የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 15:1-35

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 15:1-35 አማ05

ሳሙኤል ሳኦልን እንዲህ አለው፤ “በሕዝቡ በእስራኤል ላይ ቀብቼ እንዳነግሥህ እግዚአብሔር የላከኝ እኔ ነኝ፤ አሁንም ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር የሚለውን ስማ፤ እስራኤላውያን ከግብጽ በወጡ ጊዜ አማሌቃውያን በመንገድ ላይ እየተቃወሙ አስቸግረዋቸው ስለ ነበረ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር አማሌቃውያንን ለመቅጣት ወስኖአል። ሄደህ በዐማሌቃውያን ላይ አደጋ በመጣል ያላቸውን ሁሉ ደምስስ፤ ከእነርሱ ምንም ነገር አታስቀር፤ ወንዶችን፥ ሴቶችን፥ ልጆችንና ሕፃናትን፥ ከብቶችን፥ በጎችን፥ ግመሎችንና አህዮችን ሁሉ ግደል።” ሳኦልም ሠራዊቱን በአንድነት ጠርቶ ጤሌም በሚባል ስፍራ ቈጠራቸው፤ የወታደሮቹም ብዛት ከእስራኤል ሁለት መቶ ሺህ ከይሁዳ ዐሥር ሺህ ሆነው ተገኙ፤ ከዚያም እርሱና ሠራዊቱ ወደ ዐማሌቃውያን ከተማ ሄደው በአንድ ደረቅ ጅረት ውስጥ ደፈጣ አደረጉ፤ “እስራኤላውያን ከግብጽ በወጡ ጊዜ ቸርነት ስላደረጋችሁላቸው እናንተን ከአማሌቃውያን ጋር እንዳላጠፋ ከዐማሌቃውያን ተለይታችሁ ሂዱ” ብሎ ሳኦል ለቄናውያን ነገራቸው። እነርሱም ከዐማሌቃውያን ተለይተው ሄዱ። ሳኦል ከሐዊላ ጀምሮ በግብጽ ምሥራቅ እስከምትገኘው እስከ ሹር በሚያደርሰው መንገድ ሁሉ ዐማሌቃውያንን ድል አደረገ። የዐማሌቅ ንጉሥ የነበረውን አጋግን በሕይወት ማርኮ፥ ሕዝቡን ሁሉ በሰይፍ ፈጀ፤ ነገር ግን ሳኦልና ሠራዊቱ የአጋግን ሕይወት አተረፉ፤ እንዲሁም ምርጥ ምርጥ የሆኑትን በጎችና የቀንድ ከብቶች፥ የሰቡ ሰንጋዎችንና ጠቦቶችን ከዚህም ጋር መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ አላጠፉም፤ እነርሱም ያጠፉት የማይረባውንና የማይጠቅመውን ነገር ብቻ ነበር። እግዚአብሔር ሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ “ሳኦል እኔን ትቶአል፤ ትእዛዜንም ስላልጠበቀ እርሱን በማንገሤ ተጸጸትሁ፤” ሳሙኤልም በዚህ ነገር ተቈጥቶ ሌሊቱን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር በመጮኽ ማለደ፤ በማግስቱም ማለዳ በመነሣት ሳኦልን ፈልጎ ለማግኘት ሄደ፤ ሳኦል ለራሱ ሐውልት ወዳቆመባት ወደ ቀርሜሎስ ከተማ ከደረሰ በኋላ ተመልሶ ወደ ጌልጌላ መሄዱን ሰማ፤ ሳሙኤል ወደ ሳኦል ሄደ፤ ሳኦልም “ሳሙኤል ሆይ! እግዚአብሔር ይባርክህ፤ እኔም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ፈጽሜአለሁ” አለው። ሳሙኤልም “ታዲያ ይህ የምሰማው የቀንድ ከብትና የበግ መንጋ ድምፅ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። ሳኦልም “እነርሱ ወታደሮቼ ከዐማሌቃውያን የማረኩአቸው ናቸው፤ ምርጥ ምርጥ የሆኑትን የቀንድ ከብቶችና በጎች ለአምላክህ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ለማቅረብ አምጥተዋል፤ የቀሩትን ግን በሙሉ ደምስሰናል” ሲል መለሰለት። ሳሙኤልም “ተወው በቃ፤ እግዚአብሔር ትናንትና ማታ የገለጠልኝን እነግርሃለሁ” አለው። ሳኦልም “እሺ ንገረኝ” አለ። ሳሙኤልም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “አንተ ስለ ራስህ የነበረህ ግምት አነስተኛ ቢሆንም የእስራኤል ነገዶች መሪ አልሆንክምን? እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ቀብቶ አንግሦሃል፤ ኃጢአተኞች የሆኑትን እነዚያን አማሌቃውያንን እንድትደመስስ ልኮሃል፤ እስኪጠፉም ድረስ እነርሱን ግደል ብሎ ነግሮሃል። ታዲያ ስለምን ትእዛዙን አልፈጸምክም? ለምርኮስ በመሳሳትና በመስገብገብ እግዚአብሔርን ደስ የማያሰኝ ነገር ስለምን አደረግህ?” ሳኦልም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ፈጽሜአለሁ፤ ባዘዘኝም መሠረት ዘምቻለሁ፤ ንጉሥ አጋግን ብቻ ማርኬ ሳመጣ ሌሎችን ዐማሌቃውያን ሁሉ ገድያለሁ፤ ነገር ግን ወታደሮቼ የማረኩአቸውን ምርጥ ምርጥ የሆኑ በጎችንና የቀንድ ከብቶችን አልገደሉአቸውም፤ ይህን በማድረግ ፈንታ በጌልገላ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርገው ለማቅረብ አምጥተዋቸዋል።” ሳሙኤልም እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር የሚወደው የቱን ይመስልሃል? መታዘዝን ወይስ ቊርባንና መሥዋዕት ማቅረብን? ለእርሱ መታዘዝ ምርጥ የበግ መሥዋዕት ከማቅረብ ይበልጣል፤ በእግዚአብሔር ላይ ማመፅ እንደ ሟርተኛነት፥ የትዕቢት እልኸኛነትም ጣዖትን በማምለክ ኃጢአት እንደ መሥራት ይቈጠራል፤ አንተ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለ ተውክ በንጉሥነትህ እንዳትቀጥል እርሱም አንተን ትቶሃል።” ሳኦልም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “አዎ፤ እኔ ኃጢአት ሠርቼአለሁ፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝና አንተ የሰጠኸኝን መመሪያ አልጠበቅሁም፤ ወታደሮቼን በመፍራት እነርሱ የፈለጉትን ሁሉ አደረግሁ፤ አሁን ግን እለምንሃለሁ በደሌን ይቅር በለኝ፤ በዚያ ለእግዚአብሔር እሰግድ ዘንድ ከእኔም ጋር ወደ ጌልጌላ ተመለሰ።” ሳሙኤልም “እኔ ከአንተ ጋር አልሄድም፤ አንተ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መፈጸም ትተሃል፤ አንተም የእስራኤል ንጉሥ ሆነህ እንዳትቀጥል እርሱ ትቶሃል” ሲል መለሰለት። ከዚያም በኋላ ሳሙኤል ተለይቶ ለመሄድ ፊቱን መለሰ፤ ሳኦል ግን ሳሙኤል እንዳይሄድበት የካባውን ጠርዝ ሲይዝ ተቀደደ፤ ሳሙኤልም ሳኦልን እንዲህ አለው፤ “ዛሬ እግዚአብሔር የእስራኤልን መንግሥት ቀዶ ከእጅህ በመውሰድ ለተሻለ ለሌላ ሰው ሰጥቶታል፤ የእስራኤል ክብር የሆነ እግዚአብሔር አያብልም፤ ሐሳቡንም አይለውጥም፤ እርሱ እንደ ሰው ስላልሆነ ሐሳቡን አይለውጥም።” ሳኦልም “በእርግጥ በደል ሠርቼአለሁ፤ ይሁን እንጂ ሌላው ቢቀር በሕዝቤ መሪዎችና በእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ፊት አክብረኝ፤ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር እሰግድ ዘንድ ከእኔ ጋር አብረህ ሂድ” ሲል ለመነው። ስለዚህም ሳሙኤል አብሮት ወደ ጌልጌላ ሄደ፤ ሳኦልም ለእግዚአብሔር ሰገደ። ሳሙኤልም “ንጉሥ አጋግን ወደዚህ አምጣልኝ!” ሲል ትእዛዝ ሰጠ፤ አጋግም በፍርሃት እየተንቀጠቀጠ ወደ እርሱ መጣ፤ በልቡም “ሞት እንዴት መራራ ናት!” እያለ ያስብ ነበር፤ በዚህም ጊዜ ሳሙኤል “የአንተ ሰይፍ ብዙዎች እናቶችን ልጅ አልባ እንዳደረገቻቸው፥ የአንተም እናት ልጅ አልባ ሆና ትቀራለች” አለው። ከዚህም በኋላ በጌልገላ በሚገኘው በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት አጋግን ቈራርጦ ጣለው። ከዚህም በኋላ ሳሙኤል ወደ ራማ ሄደ፤ ንጉሥ ሳኦልም ወደ ጊብዓ ተመለሰ። ከዚያን ሰዓት ጀምሮ ሳሙኤል በነበረበት ጊዜ ሁሉ ንጉሥ ሳኦልን በዐይኑ አላየውም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሳኦልን በእስራኤል ላይ በማንገሡ ተጸጽቶ ስለ ነበር፥ ለእርሱ በማዘን ያለቅስለት ነበር።