዚአብሔርን ሠራዊት ስለ ተፈታተነ ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል። ከአንበሳና ድብ ያዳነኝ እግዚአብሔር ከዚህም ፍልስጥኤማዊ እጅ ያድነኛል።” ሳኦልም “መልካም ነው! እንግዲህ ሂድ፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሁን!” ሲል መለሰለት። ሳኦልም የገዛ ራሱን የጦር ልብስ ለዳዊት አለበሰው፤ ከነሐስ የተሠራውን የራስ ቊር በዳዊት ራስ ላይ ደፍቶ ጥሩርም አለበሰው፤ ዳዊትም ይህን ዐይነት ልብስ ለብሶ ስለማያውቅ ሰይፉን በጦር ልብሱ ላይ ታጥቆ ለመሄድ ሲነሣ መራመድ አልቻለም፤ ስለዚህ ዳዊት ሳኦልን፦ “ያልተለማመድኩት ነገር ስለ ሆነ ይህን ሁሉ ልብስ ለብሼ መዋጋት አልችልም፤” አለ፤ ስለዚህም ያንን ሁሉ አወለቀ፤ በትሩን አንሥቶ፥ ከወንዝ ዳር አምስት ድቡልቡል ድንጋዮች መርጦ በመልቀም በእረኝነት ኮረጆው ከተተ፤ ወንጭፉንም ይዞ ወደ ፍልስጥኤማዊው ቀረበ። ፍልስጥኤማዊው ጎልያድ ወደ ዳዊት ለመቅረብ መራመድ ጀመረ፤ ጋሻጃግሬውም በፊት በፊቱ ይሄድ ነበር፤ ዳዊት ቀይ፥ መልከ መልካም፥ ትንሽ ልጅ ስለ ነበረ ዳዊትን ጎልያድ ትኲር ብሎ ባየው ጊዜ በንቀት ዐይን ተመለከተው፤ ስለዚህም ጎልያድ ዳዊትን “በትር ይዘህ የምትመጣው እኔ ውሻ ነኝን” ካለው በኋላ በአማልክቱ ስም ረገመው። ቀጥሎም “ወዲህ ና! ሥጋህን ለሰማይ አሞራዎችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ” አለው። ዳዊትም እንዲህ ሲል መለሰ “አንተ ሰይፍ፥ ጦርና ሾተል ይዘህ መጥተህብኛል፤ እኔ ደግሞ አንተ በምትፈታተነውና በእስራኤል ሠራዊት አምላክ ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ፤ በዚህች ቀን እግዚአብሔር በአንተ ላይ ድልን ያጐናጽፈኛል፤ እኔም ራስህን እቈርጣለሁ፤ የፍልስጥኤማውያንንም ወታደሮች ሥጋ ለአሞራዎችና ለአራዊት ምግብ አድርጌ እሰጣለሁ፤ ከዚያም በኋላ መላው ዓለም በእስራኤል ዘንድ አምላክ እንዳለ ያውቃል። እዚህ የተሰበሰቡት ሁሉ እግዚአብሔር የሚያድነው በሰይፍና በጦር አለመሆኑን ያውቃሉ፤ ጦርነቱ የእግዚአብሔር ነውና፤ በእናንተም ላይ ድልን እንድንጐናጸፍ ያደርገናል።” ፍልስጥኤማዊው አደጋ ሊጥልበት ወደ ዳዊት በቀረበ ጊዜ ዳዊት ጎልያድን ለመግጠም ወደ ጦሩ ግንባር እየሮጠ ሄደ። እጁንም ወደ ኮረጆው ከቶ አንዲት ድንጋይ በማውጣት በጎልያድ ላይ ወነጨፈ፤ ድንጋዩም ግንባሩን በጥርቆ ወደ ራስ ቅሉ ገባ፤ ጎልያድም በምድር ላይ በግንባሩ ተደፋ። በዚህም ዐይነት ዳዊት በወንጭፍና በድንጋይ ጎልያድን መትቶ በመግደል ድል አደረገ! በእጁም ሰይፍ አልነበረም። ወደ እርሱም ሮጦ በመሄድ በላዩ ላይ ቆመ፤ የጎልያድንም ሰይፍ ከሰገባው በመምዘዝ ራሱን ቈረጠው። ፍልስጥኤማውያንም የእነርሱ ዝነኛ ተዋጊ ጎልያድ መገደሉን ባዩ ጊዜ ሸሹ።

Free Reading Plans and Devotionals related to አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 17:32-51